አለመግባባቶች፣ ግጭቶችና ጦርነቶች ኢትዮጵያን ብዙ አሳጥተዋል፤ ከሕዝቦቿም ብዙ አጉድለዋል፡፡ እነዚህ ሀገሪቱንና ሕዝቧን ለከፋ ጉዳት ሲዳርጉ የቆዩ ችግሮች ያለመነሻ የተፈጠሩ አይደሉም፡፡ እነዚህን መነሻዎች በመለየት ተገቢው ርምጃ ባለመወሰዱ ሳቢያ ዜጎችና ቡድኖች አጣን ያሉትን ሁሉ በኃይል ለማግኘት ርምጃዎች ሲወስዱ ኖረዋል፤ በዚህም ከሁሉም ወገን የዜጎች ሕይወት እንደ ቀጥል ረግፏል፤ አካላቸውን ያጡ እንዲሁም ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች የሚባሉትም አያሌ ናቸው፡፡
በግጭትና ጦርነት ሀገሪቱንና ሕዝቦቿን ከድህነት አረንቋ በማውጣት በብልጽግና ጎዳና ለማራመድ ትልቅ አቅም በመሆን ሊያገለግል የሚችል የዜጎችና የሀገር ሀብት ወድሟል፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ በሚፈለገው ልክ እንዳይመጣ፣ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትና ልማትም እንዲሁ በሚፈለገው ልክ እንዳይካሄድ ሆኗል፡፡
የችግሩ ምልልስና አሳሳቢነት ሀገሪቱ ችግሮቹ በጦርነትና ግጭት ሳይሆን በውይይት መፈታት አለባቸው ወደሚል ድምዳሜ አድርሷታል፡፡ የለውጡ መንግሥትም ይህን ታሪክ የሚቀይር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፤ የምክክር ተሳታፊዎችን ከአብዛኞቹ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመመልመል ሥራ ተጠናቆ አሁን ደግሞ በምክክሩ ውይይት የሚደረግባቸው አጀንዳዎች ወደሚሰበሰቡበትና ምዕራፍ ተገብቷል፡፡
አጀንዳ የመሰብሰቡ ሥራም ትናንት በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡ እስከ ግንቦት 27 ቀን 2016 የሚካሄደውና ከሁለት ሺ 500 በላይ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበት ይህ የምክክር መድረክ ሶስት ጉዳዮች የሚካሄዱበት ስለመሆኑ ኮሚሽኑ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በዚህ እርከን ላይ የሚመጡ ተሳታፊዎች በምክክርና በውይይት የእጀንዳ ሃሳቦችን ይሰጣሉ፣ አጀንዳዎቻቸውን የጋራ በማድረግ ያደራጃሉ፤ የመፍትሄ ሃሳብ ያንሸራሽራሉ፡፡ ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውንም ይመርጣሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካሄድ በጀመረው የምክክር መድረክም ይሄው ይከናወናል።
አዲስ አበባ የዚህ ምክክር መድረክ ወሳኝ ምዕራፍ ጅማሬ መሆኗ ብዙ ፋይዳዎች አሉት፤ ከተማዋ የሀገሪቱ ዋና ከተማ መሆኗ፣ የመላ ሀገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወዘተ በብዛት ያሉባት እንደመሆኑ መድረኩን በሚገባ መጠቀም ከተቻለ አብዛኛዎቹን የሀገሪቱን አጀንዳዎችን እዚሁ ማግኘት የሚችልበት ዕድል ሊኖር ይችላል፤ በክልሎች እና በሌሎች ከተሞች የሚካሄዱ ተመሳሳይ መድረኮች ውጤታማ እንዲሆኑ ትልቅ አቅም የሚፈጠርበትም ነው፡፡
በመድረኩ እንደሚከናወን የሚጠበቀው ተግባር ሲታሰብ የመድረኩ ተሳታፊዎች ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ ተሳታፊዎች ለአዲስ አበባ ከተማም ለሀገርም የሚጠቅሙ ወሳኝ ጉዳዮችን በማንሳት መወያየትና ለሀገራዊ ምክክር ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ባለመግባባት ሳቢያ ዜጎችን ለግጭትና ጦርነት የዳረጉ ግዙፍ ጉዳዮችን በአጀንዳነት ማንሳትና መወያየት ከዚያም መፍትሄ ማመላከት አለባቸው፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ አንደ ሀገር በእጅጉ ሲፈለግ የኖረ ነው፡፡ ይህን መድረክ እውን ለማድረግ ብዙ ዋጋ ተከፍሏል፡፡ አሁን ደግሞ ዜጎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች ፣ ወዘተ በየወኪሎቻቸው አማካይነት በመድረኩ የሚሳተፉበት ወቅት ላይ ተደርሷልና ለእዚህ ምዕራፍ በስኬት መጠናቀቅ መሥራት ይገባል፡፡
ከስንት አንዴ በሚገኝ፣ የሀገሪቱንና የሕዝቦቿን የዘመናት ጥያቄ ይመልሳል ተብሎ በሚጠበቅ በዚህ ታላቅ መድረክ መሳተፍ መታደል ነው፤ በመድረኩ ብቻም ሳይሆን ከመደረኩ ውጪም ሃሳብ ማቅረብ የሚቻልባቸው አግባቦች ያሉ እንደመሆናቸው እንደ ዜጋም መታደል ነው ፡፡ ይህን መልካም አጋጣሚ አሟጦ መጠቀም መቻል ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ሲንከባለሉ የመጡ ወሳኝ ችግሮችን በመፍታት ሂደት ዐሻራ ማኖርም ነው፡፡
በምክክሩ ሃሳብን በነጻነት ማቅረብ፣ በቀረቡ ሃሳቦች ላይም እንዲሁ በነጻነት መወያየትና ሃሳቦቹን ለቀጣይ ምክክር ማደራጀት ይጠበቃል፡፡ ይህ ደግሞ ሃሳብ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን በሚገባ መደማመጥንና በጥልቅ መወያየትን ይጠይቃል፡፡ በዚህች ሀገር ከዚህ በኋላ አጀንዳን ለማስፈጸም ግጭትና ጦርነት ውስጥ ላለመግባት ነው እየተሠራ ያለው፤ አጀንዳ በውይይትና ምክክር አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ነው ምክክሩ የሚካሄደው፡፡
ይህን መድረክ በንቃት በመሳተፍ የምክክር መድረኩ ዓላማዎች እንዲሳኩ ማድረግ ከምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ብዙ ይጠበቃል፡፡ በአዲስ አበባ የምክክር መድረኩ አጀንዳ የማሰባሰብ መርሃ ግብር ትናንት በተጀመረበት ወቅት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደተናገሩትም፤ በሰከነ እና በተረጋጋ ሁኔታ በመምክር ወደ መግባባት መድረስ አማራጭ የሌለው ብቸኛ ሀገራዊ መፍትሄ ነው፡፡ መርሀ ግብሩ አጀንዳዎች የሚለዩበት መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ ለሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ ውጤታማነት ቁልፍ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡
እንደሚታወቀው፤ ዜጎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ወዘተ እስከ አሁንም መግባባትን ለሚጠይቁ ሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ ያሉትን በተናጠልም በተለያዩ መድረኮችም ሲያንጸባርቁ ፣ ሰፊ ሀገራዊ መድረክ እንዲዘጋጅም ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ እነሆ አሁን ያ መድረክ ተፈጥሮ፣ የተለያዩ የዝግጅት ምዕራፎችም ተደርገው እነሆ ለአጀንዳ ማሰባሰቡ ምዕራፍ ተደርሷል፡፡
‹‹ሜዳውም ፈረሱም ይኸው›› እንደሚባለው መድረኩ ሃሳብ መስጠትን፣ ማደራጀትንና መፍትሄ ማመላከትን የሚጠይቅ እንደመሆኑ የመድረኩ ተሳታፊዎች፣ መላው ሕዝብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌሎች አካላት በተለያዩ መንገዶች በእጅጉ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሀገሪቱንና የዜጎቿን ዘመናትን የተሻገሩ ችግሮችን ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/ 2016 ዓ.ም