ፍላጎቶችን ማጣጣም የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለመፍጠር

በአንድ ሀገር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ልዩነቶችንም ሆነ እነሱን ተከትሎ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ መፍታት የሚችል ሀገራዊ ማህበራዊ የአስተሳሰብ መሠረት መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህም ደግሞ እንደ ሀገር ያሉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን ደጋግሞ በአግባቡ መገምገም፤ በአዎንታዊ ሆነ በአሉታዊ መልኩ በማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ፍላጎት ላይ የሚፈጥሩትን ጫና አጥርቶ ማወቅ ያስፈልጋል ።

በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር አሁን ባለንበት የለውጥ ወቅት፤ ለውጡ እንደ ቀደሙት ዘመናት ለውጦች ብዙ ያልተገባ ዋጋ አስከፍሎን የተፈለገውን ውጤት ሳያስገኝ እንዳይመክን፤ ከሁሉም በላይ ልዩነቶችን በመነጋገር መፍታት፤ ዘላቂ ሀገራዊ ሰላም ማስፈን የሚያስችል አዲስ ማህበረሰባዊ የፖለቲካ ባህል ፣ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነት መፍጠር ይኖርብናል።

ለእኛ ያለንበትን ድህነት እና ኋላ ቀርነት አሸንፎ መውጣት እንደ ሀገር የህልውና ጉዳይ ከሆነብን ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ይህንን የህልውና አደጋ የምንሻገረው ዘመኑን በሚዋጅ የልማት እሳቤ ነው። ለዚህ ደግሞ ሰላም ወሳኙ ጉዳይ ይሆናል። ዘላቂ ሰላም መፍጠር የምንችለው ደግሞ የተለያዩ ፍላጎቶችን አጣጥሞ የሚሄድ ማህበረሰባዊ የአስተሳሰብ መሠረት መገንባት ስንችል ነው ።

ያለ ሰላም የበለጸገች ሀገር መፍጠር ቀርቶ ነገን ተስፋ አድርጎ መቆም አይቻልም። ለዚህ በየዘመኑ ከተፈጠሩ የለውጥ ንቅናቄዎች ማግስት እንደ ሀገር ያጋጠሙን ፈተናዎች እና ፈተናዎቹን ለመሻገር የከፈልናቸው ያልተገቡ ዋጋዎችን ማሰብ ይበቃል። ይህም ለለውጥ እሳቤዎች ስኬት ሰላም የቱን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያመላክታል።

በዘመናት መካከል እንደ ጥላ እየተከተለ ትውልዶችን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ያለውን ሀገራዊ የሰላም እጦት ለዘለቄታው መፍታት አሁን የሁሉንም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ ሆኗል፤ አዲስ የአስተሳሰብ ባህል መፍጠር እና ማዳበር ፤ ለዚህ የሚሆን ከትናንት የተማረ አእምሮ መፍጠርም ትኩረት ሰጥተን ልንሰራው የሚገባን ዋነኛ የቤት ሥራችን መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል።

አሁን ያለንበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሀገራዊ ሰላም እጦት ምክንያት የሆኑ ችግሮቻችንን በትክክል ተረድተን ፤ በችግሮቹ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ይዘን አለቅ ካለን የግጭት አዙሪት የሚያወጣንን መፍትሔ ለማፈላለግ አብዝተን የምንተጋበት ነው ።

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ እውነታዎችን በአግባቡ ተረድተን እንደ ሀገር የጀመርነው ለውጥ በመላው ሕዝባችን ውስጥ የፈጠረውን መነቃቃት እንደ አንድ ታሪካዊ የመሻገሪያ አቅም ወስደን ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ እንደ ሀገር ያለምናቸውን የለውጥ ህልሞች እውን ለማድረግ በተሻለ የኃላፊነት መንፈስ የምንቀሳቀስበት ነው ።

ታሪካዊ ጠላቶቻችን እና በየዘመኑ ድህነትን አሸንፈን ለመውጣት የምናደርገው ጥረት ሰላም የሚነሳቸው ኃይሎች በእያንዳንዱ የለውጥ ክስተት ማግስት የውስጥ መሻታችንን ለማዳፈን ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። በዚህም በብዙ ትውልዶች መስዋእትነት ዛሬ ላይ የደረሰችውን ሀገራችንን ሕልውና ተፈታትነዋል።

ያልተገራ ፍላጎት ካላቸው የሀገር ውስጥ ኃይሎች ጋር በመናበብና በመቀናጀት ጭምር ለብዙ ወንድሞቻችን ሞት እና የአካል ጉዳት ፣ መፈናቀል እና ስደት ፣ ከፍ ላለ የሀገር ሀብት ውድመት ምክንያት ሆነዋል። የለውጡን ግለት በማቀዛቀዝ በዜጎች ሀገራዊ ተስፋ ላይ ጥርጣሬ ጭረዋል።

ለጠላቶቻችን የጥፋት ሴራ አቅም በመሆን የሚያገለግለው እንደ ሀገር በየዘመኑ ብዙ ዋጋ ያስከፈለን የፖለቲካ ባህላችን፣ ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል አስገድዶናል። እንደ ሀገር ችግሮችን ተነጋግሮ መፍታት የሚያስችሉ ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶች ቢኖሩንም፤ ለእነሱ ቅድሚያ ሰጥተን መንቀሳቀስ አለመቻላችን “ሸክላ ሠሪ በገል ይበላል” እንደሚባለው ሆኖብናል፡፡

በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች የቱን ያህል መስዋእትነት ከፍለው ባለሀገር እንዳደረጉን በየእለት ትርክታችን አብዝተን እየተረክን ፣ ከትርክት ባለፈ በልዩነቶቻችን ዙሪያ ቁጭ ብሎ መነጋገር ባለመቻላችን ፣ የትውልዶችን መስዋእትነት በሚፈታተን ፣ ሀገርን እንደ ሀገር የህልውና ስጋት ውስጥ በሚጨምር ያልተገባ መንገድ ላይ ቆመን እየዳከርን ነው።

ይህንን እንደጥላ የሚከተለንን እና ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ያለውን ሀገራዊ የሰላም ችግራችንን ተሻግረን ለራሳችንም ሆነ ለመጪዎቹ ትውልዶች የተሻለች ሀገር ለመፍጠር አሁን በእጃችን ያለውን ሀገራዊ የምክክር መድረክ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል። በተለይም የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው የፖለቲካ ቡድኖች ፍላጎታቸውን ዘለቂ ለሆነ ሀገራዊ ሰላም እና ለሕዝባችን የመልማት ፍላጎት መስዋእት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

መላው ሕዝባችንም የእሱም ሆነ ፤ በዘመናት መካከል ትውልዶች የተመኙት የበለጸገች ሀገርን የማየት ተስፋ እውን ሊሆን የሚችለው የተለያዩ ፍላጎቶችን ማጣጣም የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደ ሀገር መፍጠር ስንችል መሆኑን በመረዳት ሕዝቡ ራሱን ለዚህ እውነታ ማዘጋጀት፤ አስተሳሰቡ ገዥ እንዲሆን ሁለንተናዊ ጫና መፍጠር ይጠበቅበታል ።

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You