በልማት ሥራዎች በሲስተም መቋረጥ ግብር ከፋዮች እንዳይጉላሉ አማራጭ ማስቀመጥ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፦ በልማት ሥራዎች በሲስተም መቋረጥ ግብር ከፋዮች እንዳይጉላሉ አማራጭ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡ በኮሪደር ልማት በተፈጠረው የሲስተም መቋረጥ ግብር ከፋዮች እንዳይጉላሉ በቂ አማራጭ አስቀምጦ እየሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የአራዳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉ ኃይለ ሚካኤል ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስትና ወረዳ አንድ በኮሪደር ልማት የግብር መክፈያ ጣቢያዎች ላይ የሲስተም መቋረጥ አጋጥሞ ነበር። ነገር ግን በሌሎች ወረዳዎችና በክፍለ ከተማው በኩል የሚስተናገዱበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ከዚህ አኳያ በከተማም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ተገልጋዩ እንዳይንገላታ የተለያዩ አማራጮችን አስቀምጦ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በዚህም የወረዳ አምስት ግብር ከፋዮች ወረዳ ስድስት እንዲስተናገዱ ተደርጓል ብለዋል፤ በተመሳሰይ የወረዳ አንድ ተገልጋዮችም በጽህፈት ቤቱ አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል። አገልግሎቱ ላይ ጫና እንዳይፈጠርም ሠራተኞችን ወደዛ በማዛወር በቂ የሰው ኃይል፤ ኮምፒውተርና ሌሎች ግብአቶች እንዲሟሉ መደረጉን አብራርተዋል።

በተጨማሪ ከሦስት ዓመት ወዲህ ክፍያ በኢ-ፔይመንት ሲስተም እየተከናወነ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም በተለይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መረጃዎች የሚላኩላቸው ግብር እንዲከፍሉ የሚደረገውም በስልካቸው በመሆኑ በመደበኛ አካሄድ ቅርንጫፍ መምጣት የሚያስፈልግበት ሁኔታ እንደሌለም ተናግረዋል።

የአማራጭ ሁኔታዎች የተመቻቹት ችግሩ እንደታወቀ ከኢትዮ ቴሌኮም አመራሮች ጋር በተደረገ ንግግር ለማስተካከል ጊዜ እንደሚወስድ እንደታወቀ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ አማራጮቹ የትኛውም ግብር ከፋይ ቀድሞ ያገኝ የነበረውን አገልግሎት በጊዜም በጥራትም በተመሳሰይ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

አገልግሎቱ የሚሰጠው በአንድ ሲስተም በመሆኑ የትኛውም ተገልጋይ በየትኛውም ወረዳ ምንም የተለየ እንግልት ሳይገጥመው መገልገል ይችላል ያሉት ሥራ አስኪያጇ፤ ይህም ሆኖ በአንዳንድ ልዩ ጉዳዮች የተገልጋዮች ማህደር መቅረብ ካለበትም በፍጥነት የሚመጣበት ሁኔታ የተመቻቸ ሲሆን፤ በተቋማቱ መካከል የቦታ ርቀትም ስለሌለ በአግባቡ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ነው ያሉት።

እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለጻ፤ እነዚህን የቦታ ለውጦችም ማስታወቂያ በመለጠፍ እንዲሁም ለአገልግሎት ለሚመጡ ተገልጋዮች በሙሉ ሠራተኞች እንዲያሳውቁ በማድረግ የመረጃ ክፍተት እንዳይፈጠር ተደርጓል። በዚህም በርካታ ግብር ከፋዮች በተቀመጠው አማራጭ መሠረት እየተስተናገዱ ይገኛል።

ይህም ሆኖ ጽህፈት ቤቱ ቅሬታ መስሚያ የተደራጁ ክፍሎች ያሉ በመሆኑ የተለየ ችግር ያጋጠመው ካለ አቤቱታውን በማቅረብ እዛው ባለበት መፍትሔ የሚሰጠው መሆኑንም ጠቁመዋል። መጪው ወቅት ግብር ማሳወቂያ ነው። በመሆኑም ደንበኞቻችን በተለይም የቦታና ቤት ግብር ከፋዮች በወቅቱ በመክፈል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና ከቅጣትም እንዲተርፉ አሳስበዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You