በቢሾፍቱ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የኮሪደር ልማት እየተካሄደ ነው

– በልማቱ ለተነሱ 300 ነዋሪዎች ምትክ መሬት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፡- በቢሾፍቱ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የኮሪደር ልማት እየተሠራ መሆኑን የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ በልማቱ ለተነሱ 300 ነዋሪዎች ምትክ መሬት መሰጠቱም ተገልጿል፡፡

የቢሾፍቱ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በከተማዋ በ19 ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት መሠራት ተጀምሯል፡፡ 80 ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ሰባት ትላልቅ መንገዶች ላይ የዲዛይን ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

በከተማዋ የኮሪደር ልማት ለማከናወን ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የመነሻ በጀት ተመድቦ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ በአጠቃላይ ከ96 ኪሎ ሜትር በላይ የኮርደር ልማት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኮሪደር ልማት ሥራው 24 ሰዓት ያለ እረፍት እየተሠራ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ ሊፈጅ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ገዛኸኝ ገለጻ፤ በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የእግረኛ መንገድ የያዘ ብቻ ሳይሆን አንድ የመኪና መተላለፊያ ብቻ የነበረውን ዋና አስፓልት ባለ ሁለት ለማድረግ የሚሠራም ጭምር ነው፡፡ የመንገድ ስፋቱንም ከ80 እስከ 150 ሜትር እንዲሸፍን የሚደረግ ይሆናል፡፡ ይህ ግንባታ ሲጠናቀቅም ከ30 ዓመት በላይ ያለ ምንም እክል እንዲያገለግል ታስቦ የሚሠራ ነው ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ የብስክሌት መንገድ 30 ሄክታር የሚሸፍን አረንጓዴ ስፍራ እና የእግረኛ መንገድ ያካተተ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ገዛኸኝ፤ በአጠቃላይ ይህ የልማት ሥራ የረጅም ጊዜ ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በኮሪደር ልማቱ የሚፈርሱ የቀበሌ ቤቶች መኖራቸውን የሚገልጹት ምክትል ከንቲባው፤ ከተማ አስተዳደሩም በልማት ለሚነሱ ማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ ልማቱ ወደማይነካቸው አካባቢዎች ከማዘዋወር በተጨማሪ ለ300 አባ ወራዎች መሬት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ቢሾፍቱ ከተማ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ምክትል ከንቲባው፤ ይህን ራዕይ ለማሳካት ከተማዋን ማስዋብና ለእንግዶች ምቹ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ውብ፣ጽዱና የትራፊክ ፍሰት የተሳለጠባት ከማድረጉ ባሻገርም ለከተማዋ ነዋሪዎች ሰፊ ሥራ እድል የሚፈጥር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You