ተፈጥሮን መጠበቅና መንከባከብ ለሰው ልጅ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን አማራጭ የሌለው እውነት ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅ ተፈጥሮን በጠበቀና በተንከባከበበት ልክ፤ ተፈጥሮም ለሰው ልጅ የሚሰጠው ጸጋ እጅጉን ከፍ ያለ ነው። ካልሆነም ውጤቱ በተቃራኒው የሚገለጽ ነው። ለዚህ ዋና ማሳያው ደግሞ ዛሬ ላይ ዓለምን በእጅጉ አስጨንቆ የያዛት የአየር ንብረት ጉዳይ ነው።
ይሄ የሰው ልጅ የሥራ ውጤት የሆነው ችግር ታዲያ መልሶ የሰው ልጅን አንዴ በድርቅ፣ ሌላ ጊዜ በጎርፍ፣ ሲሻውም በወጀብ እያጎሳቆለው ይገኛል። እናም ይሄንን የተገነዘቡ ብልህ ሕዝቦችና መንግሥታት ታዲያ፤ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ሥራን ወደማከናወን ገብተዋል። በኢትዮጵያ ይሄው የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችለው ተግባር እየተከናወነ ሲሆን፤ በተለይም ላለፉት አምስት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የተከናወኑ የችግኝ ተከላ ተግባራት እጅጉን ጠቃሚ ውጤት የታየባቸው ናቸው።
የዚህ ቅዱስ ተግባር ዘንድሮም ለስድስተኛ ተከታታይ ዓመት መሰል ተግባር የሚከናወን ሲሆን፤ በዚህ ክረምት ለሚካሄደው የሁለተኛው ምዕራፍ ሁለተኛ ዙር የችግኝ ተከላ ተግባር የሚውል ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል። የእነዚህ ችግኞች ዝግጅትም ከ115 ሺህ በላይ በሆኑ የችግኝ ጣቢያዎች የተከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም የመንግሥት የችግኝ ጣቢያዎች፣ የግለሰብ የችግኝ ሥፍራዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚያዘጋጇቸው እንዲሁም በሌሎች በግሉ እና በመንግሥት ባለቤትነት ተይዘው የሚካሄዱ የፕሮጀክት ችግኝ ጣቢያዎች ተጠቃሽ ናቸው።
ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ በሀገር ደረጃ ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት ተለይቷል። ከዚህ ውስጥም ለ700 ሺህ ሄክታሩ ካርታ የማዘጋጀት (የጂኦ ሪፈረንሲንግ) ሥራ ለማከናወን ታቅዶ በስፋት ሲሠራ ቆይቷል። ይሄ መከናወኑ ደግሞ ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው ነው። ምክንያቱም ችግኝ የተተከለባቸው ስፍራዎች ካርታ ተዘጋጀላቸው ማለት የተተከሉት ችግኞች የትና በምን ሁኔታ እንዳሉ ለመለየት የሚያስችል ብቻ ሳይሆን፤ የሚከናወነው ተግባርም ዓለም አቀፍ ቅቡልነትና እውቅና እንዲኖረውም የሚያስችል ማስረጃና መረጃ ለማቅረብ የሚያስችል ነው።
ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት በተካሄዱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ከ31 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ችግኞቹን ተንከባክቦ የማጽደቅ ምጣኔውም ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ የመጣ ሲሆን፤ ለአብነትም በ2015 ዓ.ም ክረምት ላይ የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት ምጣኔ ከ90 በመቶ ከፍ ያለ ነበር። ይሄ መሆኑ ደግሞ አንድም በመንግሥት የተሰጠው ትኩረት ሲሆን፤ በዋናነት ግን ኅብረተሰቡ ከችግኞቹ የሚያገኛቸውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች በመገንዘብ የራሱ አድርጎ መጠበቅና መንከባከብ በመቻሉ ነው።
ምክንያቱም፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩ፣ ከአካባቢ ጥበቃ እና ተያያዥ ፋይዳዎቹ ባሻገር፤ ከፍ ያለ የሥራ እድል ፈጠራን ማዕከል አድርጎ እየተከናወነ ያለ ነው። በዚህም ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተለይም ሴቶች የሥራ እድል ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን፤ በዚህ ዓመትም በተመሳሳይ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ተሰጥቶታል። ለምሳሌ፣ ችግኝ በተዘጋጀባቸው ከ115 ሺህ በላይ ጣቢያዎች በእያንዳንዳቸው ከ10 እስከ 500 ለሚሆኑ ዜጎች (ትንንሾቹ እስከ 10፣ ትልልቆቹ ደግሞ እስከ 500 ሰው) የሥራ ዕድል የሚፈጥሩም ናቸው።
ከዚህ ባሻገር፣ መርሀ ግብሩ ለደን የሚሆኑ ችግኞች የሚተከሉበት ብቻ ሳይሆን፤ ለከተማ ውበት፣ ለመድኃኒት፣ ለገቢ ምንጭነት፣ ለምግብ እና መኖ አገልግሎት የሚሆኑ ችግኞችም ከፍ ባለ ምጣኔ እንዲካተቱ የተደረገበትም ነው። ለምሳሌ፣ ከቀደሙት ዓመታት አንጻር ሲታይ በዚህ ዓመት የሚተከለው የፍራፍሬ ችግኝ ቁጥሩ ከፍ ያለ ነው። በተመሳሳይ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው የቀርከሃ ችግኝም ከክልሎች ጋር በመተባበር መጠኑ ከፍ እንዲል ተደርጓል።
በመሆኑም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብሩ፣ በእነዚህና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎቹን ከዓመት ዓመት ሕዝቡ እየተገነዘባቸው፤ በልኩም እየተጠቀመባቸው ከመሆኑ አኳያ፤ አፈጻጸሙም በዛው ልክ እያደገ መጥቷል። ባለፉት አምስት ዓመታትም ከዕቅድ በላይ እየተፈጸሙ ለመዝለቃቸውም ሆነ፤ በአንድ ጀንበር በሪከርድ የተሰበረባቸው በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የመተከላቸው ምስጢርም ይኼው ነው።
የዘንድሮው መርሀ ግብርም፣ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ለምታደርገው ጥረት ያለውን ከፍ ያለ ፋይዳ በመረዳት፤ በሌላ በኩል መርሀ ግብሩ ያለውን ከፍ ያለ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ በመገንዘብ ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ አፈጻጸም ሊታይበት የሚገባ ነው።
ለዚህ ይሆን ዘንድም ከወዲሁ አስፈላጊውን ሥራ መሥራት የሚገባ ሲሆን፤ የሕዝቡን ባለቤትነት በሚያረጋግጥ መልኩ አቅጣጫ አስቀምጦና ይሄንኑ አስገንዝቦም ለተፈጻሚነቱ መረባረብ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ፣ ተግባሩ የኢትዮጵያውያን ከፍ ብሎ የማሰብ አቅም፤ ያሰቡትን የመፈጸም ቁርጠኝነት፤ እንዲሁም ያሰቡትን በመፈጸም ሂደት ውስጥ የሚታይ የመተባበር ከፍታ የሚገለጥበት መሆኑን ላፍታም መዘንጋት አይገባም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም