አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባሩ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ይወጣ!

በ2017 ዓ.ም በሀገራችን እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየትን ራዕዩ አድርጎ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በታሪክ ሂደት የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በማያዳግም መልኩ እልባት ለመስጠት ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል::

ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ወደ ጎን በማድረግ በሰላማዊ አማራጭ ብቻ ሀገራቸውን እንዲያሸጋግሩ ጥሪ በማድረግ ላይ ይገኛል:: በሁለት ዓመት ተኩል ቆይታውም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ልምዶችን ከመቀመር ባሻገር የታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ በመውረድ ስለምክክር አስፈላጊነት ሰፋ ያሉ ግንዛቤዎችን ሲፈጥር ቆይቷል::

ከዚሁ ጎን ለጎንም በአስር ክልሎች የተሳታፊና የተባባሪ አካላት ምርጫ አካሂዷል፤ ሥልጠናም ሰጥቷል:: እነዚህ ሥራዎች በተጠናቀቁባቸው ክልሎች ደግሞ አጀንዳ የመቅረጽ እና በተቀረጹት አጀንዳዎች ላይም ምክክር አድርጎ የመቋጨት ሥራ ይሠራል::

ከግንቦት 21 ጀምሮ እስከ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናትም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር ያከናውናል:: የምክክር አጀንዳዎችን ማሰባሰብ፣ ልየታ እና ቀረጻ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው:: ይህ ሂደት ደግሞ በርካታ ልምዶች የሚቀመሩበት ለሰላምና እርቅ የተመረጠው ዘዴ ትክክል መሆን አለመሆኑ የሚታይበትና የሚቃኝበት ነው::

በኢትዮጵያ በሂደት ላይ ያለው ምክክር አጀንዳዎቹ አስቀድመው የተወሰኑ ባይሆኑም መርሆዎች ግን ተቀምጠውለታል:: ምክክር እንዲካሄድባቸው የሚቀረጹ አጀንዳዎች እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው፣ የአለመግባባት መንስዔዎችን በትክክል በሚዲስሱ አጀንዳዎች ላይ የሚያተኩሩ እና ጥልቀትና አግባብነት ያላቸው መሆን እንዳለባቸው መርሆዎች መቀመጣቸውን የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሲገልጽ ቆይቷል:: በአዲስ አበባም የሚካሄደው አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሂደት በተቀመጡለት መርሆዎች መሠረት እንደሚከናወንም ተጠቁሟል::

አዲስ አበባ አንጻራዊ ሰላም ያለባትና ለብሔራዊ ምክክርም የተሻለ መደላድል የተፈጠረባት ከተማ በመሆኗ የአጀንዳ ማሰባሰቡ ተግባር የተሳካ እንደሚሆን ይጠበቃል:: በከተማዋ ሃሳብ አለኝ የሚል የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ሃሳባቸውን ያለምን ገደብ የሚሰጡበትና በመደማመጥ ጉዳዮች እልባት የሚያገኙበት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል::

ይህን መነሻ በማድረግም ወደሌሎች ክልልች ተሞክሮውን የማስፋት ሥራም በቀጣይነት የሚከናወን ይሆናል:: በቀጣይም የምክከሩን አጀንዳዎችን ከኅብረተሰቡ የመቀበልና ምክክሩን ወደ መሬት የማውረድ ሥራዎች ይከናወናሉ፡ በአጠቃላይ ከአዲስ አበባ የሚገኘው ልምድ በቀጣይ ለሚካሄዱ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎች እርሾ ሆኖ ያገለግላል::

በተለይም ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ከአዲስ አበባ ልምድ በመቅሰም በተቻለ ፍጥነት ወደ አጀንዳ ማሰባሰቡ ሥራ ሊገቡ ይገባል:: የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችም ቢሆኑ ከሞላ ጎደል መንግሥትም ጣልቃ ገብቶ በአካባቢው ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ችግሩን እንፈታለን ብለው የተነሱትም ኃይሎችም ችግራቸውን በውይይት ለመፍታት መሞከር አለባቸው::

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ግጭት፤ ጦርነትና መወነጃጀል ሳይሆን ውይይትና ምክክር ብቻ ነው:: ስለዚህም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደሀገር ከማዳበር ውጪ ፍላጎትን በኃይል መጫን ጊዜ ያለፈበት ተግባር ነው:: ስለዚህም ግጭትንና ጦርነትን እንደ ችገር መፍቻ የወሰዱ አካላት የሕዝባቸውንና ሀገራቸውን መጻኢ ጊዜ ማሳመር ከፈለጉ የተፈጠረውን የምክክር ዕድል ሊጠቀሙበት ይገባል::

በምክክር የመግባባት ሂደት በየምዕራፉ መመካከርንና መግባባትን ይጠይቃል:: በዚሁም መሠረት ምክክር በሚካሄድባቸው አጀንዳዎች ላይ መመካከሩና መግባባት ላይ መድረሱ አስፈላጊ ነው:: ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ አጀንዳዎችን ከምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎች፣ ከተለያዩ ጥናቶች፣ ግለሰቦች ወይም ተቋማት ከሚሰጧቸው የአጀንዳ ሃሳቦች በማሰባሰብ የመለየት፣ የመቅረጽ እንዲሁም ቅደም ተከተል በማስያዝ ምክክር እንዲደረግባቸው ያደርጋል::

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የምክክር ኮሚሽኑ በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ ውጤት እያስመዘገበ ነው:: በሂደቱም ወሳኝ የሚባለውን የአጀንዳ ማሰባበሰብ ሥራ ለማከናወን ዝግጅቱን አጠናቋል::

ስለዚህም ነገ በአዲስ አበባ የሚጀመረው አጀንዳ የማሰባሰቡ ሥራ ውጤታማ እንዲሆንና የተሻለ ተሞክሮ ሆኖ ወደ ሌሎች ክልሎችም እንዲሸጋገር የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ኃላፊነታቸውን በሚገባ ሊወጡ ይገባል::

አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You