መንግሥት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን ቀርጾ ተግባራዊ አድርጓል። ከእነዚህ መርሃ ግብሮች መካከልም በተለይም በገጠር የሚኖሩ እና የኢኮኖሚ መሠረታቸው ግብርና የሆነ እናቶች ከተረጂነት ማላቀቅ የሚያስችሉ የግብርና ልማት ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ይህ መርሃ ግብር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ይሁን እንጂ ከፍተኛው የሕዝብ ቁጥር የያዙ ግን ደግሞ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ላልነበሩ ሴቶች የላቀ ትኩረት ይሰጣል። በገጠር የሚኖሩ እናቶች ልክ እንደ ወንዱ ሁሉ አምርተው የራሳቸውን ገቢ የሚያመነጩበትና ቤተሰባቸውን የሚደጉሙበትንም መንገድ ይቀይሳል።
ይህንን የልማት መርሃ ግብር ተግባራዊ ካደረጉ ክልሎች መካከል ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተጠቃሽ ነው። የክልሉ መንግሥት አርሶ አደሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብሎ እየተገበራቸው ካሉ የልማት መርሃ ግብሮች መካከልም የሌማት ቱሩፋት እና የ30-40-30 የአትክልትና ፍራፍሬ ኢኒሼቲቭ ዋነኞቹ ናቸው።
እነዚህ የግብርና መርሃ ግብሮች ምርታማነትን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያመጡ ከመሆናቸውም ባሻገር ሁሉም የአርሶ አደር ቤተሰብ የምግብ ዋስትናውን የሚያረጋግጥበት፣ የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኝበት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው ናቸው።
በዚህ ረገድ የክልሉ መንግሥት በተለይ ሴቶች በምግብ እጥረቱም ሆነ በኢኮኖሚው ዋነኞቹ ተጎጂዎች መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሴቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል። በዚህም በርካታ እናቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆንና ኑሯቸውን ማሻሻል የቻሉ ሲሆን ራሳቸውም ሆነ ልጆቻቸውን በምግብ እጥረት ይደርስ የነበረውን ጉዳት ለመታደግ እንዳገዛቸው ነው ከክልሉ ያገኘነው መረጃ የሚያመላክተው።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድንም ይህንኑ የግብርና ልማት መርሃ ግብሩ ተግባራዊ ከሆኑባቸው የክልሉ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ከንባታ ዞን በቅርቡ የመስክ ጉብኝት አድርጓል። በዞኑ በግብርና ሥራ ከፍተኛ ውጤት ካመጡ እና ለሌሎችም ጭምር አብነት ተደርገው ከሚጠቀሱት ወይዘሮ አማረች ወልደሃዋሪያት ቤት ጎራ ብሎ ነበር። አርሶ አደሯ ልክ እንደወትሮ ሁሉ ማልደው ተነስተው ሥራ ላይ ተጠምደው ነው ያገኘናቸው።
የብርታት ተምሳሌት እንደሆኑ የሚጠቀሱት አርሶ አደር አማረች ፈጣሪንም ሆነ ሰውን ሁሉ ማመስገን ይቀናቸዋል፡ ‹‹ስናመሰግን ይጨመራል›› የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ዘልቆ የገባቸው እኚህ እናት ይህንን ቃል ዘወትር እንደሚናገሩት ሁሉ በሕይወታቸውም የሆነው ይኸው ነው። ልጆቻቸውን ለማሳደግም ሆነ ያለ አጋዥ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ሲሉ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል። ሆኖም ምሬትም ሆነ ተስፋ መቁረጥ አያውቃቸውም። ተወልደው፣ ተድረው፣ ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ሀብት ያፈሩባት ከንባታ ዞን ቀዲዳ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው ዛቶ ሾደራ ቀበሌ ነዋሪም ‹‹የሴት ወንድ›› ሲል ያሞካሻቸዋል፤ ጥንካሬያቸውን ይገልፃል። በችግር እና በትዳር አጋራቸው ጫና ቤት ለቀሩ በርካታ የመንደራቸው ሴቶችም እንደተምሳሌት ተደርገው ነው የሚወሰዱት፤ ገበሬዋ አማረች ወልደሐዋሪያት።
