ብልሹ አሠራርን እንደሚከላከል የታመነበት የንግዱ ዘርፍ አዲስ መመሪያ

መንግሥት የንግዱ እንቅስቃሴ በሕግና ሥርዓት እንዲመራ ለማድረግ የሚያስችሉ ሕጎችን በማውጣት፣ በሕጎቹ ላይም ግንዛቤ በማስጨበጥ ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል:: አስፈጸሚው አካልም የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎችን በአግባቡ ማከናወን እንዲችል አዋጆችን፣ መመሪያና ድንቦችን ወዘተ. በሚገባ ተረድቶ የንግድ ሥራውን በአግባቡ እንዲመራ በማድረግ ላይ በትኩረት ይሠራል:: የንግዱ ማህበረሰብም እነዚህን ሕጎች አክብሮ እንዲሠራ ለማድረግ ግንዛቤ ከማስረጽ አንስቶ፣ ቅሬታዎች ካሉትም መድረኮችን በማዘጋጀት አዳምጦ መፍትሔ የማመላከት ሥራዎችን ይሠራል::

ይህ ሁሉ ሆኖም ግን በንግድ ሥራው ላይ ክፍተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፤ ሲያጋጥሙም ኖረዋል:: በአንዳንድ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በኩል የሕግ ጥሰቶች ሲፈጸሙ፣ ሕጎች የንግዱ ማህበረሰብን አላሠራ ሲሉ፣ ተቆጣጣሪ አካላት ከሕግ ውጪ የሚሠሩበት ሁኔታ ሲያጋጥም ይስተዋላል:: ይህን ተከትሎ የንግዱ ማህበረሰብ ቅሬታዎችን ሊያነሳ፣ መንግሥትም ቅሬታዎቹን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ይታያል:: እነዚህ ጥረቶቹ አዋጆችን፣ መመሪያዎችን እስከማሻሻል ሊደርሱ ይችላሉ::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በከተማዋ የሚከናወኑ የንግድ ሥራዎች ቁጥጥርና ክትትልን በተመለከተ በቅርቡ አንድ መመሪያ አውጥቷል:: ይህ የቁጥጥርና ክትትል መመሪያ የንግዱን አሠራር ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ለማድረግ ያስችላል በሚል ታምኖበታል:: ‹‹የመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሠራር ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 159/2016›› በሚል የተዘጋጀው ይህ መመሪያ ወደ ተግባር መሸጋገሩን ቢሮው ሰሞኑን አስታውቋል። በንግድ ቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች ላይ ነጋዴውንም ሆነ አስፈፃሚ አካላትን ያካተተ ማሻሻያ ተደርጎ በቅርቡ ወደ ተግባር መግባቱን አመልክቷል።

መመሪያውን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በቅርቡ በሰጠው ማብራሪያ ላይ እንደተመለከተው፣ በአዲሱ የመንደር ንግድ ቁጥጥር አሠራር ሥርዓት መመሪያ ላይ የወረዳ የንግድ ቁጥጥር ባለሙያ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድ ሕጉ የሚፈቅድለት እስከምን ድረስ እንደሆነ በግልጽ ሰፍሯል። መመሪያው በተለይ በወረዳ ባሉ የንግድ ሥራዎች ላይ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራ የሚያከናውኑ ባለሙያዎች አሠራር ወጥነት ባለው መልኩ እንዲመራ ያስችላል፤ ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ያግዛል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ቅድስት ስጦታው፤ የመመሪያውን ይዘት እና አተገባበርን አስመልክቶ በተሰጠ በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳስታወቁት፤ መመሪያው ከንግድ ቁጥጥር ሥርዓት ጋር በተያያዘ አዲስ ወጥነት ያለው አሠራር ለመተግበር ያግዛል። በዚህ መመሪያ ላይ በንግድ ቁጥጥር ሥራው በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር እርከኖች የሚወሰኑ አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃዎች በግልጽ ተካተዋል።

ምክትል ኃላፊዋ ቀደም ሲል በወጣ መመሪያ መሠረት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን አስታውሰው፣ በሥራ ሂደትም ሲገጥሙ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት በሚል አዲሱ መመሪያ መውጣቱን አስታውቀዋል:: የቢሮው ባለሙያዎች በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለቁጥጥርና ክትትል ሥራ በሚሰማሩበት ወቅት ወጥ፣ ግልጽና ፍትሐዊ በሆነ አሠራር መሥራት እንደሚያስችላቸው አብራርተዋል።

አዲሱ መመሪያ በዋናነት ሁለት ጉዳዮች ላይ ማተኮሩን ጠቁመው፤ መመሪያው በየደረጃው የሚካሄደውን የንግድ ቁጥጥርና ክትትል ሥርዓት ፍትሐዊ፣ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል። ይህም የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም ሸማቹ ኅብረተሰብ ከንግድ ሥርዓቱ የሚጠብቀውን አገልግሎት በተገቢው መልኩ እንዲያገኙ ታስቦ መውጣቱን ጠቅሰው፤ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ ሕገወጥ ድርጊቶችን ለማረም እንደሚያስችል ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በሁለተኛነት ደግሞ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ተጠያቂነት ያለበት የክትትል እና ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዲሱ መመሪያ ወጥቷል:: መመሪያው በንግድ ቁጥጥርና ክትትል ሥርዓቱ ውስጥ ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን በአሠራር ለመድፈንና ከማእከል እስከ ወረዳ ባሉ የንግድ ዘርፎች የሚካሄዱ የንግድ ቁጥጥር ሥራዎችን ወጥነት ባለው መልኩ ለማካሄድ ይረዳል።

በመመሪያው መሰረት በወረዳዎች ደረጃ የሚካሄድ የንግድ ቁጥጥርና ክትትል ሥራ ወረዳዎች የንግድ ድርጅቶችን ቁጥር፣ የቆዳ ስፋትና የባለሙያዎችን ቁጥር ታሳቢ ባደረገ መልኩ በመንደር በመከፋፈልና ከሁለት እስከ ሦስት የሚደርሱ የወረዳ የቁጥጥር ባለሙያዎችን በመመደብ ይተገበራል።

እንደ ምክትል የቢሮ ኃላፊዋ ማብራሪያ፤ ከዚህም ባሻገር መመሪያው የወረዳ የንግድ ቁጥጥር ባለሙያዎች ከንግድ ጥፋቶች ጋር በተያያዘ ለቅርብ ኃላፊዎቻቸው በጽሑፍ በማሳወቅ ከጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ማሸግ ድረስ የሚወስዷቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እንዲገደቡ ተደርገዋል፤ እነዚህ ጉዳዮችም የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲነግዱ በተገኙ እንዲሁም ባልታደሰ፣ በታገደ ወይም በተሰረዘ የንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የተገኙ የንግድ ድርጅቶችን የተመለከቱ ብቻ መሆናቸውን መመሪያው በግልፅ አስፍሯል።

ይሁንና የወረዳ የንግድ ቁጥጥር ባለሙያዎች በቁጥጥርና ክትትል ወቅት በሚደርሱባቸው ሌሎች ጥፋቶች ላይም እርምጃ መውሰድ ሳይኖርባቸው ጥፋቱን በጽሑፍ ለወረዳቸው ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊ የማሳወቅ፣ ኃላፊውም ለክፍለ ከተማ ንግድ ጽ/ ቤት ጥፋቱን በግልፅ ጠቅሶ ሪፖርት የማድረግ፣ በተመሳሳይም የክፍለ ከተማው ንግድ ጽ/ቤት ለቢሮው በጽሑፍ ሪፖርት በማድረግና ጥፋቱን በማሳወቅ ከቢሮው በሚሰጠው የውሳኔ ሃሳብ መሠረት ተግባሪያዊ እንዲደረግ ለወረዳው የማሳወቅና አፈጻጸሙንም የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖርበታል።

ከዚህ በተጨማሪ መመሪያው ከከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የንግዱ ማህበረሰብ ጥቆማ ማቅረብ የሚችልበት እንዲሁም በደረጃው በሚተላለፉ ውሳኔዎች ላይ ቅሬታዎች ካሉት ቅሬታዎቹን በወረዳ፣ በክፍለ ከተማና በማዕከል ደረጃ በማቅረብ ምላሽ ማግኘት የሚያስችለው የቅሬታ አቀራረብና አፈታት ሥርዓትንም አካትቷል።

በመሆኑም ቢሮው ወደ ተግባር ያሸጋገረው ‹‹በመንደር የንግድ ቁጥጥርና ክትትል አሠራር ሥርዓት መመሪያ 159/2016›› ያስቀመጣቸውን ዓላማዎች ለማሳካትም የንግዱ ማህበረሰብ በአንድ በኩል የንግድ ተግባሩን በተረጋጋ መንፈስ ለማከናወን በሌላም በኩል በመመሪያውና በሌሎች የንግድ ሕጎች የተቀመጡ ግዴታዎቹን በአግባቡ መወጣት እንዲችል እንዲሁም መብቶቹ ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ለማስቻል በመመሪያው ላይ የተሟላ ግንዛቤ ሊጨብጥ ይገባል።

መመሪያው ዋና ዋና ጉዳዮችንም ያካተተ ነው፤ የፀና የንግድ ፍቃድ ስለመኖሩ፣ የዋጋ ዝርዝር ስለመለጠፉ እና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ 25 ያህል ጉዳዮች/ ኤሌመንቶች/ የተካተቱበት መሆኑ በመግለጫው ተጠቁሟል። ተግባራዊነቱም ላይ ስምሪት የሚሰጠው በየመንደሩ በብሎክ አደረጃጀት ባለሙያ ተመድቦ ሲሆን፣ ሌላው መንገድ ደግሞ ማንኛውም ጥቆማ በሚሰጥበት ሂደት ተግባራዊ የሚሆንበት አሠራርም አለው።

በንግድ ስራ የተሰማሩ ክፍሎች የጸና ንግድ ስራ ፈቃድ ያላቸው ስለመሆናቸው ሸማቹ እንዲመለከት ለማድረግ የንግድ ፈቃዱን በግልጽ በሚታይ ቦታ ማስቀመጥ፣ የእቃዎች ዋጋ ዝርዝር መለጠፍ፣ ሸማቾች ለሚገዙት ዕቃ ደረሰኝ መስጠት በመንደር ቁጥጥር ሂደቱ ትኩረት እንደሚደረግባቸው ምክትል የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሪት ቅድስት አስገንዝበዋል።

የመመሪያው ክፍል ሦስት በመንደር የንግድ ቁጥጥርና ክትትል አሠራር ሥርዓት የቢሮ አደረጃጀቶች እና የቁጥጥር ባለሙያዎች ተግባር እና ኃላፊነትም እንዲሁ ይዳሰሳል። የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የተሰጠው ስልጣን እንዳለ ሆኖ፣ ክፍለ ከተማ እና ወረዳዎችም በተመሳሳይ የሚሠሯቸው ሥራዎች እንዳሉም ተመልክቷል::

የመመሪያው ክፍል አራት ደግሞ በንግድ ድርጅቶች ላይ ጥፋት ወይም ጉድለት ሲገኝ የሚወሰዱ እርምጃዎችን አመላክቷል። መመሪያውን ከሌሎች ቀደም ሲል ከነበሩ መመሪያዎች የሚለየው የቀድሞዎቹ መመሪያዎች ወረዳ ላይ ያሉ ባለሙያዎች በሁሉም ጉብኝቶች ላይ እርምጃ የሚወስዱበት የአሠራር ሥርዓት የነበራቸው መሆኑን ምክትል የቢሮ ኃላፊዋ አስታውሰዋል።

አሁን ግን በየጊዜው የሚመጡ ጥቆማዎችን በመመሪያው አስፈላጊነት ላይ ባሉ ጉዳዮች ላይ መሠረት በማድረግ በዋናነት የፀና የንግድ ፍቃድ በሌለው ነጋዴ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚያስወስድ ገልጸዋል። በተመሳሳይ ደግሞ ሕጋዊ እርምጃ የሚያስወስድ ተግባር መሆኑን አስረድተዋል። የፀና የንግድ ፍቃድ የሌለው ሲባል በበጀት ዓመቱ ሙሉ በሙሉ የንግድ ፍቃድ የሌለው ወይንም ደግሞ ማደስ እየተገባው ያላደሰ፣ በሥራ ላይ ሆኖ የታገደ ሆኖ የሚሠራ ሲያገኙ ለወረዳው የቅርብ ኃላፊ አሳውቆ እርምጃ ይወስዳል። በማስጠንቀቂያም እስከማሸግ ድረስ እርምጃ ይወስዳል። የደረሰበትን እርምጃ ደግሞ ለሚመለከተው የሚያሳውቅበት ሂደት ያለው መሆኑን ያስረዳሉ።

ተቆጣጣሪው ከዚያ ውጪ ያሉ ጥፋቶች ሲኖሩ ደግሞ ደረጃ በደረጃ ቁጥጥር ያደርጋል፤ ያገኘውን ግኝት ደግሞ ቅፅ 01 በሚባለው ላይ ያሰፍራል። ያሰፈረውን እና ሪፖርት ደግሞ ለጽህፈት ቤት ኃላፊው ያቀርባል። የውሳኔ ሃሳቡን ጨምሮ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በማስፈፀም ረገድ ደግሞ ስልጣኑ የተገደበበት ሂደት የለም። የተለያዩ የስነምግባር ችግር ያለባቸው ጥቂት አጥፊ ተቆጣጣሪዎችን ለማረም ግልፅ አሠራር ለማስፈን እና ወረዳ ከወረዳ ወጥ አሠራር በማስፈለጉ ጭምር መመሪያው ማስፈለጉን አመላክተዋል።

ነጋዴውም በተለያየ መንገድ ቅሬታውን ማቅረብ የሚችልበት አሠራር በመመሪያው መቀመጡን ጠቅሰዋል:: ነጋዴው ውሳኔ ከተላለፈበት በኋላ ቅሬታ ካለው በአስር ቀን ቅሬታ ማቅረብ የሚችልበት እና በአምስት ቀን ምላሽ የሚያገኝባቸው መብቶች አብረው በመመሪያ ላይ ተቀምጠዋል። መመሪያው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ሕጋዊ አሠራሩን ጠብቆ ማሻሻያዎች ሊደረጉበት እንደሚችሉም ምክትል የቢሮ ኃላፊዋ አመላክተዋል ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ መመሪያው ሲወጣም በየደረጃው ያለውን አካል ሃሳብ ለማካተት ተሞክሯል። መመሪያው ቢሮው ከተዘጋጀ በኋላ ሕጋዊ ሂደቱን ጠብቆ በፍትህ ሚኒስቴር እንደሚዘገብ ተደርጓል፤ በመመሪያው ላይም እስከታች ያለውን ባለሙያ የማስገንዘብ ሥራም ተሠርቷል። አሁን ደግሞ መደበኛ በሆነ ሁኔታ በክፍለ ከተማ ስልጠና ጭምር በመስጠት ወደ ሙሉ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ነው።

በቢሮው የሕግ አገልግሎት ኃላፊ አቶ መለሰ ተገኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ በንግድ ሥራው ላይ ቁጥጥር ሲደረግ የቆየ ቢሆንም፣ በሂደት የታዩ ስህተቶችን ማረም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፤ ቢሮው አዲሱን መመሪያ አዘጋጅቶ በፍትህ ሚኒስቴር ክትትል እና ድጋፍ ለትግበራ ዝግጁ ማድረጉን አስረድተዋል።

አዲሱ መመሪያ በዋነኛነት ያስፈለገበት ምክንያትም በመጀመሪያ ደረጃ ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ነው ያሉት አቶ መለሰ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ነጋዴውም መብቱንና ግዴታውን አውቆ በተረጋጋ ሁኔታ ሥራውን እንዲቀጥል ለማድረግ ነው ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አቤቱታ እና ቅሬታ በሚኖርበት ጊዜ ቅሬታውን በማቅረብ ነጋዴው ሥራውን በአግባቡ የሚሠራበት ሁኔታ የተመላከተበት መሆኑን አስታውቀዋል።

መመሪያውን በማውጣት ሂደት በተለያዩ ጊዜያት የወጡ የንግድ ፈቃድ እና መመሪያ አዋጆችን፣ ደንብና መመሪያዎችን ለመመልከት መሞከሩ ተጠቁሟል። በእነዚህ አዋጆችና መመሪያዎች የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ የተሰጠው ስልጣን እና ተግባር ምን እንደሆነ ማየት ያስፈለገ በመሆኑም እነዚህን አካትቶ ግልፅ አሠራር በዝርዝር የተቀመጠበት አዲስ መመሪያ መውጣቱን አመልክተዋል። መመሪያው ወቅቱን የጠበቀና ትክክለኛ መመሪያ መሆኑን ኃላፊው ገልጸው፤ የንግዱ ማህበረሰብ መመሪያውን መሠረት በማድረግ እንዲሠራ፣ አስፈጻሚ አካላትም ተገቢው ገንዛቤ ኖራቸው ሥራውን በአግባቡ እንዲመሩ ማድረግ ላይ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአዲሱ መመሪያ በቢሮ ደረጃ የሚሰሩ ሥራዎች፤ በወረዳ እና በክፍለ ከተማ ያሉ የንግድ ጽህፈት ቤቶች ምን ይሠራሉ የሚለው በግልፅ ተቀምጧል። የወረዳ የቁጥጥር ሰዎች ለክትትል እና ቁጥጥር ባለሙያዎች ክትትል የሚደረግባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ በመመሪያው ከተራ ቁጥር አንድ እስከ 25 የተቀመጡ ተግባራትን ያከናውናሉ።

የቁጥጥርና ክትትል ባለሙያዎች ቀደም ሲል ለሥራ ሲወጡ የስምሪት አሠራር አልነበራቸውም ሲሉም አቶ መለሰ ጠቅሰው፤ አሁን ግን ለሥራ ከመውጣታቸው በፊት ከኃላፊያቸው ጋር ተነጋግረው ምን ሥራ፣ የት እና መቼ እንደሚሠሩ አውቀው ቢያንስ ሁለት ወይም ሦስት ባለሙያዎች አብረው እንዲወጡ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ባለሙያዎቹ የሚሄዱበት ቦታ፣ ሙሉ ስማቸው፣ የሚሄዱበት ቀን እና ሰዓት ይመዘገባል ያሉት ኃላፊው፤ ሥራቸውን አጠናቀው ሲመለሱም የሠሩትን ሥራ ለቅርብ ኃላፊያቸው የሚያስረክቡበት አሠራር ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

በኃይሉ አበራ

 አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You