– 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፡– በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር 25 በመቶ የሚሆነው በዓባይ ተፋሰሶች እንደሚተከል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡ በ2016/17 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የቅድመ-ተከላ ዝግጅት በሁሉም አካባቢዎች እየተሠራ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት የ2016/17 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የቅድመ ዝግጅት ሥራን አስመልከቶ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል በ132 ሺህ 144 የችግኝ ጣቢያዎች ችግኝ የመፍላት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ 25 በመቶ የሚሆነው በዓባይ ተፋሰሶች የሚተከል መሆኑን በመግለጫው ገልጾ፤ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ዝግጅትና ተከላ ለበርካታ ወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የሥራ እድል እንደፈጠረ ተጠቁሟል፡፡
በ6 ሺህ 200 ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፤ ለተከላ የተዘጋጁት ችግኞችም ዘርፈ ብዙ ገቢ የሚያስገኙ አትክልትና ፍራፍሬ፤ ጥምር ደን፤ ለከተማ ውበት እና ለደን የሚዉሉ ናቸው፡፡ ለአረንጓዴ አሻራ ስኬታማነት የሁሉንም ተሳትፎና ዝግጁነት ከወዲሁ የሚጠይቅ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
አረንጓዴ አሻራ ለኢትዮጵያዊያን እንደ ባህል እስኪቆጠር ድረስ ተግቶ በመሥራት አረንጓዴ የለበሰች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በጋራ መቆም እንደሚገባ ገልጿል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡ የተተከሉት ችግኞችም በዘርፉ ሙያተኞች በተደረገው ክትትል 90 በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸው በመግለጫው ተነስቷል፡፡
የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ሲጠናከርና ተከታታይነት ባለው መንገድ ሲሠራ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ነጻ የሆነና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን መሠረት ያደረገ አካባቢያዊ የአየር ንብረት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የተራቆተ መሬትና አካባቢ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚኖረው ተጽዕኖ ቀላል እንደማይሆን ተገልጿል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በመላ ሀገሪቱ በተተከሉ ችግኞች ቀደም ሲል ተራቁተው የነበሩና የአፈር መሸርሸር አጋጥሟቸው የነበሩ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት ወደ ቀድሞ ገጽታቸው ተመልሰዋል፡፡ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ በተለያዩ ዘርፎች ውጤቶችን እያሳየ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ ተደጋጋሚ ድርቅ ሲያጠቃቸው የነበሩ አካባቢዎች ዝናብ ማግኘት ጀምረዋል፣ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ተችሏል፤ የደረቁ ምንጮችና ሀይቆች ወደ ነበሩበት መመለስ ችለዋል፣ ለበጋና የመኸር እርሻ ተስማሚ የሆነ ዝናብ ማግኘትም ተችሏል፡፡
ከሥራ እድል ፈጠራ አንጻርም ለእንስሳት መኖ፣ ለንብ ማነብ፣ ለካርቦን ሽያጭ፣ ለጎረቤት ሀገራት መልካም ጉርብትና እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ በመግለጫው ተነስቷል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር