ሰብዕናው የተገነባ ትውልድን ለማፍራት የትምህርት ተቋማት ሊሠሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡- ሰብዕናው የተገነባ ትውልድን ለማፍራት የትምህርት ተቋማት የበለጠ ሊተጉ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

ከሚያዚያ እስከ ሚያዚያ የጸረ አደንዛዥ ዕጾችና አሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችን የመከላከል ሀገር አቀፍ ንቅናቄ የአፈጻጸም ግምገማ በትናንትናው ዕለት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወይዘሮ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደተናገሩት፣ ከአደንዛዥ ዕፅ የጸዳና ሰብዕናው የተገነባ ትውልድን ለማፍራት በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየሠሩ ያሉትን ሥራ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡

ተምረው የሚመረቁ ብቻ ሳይሆን ሰብዕናቸው የተገነቡ ትውልድን ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምን ያህል ተጋድሎ እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህን ጥረት የማህበረሰቡን ችግር በሚፈታ ጥናት ላይ የተመሠረተ በማድረግ ድርሻ አላችሁ ብለዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህንን እምቅ አቅም በመጠቀም የማይናቁ ውጤቶችን ማስመዝገቧን አንስተዋል፡፡

እርሳቸው እንደተናገሩት፤ በወጣቶች ዘንድ መነቃቃትን በመፍጠር ከፌዴራል መንግሥት ጀምሮ በክልል እስከ ታችኛው ተዋረድ ባሉ መዋቅሮች አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት ወጣቶችን በተለያዩ መስኮች ማሳተፍ ተችሏል፡፡

ይህንን ጅምር አጠናክሮ ለማስቀጠል ለወጣቱም ሆነ ለሌላው ማህበረሰብ የጊዜው ፈተና የሆነው የአደንዛዥ

ዕፅ ተጠቃሚነትና የአሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች መስፋፋትን ለመከላከል በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።

መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችን እና አደንዛዥ እጽን መከላከል ካልቻልን የወጣቱን ወጣት በመሆን ብቻ የሚገኝ ተፈጥሯዊ አቅም ሊነጥቀው ይችላል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይህን በትውልድ ላይ የተደቀነውን ችግር ለመቅረፍ የቤት ሥራችንን እንወጣ ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ፤ የትውልድን ሰብዕና የመገንባት ኃላፊነት የጥቂት ግለሰቦች ወይም የጥቂት ተቋማት ጉዳይ አይደለም ያሉ ሲሆን፤ አያይዘውም፣ ወጣቱን ትውልድ ለሀገር የሚጠቅም ኃይል ለማድረግ ሁሉም አጽንኦት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ትውልድን ከአደንዛዥ ዕጽና ከአሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች ለመጠበቅና በሱስ ውስጥ ያሉትን ከሱስ ለማላቀቅ በሚደረገው ጥረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የወጣት አደረጃጀቶች የሚሠሩት እንዳለ ሆኖ እያንዳንዱ ቤተሰብ የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ከሚያዚያ 2015 ዓ.ም ሚያዚያ ወር ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 2016 ዓ.ም ድረስ ሲካሔድ የነበረውን ንቅናቄ አፈጻጸም ግምገማ ያቀረቡት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ፣ በንቅናቄው በርካታ ሥራዎች መሥራታቸውን አንስተዋል።

በተሰሩ ሥራዎች ለውጦች መምጣታቸውንም ገልጸው፤ በንቅናቄው የቅንጅት ክፍተት እንደነበረ አመላክተዋል፡፡ ይህም የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዳይቻል ተግዳሮት እንደነበርም አንስተዋል።

በቀጣይ ሰብዕናው የተገነባ ወጣትን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት፣ የፍትህ አካላት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ራሱ ማህበረሰቡ በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ትውልድን ከአደንዛዥ ዕጽ ነጻ የማድረግ ሥራ የትውልድ ቅብብሎሽን የማስቀጠል ተግባር ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህ ጉዳይ የማያገባው አካል የለም ብለዋል፡፡

ትውልዱን በዘላቂነት ከእጽና ከአሉታዊ መጤ ልማዶች ለመከላከል ሌሎች የወጣቱን ትኩረት የሚስቡና አቅሙን አውጥቶ መጠቀም በሚችልባቸው የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም የፌዴራልና የክልል ተቋማት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You