‹‹ባለቤቴ ጥሎኝ ሲሄድ ቤቴ ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ አልነበረም፤ ልጆቼን የማሳድግበት አንዳችም ቅሪት አልነበረኝም›› በማለት የኋላ የችግራቸውን ዘመን ያስታውሳሉ። ለልጆቻቸው የእለት ጉርስ ለማግኘት ከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ ገብተው የብዙዎችን ፊት ለማየት ተገደው እንደነበር ያነሳሉ። ይህንን የወይዘሮ አማረች እና ቤተሰቦቻቸው ጭንቀት የተመለከቱ አጎታቸው አንዲት የሃበሻ ጊደር በቅናሽ ዋጋ ይሸጡላቸዋል። ‹‹ያቺን ከዶሮ ትንሽ ከፍ የምትለውን ግልገል 160 ብር በሁለት ክፍያ እንድወስዳት አጎቴ ቢሰጠኝም በወቅቱ ግን ምንም ገንዘብ ስላልነበረኝ ተጨንቄ ነበር ፤ ሆኖም እግዚአብሔርን ተማምኜ በድፍረት ወሰድኳት›› ይላሉ።
በብድር የወሰዷትን ጊደር እዳ ለመክፈል ሲሉ በጓሯቸው የተከሉትን አቦካዶና ሌሎች ፍራፍሬዎችን ቀን ከሌሊት ተንከባከቡ፤ ያመኑት ፈጣሪያቸውም አላሳፈራቸውም፤ ልፋታቸውን አይቶ ፍሬያማ አደረጋቸው፤ ከአንዱ አባካዶ አንድ ቅርንጫፍ ብቻ 100 ኪሎ አባካዶ ለቀመው ሸጡ። አባካዶው ተሸጦ ካገኙት 500 ብር ከፊሉን ለአጎታቸው ሰጡ። ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ውስጥም ብድራቸውን አጠናቀው መክፈላቸውን ይናገራሉ። በተጓዳኝም ባላቸው አነስተኛ መሬት ላይ በግብርና ባለሙያዎች እየታገዙ የአትክልትና ፍራፍሬና ቡና እና እንሰት ልማታቸውን አስፋፉ።
‹‹ሴት ነኝ ብዬ ቤት ቁጭ አላልኩም፤ የሰው እጅ መጠበቅም ህሊናዬ የሚቀበለው ባለመሆኑ የቤተሰቤን ሕይወት ለመታደግ ስል ቀን ከሌሊት ተግቻለሁ፤ ፈጣሪዬም ልፋቴን አይቶ አላሳፈረኝም›› የሚሉት ወይዘሮ አማረች ከመጀመሪያ ልጃቸው ጋር በመተባበር የከብቶቻቸውን መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ ስድስት አደረሱ። ወተትም ሆነ የወተት ተዋፅኦዎችን ከራሳቸው አልፈው ለአካባቢው ማህበረሰብ በመሸጥ የገቢ አቅማቸውንም አሳደጉ። ልጆቻቸውም የተመጣጠነ ምግብ ከማግኘት አልፈው ወደ ትምህርት ቤት ላኩ፤ የሳር ጎጆቻቸውን ወደ ቆርቆሮ ቀየሩ።
ወይዘሮ አማረች ከራሳቸው አልፈው ለጎረቤቶቻቸውን እንደ እሳቸው ያለ አጋዥ ልጆች የሚያሳድጉና ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ እናቶች ተሞክሮ በማካፈልና እገዛ በማድረግም በመንደራቸው ይታወቃሉ። ‹‹እኔ ብቻዬን ብለወጥ ትርጉም የለውም፤ ሀገርም አታድግም፤ በተለይ እንደእኔ ብቸኛ የሆኑ እናቶች ከተረጂነት ወጥተው ራሳቸውንና ገቢያቸውን ማሳደግ አለባቸው ብዬ ስለማምን በቻልኩት አቅም ሁሉ እገዛ አደርግላቸዋለሁ፤ ከእኔ ልምድ በመነሳት ምርታማ የሚያደርጋቸውን አሠራር አሳያቸዋለሁ ፤ እመክራቸዋለሁ›› ሲሉም ይናገራሉ።
ይህ ታታሪነታቸው እና ሥራ ወዳድነታቸው በብዙዎች ዘንድ ምስጉን አድርጓቸዋል፤ የግብርና ባለሙያዎችም ሆነ የቀበሌው አመራሮች ዘወትር ከጎናቸው እንዳይለዩ ምክንያት ሆኗቸዋል። ርዳታ በሻቱ ጊዜ ሁሉ ቀን ከሌሊት ሳይሉ ለብርቷ ሴት አርሶ አደር ጥሪ ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ።
‹‹በፊት ለልጆቼ እንኳን የማይበቃው ወተት የተሻሻሉ ዝርያ ካላቸው ላሞች ጋር በማዳቀሌ አሁን በቀን ሶስት ጊዜ በማለብ ከአንድ ላም ብቻ 36 ሊትር ወተት አገኛለሁ፤ ይህንንም በመሸጥ ገቢዬን አሳድጊያለሁ›› የሚሉት አርሶ አደር አማረች የሚሰጣቸውን የባለሙያ ምክር ሳያቅማሙ ይተግብራሉ፤ በተለይ የእንስሳት ምገባ ሥርዓታቸውን በማዘመናቸው ምርታማ ለመሆን መብቃታቸውን ያስረዳሉ። ለመኖ የሚሆን የሳር ዝርያ በስፋት በመትከልና ሞላሰስን ሊተካ የሚችለውን ሸንኮራ አገዳም በማሳደግ ለከብቶቻቸው አስተማማኝ የመኖ አቅርቦት ማግኘታቸውን ያብራራሉ።
በአሁኑ ወቅት የሚያመርቱትን ወተት ከልጆቻቸው ጋር በከተማ በሚገኙ ሻይ ቤቶች እንደሚያከፋፍሉ የሚናገሩት አርሶ አደሯ ወይዘሮ፤ አንዳንድ ማህበራት ቤት ድረስ መጥተው እንደሚወስዱላቸው ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት በትራንስፖርት የሚያደርሱ መሆኑን ይገልፃል። ይህም በልፋታቸው ልክ እንዳይጠቀሙና ምርቱም እየባከነባቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
አርሷ አደሯ እናት የከብቶቻቸውን መጠንም ሆነ የወተት ልማታቸውን የማስፋፋት እቅድ ቢኖራውም ቋሚ የሆነ የገበያ ትስስር ያልተፈጠረላቸው በመሆኑ ‹‹ልከስር እችላለሁ›› የሚል ስጋት እንዳላቸው ያመለክታሉ። በመሆኑም የሚመለከተው አካል ለእሳቸውም ሆነ እንደእሳቸው በወተት ሀብት ልማት ለተሰማሩ ሴቶች ቋሚ የሆነ የገበያ ትስስር እንዲፈጥርላቸው ይጠይቃሉ። ‹‹በተለይም ደግሞ በአቅራቢያችን የወተት ማቀነባበሪያ ቢከፈትና ሁላችንም ያለ ስጋት የወተት ምርታችንን የምናንቀርብበት እድል ቢመቻች የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን፤ ሀገርንም እንጠቅማለን›› ሲሉ ይጠቁማሉ።
‹‹በቀጣይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን፤ አሁን ያለንን የወተት ሀብት ልማት ስፍራ የማስፋፋት፤ የአትክልትና ፍራፍሬ እርሻዬን ከፍ የማድረግ እቅድ አለኝ›› የሚሉት ወይዘሮ አማረች፤ በተለይም ስድስት ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን የተሻለ ደረጃ የማድረስ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንዲያስችላቸው አዋጭ የሆኑ የግብርና ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት። እቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ያላቸው ቦታ በቂ አለመሆኑን ገልፀው ፤ የቀበሌው አስተዳደር ጥረታቸውንና የወደፊት ህልማቸውን አይቶ የማስፋፊያ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
እንደ ወይዘሮ አማረች ያሉ ልበ ፅኑ ሴት አርሶ አደሮችን ለማብዛት እና ብሎም ያሉባቸውን ተግዳሮቶች መፍታት በተለይም በዘርፉ ያሉ ተቋማት ሊረባረቡ እንደሚገባ ዝግጅት ክፍሉም ያምናል። በዋናነትም ተቋማቱ ሴቶች ተጠቃሚነት እና ተሳታፊነት ላይ ከእቅድ ባለፈ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዋናነትም በገጠሩ ያሉ ሴቶች ቁጥር ከፍ ያለ እንደመሆኑ ሴቶች በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን አቅም በማሳደግ የግብርና ምርትማነትን ማጎልበት ይገባል። ይህም ሲሆን ነው የምግብ ዋስትናቸውን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ የሚቻለው።
በርግጥ መንግሥት የሴት አርሶ አደሮችን የግብርና አቅም በማሳደግ በኩል በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑ እሙን ነው። በተለይም ደግሞ ገበያ ተኮር የሆኑ ምርቶችን እንዲያመርቱ በማድረግ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል። በተለይም ሴቶችን መሠረት ያደረጉ መሠረተ ልማቶች በገጠሩ አካባቢ መስፋፋት የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማስፋት አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
በተመሳሳይም አርብቶ አደሩ አካባቢ ያሉ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እነሱን መሠረት ያደረጉ የልማት ሥራዎች መስፋፋት ይኖርባቸዋል። ይህም አርብቶ አደር ሴቶች ወደ ግብርና ሥራ እንዲገቡ ያግዛቸዋል። ሴቶች ለጠንካራ ኢኮኖሚ መሠረት ናቸው። አቅማቸውን በሁሉም መስክ በማሳደግ የተለያዩ ችግሮችን ማስወገድ ይገባል። በተለይም መንግሥት የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነት በእጥፍ ለማሳደግ ለያዘው የልማት ግብ ስኬትና ውጤታማነት በገጠር ያሉ ሴቶችን አቅም መጠቀም ወሳኝ ነው። ለዚህም ደግሞ እንቅፋት የሆኑ የመሠረተ ልማት ችግሮችን በመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል የሚለው የዛሬ የዝግጅት ክፍሉ መልዕክት ነው።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም