
ዜና ሐተታ
በየዓመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ይወጣሉ። እነዚህ ወጣቶች የመጀመሪያ ፍላጎታቸው በተማሩበት የትምህርት መስክ ወደ ሥራው ዓለም መቀላቀል ቢሆንም ለበርካቶች ይህ ዓላማ በነበር ብቻ ሲቀር ይስተዋላል። አንዳንዶች የእራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ገንዘብ ማግኘት ሲጀምሩ ሌሎች ግን በሥራ ጠባቂነት ብቻ ጊዜያቸውን ያባክናሉ።
በዚህ የተነሳ መንግሥት ለሁሉም ወጣት የሥራ እድል ማቅረብ ስለማልችል ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ ቢሆኑ እመክራለሁ ሲል ይደመጣል። ለመሆኑ የመንግሥት የሥራ እድል ሳይጠብቁ በራሳቸው ተፍጨርጭረው ሥራ ለመጀመር የሚሞክሩ ወጣቶች የሚያልፉበት መንገድ ምን ይመስላል ? በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመለከተው የመንግሥት አካልስ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታት ምን እየሠራ ይገኛል?
ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሃሳቡን የሰጠው ወጣት ሰሚር አብደላ፤ በአካውንቲግና ፋይናንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ቢኖረውም ሥራ ማግኘት ሳይችል ከአንድ ዓመት በላይት ቤት ውስጥ ማሳለፉን ይገልጻል።
የሥራ አጥ መታወቂያ እሱ ከሚኖርበት ወረዳ አውጥቶ ቢደራጅም ምንም አይነት ድጋፍ ባለማግኘቱ ምክንያት ከቤተሰብ ብር ተበድሮ አነስ ያለች ቁርስ ቤት ለመክፈት ቢሞክርም እሱ ባለው የገንዘብ አቅም የሚከራይ የንግድ ቤት ማጣቱን ያስታውሳል። ኪራያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ቦታዎች ከፍተኛ ብር ለቁልፍ ሽያጭ እየተባለ የሚጠየቅባቸው መሆኑንም ያነሳል።
በዚህ ሳቢያም ተንቀሳቃሽ ቤት በመሥራት በጎዳናዎች ቀለል ያሉ ምግቦችን እየሠራ ለመሸጥ ቢሞክርም የተለያዩ መጉላላቶች ያጋጠሙት በመሆኑ ሥራውን ማቆሙን ያስረዳል።
ወጣት ሰሚር ወጣቶች የሥራ እድል ፍጠሩ ሲባል በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰማ ቢሆንም ብድርና ቦታ ማግኘት ቀላል አይደለም ይላል።
ሌላኛው ስሙን መግለጽ ያልፈለገ የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣት እንደገለጸው የሜካኒካል ኢንጂነሪግ ተመራቂ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲ ባገኘው ትምህርት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በግብርና ዘርፉ ያሉ ችግሮች ሊያቃልል የሚችል ማሽን መሥራት ችለዋል።
የሠሩንት ማሽን ወደ ገበሬው በመውሰድ ባደረጉት ምልከታ ከፍተኛ ይሁንታ ያገኘ ቢሆንም ማሽኑን አባዝቶ ተደራሽ ለማድረግ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠማቸው ይናገራል። ለዚህም የተለያዩ የመንግሥት እንዲሁም የግል ተቋማት ቢሮችን ቢያንኳኩም የብድርም ሆነ የድጋፍ መልስ እንዳልተሰጣቸው ይናገራል።
ወጣቱ አዲስ የሥራ ሃሳብ ያላቸው በርካታ ወጣቶች ይኖራሉ ነገር ግን ወጣቱን ሥራ ፍጠር ከማለት በስተቀር ወጣቱን ወደ ሥራ መፍጠር የሚገፋፋው ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረም ሲል ሃሳቡን ይገልጻል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ደርጅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ከሚፈጥረው የሥራ እድል በተጨማሪ በራሳቸው ሥራ ለመፍጠር የሚሞክሩ ወጣቶችን በማበረታት ረገድ ምን እየሠራ ይገኛል ሲል ጥያቄውን አንስቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪት ዳይሬክተር ሰብሀዲን ሱልጣን እንደገለጹት ፤መንግሥት ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሠራም በራሳቸው ስራ ለመፍጠር የሚሞክሩ ወጣቶችን ለማበረታት ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየሠራ ይገኛል ይላሉ።
አቶ ሰብሀዲን ወጣቶች በመጀመሪያ የሚያነሱት የብድር አቅርቦት እጥረት ለመፍታት አዲስ ካፒታል እንዲሁም አዲስ ብድርና ቁጠባ ከተባሉ ተቋማት ጋር የትምህርት ማስረጃን እንዲሁም ጨረታ ዋስትናን እንደማስያዣ እየተጠቀሙ ብድር እንዲሰጡ ከስምምነት በመድረስ ወደ ሥራ መገባቱን ይገልጻል።
ነገር ግን ወጣቱ መስራት የሚፈልገውና የሚጠይቀው የገንዘብ አቅም የማይመጣጠንበት ሁኔታ መኖሩን አንስተው፤ ቦታን በተመለከተ ለተወሰኑ ለሚደራጁ አካላት የሚሰጥ ቢሆንም ለሁሉም መሥሪያ ቦታና ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል አቅም የለም ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም