የሠራተኛው የበጋ ወራት ውድድሮች በወሳኝ ምዕራፍ

ጥር 19/2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተጀመረው የሠራተኛው የበጋ ወራት ውድድር ባለፉት ወራት በተለያዩ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ሲካሄዱ ቆይተው ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበር ኮንፌዴሬሽን(ኢሠማኮ) አዘጋጅነት የሚካሄዱት እነዚህ ውድድሮች በመጪው ሰኔ ወር ይጠናቀቃሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች የሚደረጉ ፉክክሮችም ወደ ፍፃሜ እያመሩ ይገኛሉ።

በሁለት ዲቪዚዮን ተከፍሎ በሚካሄደውና ጠንካራ ፉክክር በሚያስተናግደው እግር ኳስ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ሲካሄዱ የቆዩ ጨዋታዎች ተገባደዋል፡፡ በዚህ ዲቪዚዮን የፍፃሜ ተፋላሚ የሆኑ ሁለት ክለቦችም ባለፈው ሳምንት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታቸውን አድርገው ተለይተዋል፡፡ በዚህም ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ አዋሽ ወይን ፋብሪካን በግማሽ ፍፃሜው ፍሊሚያ 3ለ1 በመርታት የዋንጫ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በተመሳሳይ ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኮካ ኮላ ሞኤንኮ ኩባንያ ጋር በመለያ ምት 10 ለ 9 አሸንፎ ወደ ዋንጫ ያለፈ ቡድን ሆኗል፡፡ በውድድሩ ፍፃሜም ቃሊቲ ብረታ ብረትና ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ዋንጫን ለማንሳት የሚፋለሙ ይሆናል፡፡ በግማሽ ፍፃሜው የተሸነፉት አዋሽ ወይን ፋብሪካና ሞኤንኮ ኩባንያ ደግሞ በመጪው እሁድ በጎፋ ካፕ ሜዳ የሚገናኙ ይሆናል፡፡

በጉጉት የሚጠበቀውና ጠንካራ ፉክክር የሚያስተ ናግደው የአንደኛ ዲቪዚዮን የእግር ኳስ የዙር ውድድርም በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ዘጠኝ ክለቦች ሲፋለሙበት በቆዩት በአንደኛ ዲቪዚዮን ውድድር የተለያዩ ቡድኖች ተቀራራቢ ነጥብ መሰብሰባቸው የፉክክሩን መጨረሻ አጓጊ አድርጎታል፡፡ የውድድር ዓመቱ የዋንጫ አሸናፊ ለመሆን የተለያዩ ቡድኖች እድል ያላቸው ሲሆን በቀጣይ የሚደረጉ ጨዋታዎችም ቻምፒዮኑ የሚለይባቸው ይሆናሉ፡፡

የዋንጫው አሸናፊ ለመሆን የተሻለ እድል የያዙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ተቀራራቢ ነጥብ ይዘው አንድ አንድ ጨዋታ ይቀራቸዋል፡፡ ንግድ ባንክ በ19 ነጥብና 13 ግብ ቀዳሚ ሆኖ ለማጠናቀቅ የቀረውን አንድ ጨዋታ ማሸነፍ ወይ አቻ መውጣት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ጨዋታም ከዮሐንስ ቢፍ ኢን ውሃ ጋር ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይ አንድ ጨዋታ እየቀረው በ16 ነጥብና 18 ግብ ሁለተኛ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች በቀሪው ጨዋታ ኢትዮ ቴሌኮምን ይገጥማል፡፡ ንግድ ባንክ የመጨረሻውን ጨዋታ ተሸንፎ ክፍያ መንገዶች ተጋጣሚውን ማሸነፍ ከቻለ በግብ ክፍያ ስለሚበልጥ ዋንጫውን የማሸነፍ እድል ይኖረዋል። በዚህም ምክንያት ሁለቱ ቡድኖች ከተጋጣሚያቸው ጋር የሚኖራቸው ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ሆኗል፡፡

ከእግር ኳስ ባሻገር በሌሎች የስፖርት ዓይነቶች የሚደረጉ ፉክክሮችም ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፣ ነገና ከነገ በስቲያም በሁለቱም ፆታ በቮሊቦል፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ከረንቦላ፣ ዳርትና ቼዝ ውድድሮች በተለያዩ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ወሳኝ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ፡፡

የ2016 የበጋ ወራት ውድድሮች ሰላሳ የሚጠጉ የሠራተኛ ስፖርት ማህበራትን በማሳተፍ “የሠራተኛው ስፖርት ለሰላም፣ ለጤናና ለምርታማነት” በሚል መርህ ባለፉት አራት ወራት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ሰኔ አጋማሽ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢሠማኮ የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ ያደረሱን መረጃ ያመለክታል፡፡ በነዚህ ወራት የውድድሩ ጉዞ የቤት ውስጥ ውድድሮችን ጨምሮ በ10 የስፖርት ዓይነቶች ፉክክር በሚደረግበት የበጋ ወራት ውድድር በሁለቱም ፆታ በአትሌቲክስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቮሊቦል፣ ዳማ፣ ቼስ፣ ገበጣ፣ ገመድ ጉተታና ሌሎችም የስፖርት ዓይነቶች ከ1500 በላይ ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በዚህ የበጋ ወራት ውድድር የሠራተኞች ስፖርታዊ ተሳትፎ የሚሰሩበትን ተቋም ከማስተዋወቅና የቤተሰባዊ ባለድርሻነት ስሜትን ከማዳበር ባለፈ ጤናማ፣ ንቁና ምርታማ የሚሆኑበት መድረክ ነው፡፡ እነዚህ ውድድሮች ሠራተኞች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋን ለማፍራት፣ የሠራተኞችን አንድነት ለማጠናከር ፣ የልማት ተቋሞቻቸውን ማስተዋወቀና የባለቤትነት ስሜታቸው እንዲጠናከር አላማ በማድረግ የሚከናወኑ ናቸው። በኢትዮጵያ ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ አንጋፋ የስፖርት መድረኮች አንዱ የሆነው ይህ የሠራተኞች ውድድር በዚህ ዘመን ሠራተኛው በስፖርት የሚያደርገው ተሳትፎ ለሚሠራበት ድርጅት ውጤታማነት የሚኖረውን አስተዋጽኦ የጎላ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ስፖርቱ የሠራተኛውን አንድነትና ለጋራ ጉዳይ አብሮ የመቆም ባሕሉን አጠናክሮበታል።

በነዚህ ውድድሮች ላይ ተቋሞቻቸውን ወክለው በሚካፈሉ ተወዳዳሪዎች መካከል ከተቋም ጋር ያለውን መቀራረብ፣ ልምድ ማካፈል እንዲሁም ለተለያዩ ክለቦች ግብዓት የሚሆኑ ስፖርተኞች ማፍራት የቻለ ውድድር መሆኑንም በሠራተኛው ስፖርት ውስጥ ረጅም ዓመታትን ያሳለፉ ሰዎች ይመሰክራሉ። በውድድሩ በሚካፈሉ ተቋማት መካከል በሚፈጠረው ፉክክር ምክንያትም ሠራተኛው የተሻለ ውጤት ይዞ ለመምጣት ሲሽቀዳደምና ለዓመታዊ ውድድሩ ዝግጅት ሲያደርግ መመልከት የተለመደ ነው፡፡

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You