ትምህርት ቤቱ ለክፍለ ዘመን ያካሄደውን ትውልድን የማነፅ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

– የላዛሪስት ካቶሊክ ትምህርት ቤት 100ኛ ዓመት ምስረታ መከበር ጀመረ

አዲስ አበባ፡- ለአንድ ክፍለ ዘመን ያካሄደውን ትውልድን በሥነ-ምግባርና በክህሎት የማነፅ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የላዛሪስት ኮቶሊክ ትምህርት ቤት አስታወቀ።

“የአንድ ክፍለዘመን የላቀ ትውልድ ውርስ” በሚል መሪ ሃሳብ የላዛሪስት ካቶሊክ ትምህርት ቤት የ100ኛ ዓመት የምስረታ በዓል መክፈቻ በትናንትናው እለት ተካሂዷል።

የላዛሪስት ካቶሊክ ትምህርት ቤት ዋና ዳይሬክተር አባ ጌታሁን ፈንታ እንደገለፁት ፤ የላዛሪስት ካቶሊክ ትምህርት ከ1917 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ለአንድ መቶ ዓመታት የመማር ማስተማር ሥራውን እያከናወነ ይገኛል ።

በነዚህ የመቶ ዓመታት እድሜም ትምህርት ቤቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ባለሙያዎችና የስኬት ተምሳሌት የሆኑ ተማሪዋችን ያፈራ የሀገር አለኝታና የትውልድ ዐሻራ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ለአሁኑና ለመጪው የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች አርዓያ የሆኑ ተግባራትን ለማስቀጠልና ትውልድን በእውቀት የማነፅ ተግባሩን ለማስቀጠል በትኩረት ይሠራል ሲሉ ተናግረዋል።

ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ተሳታፊ እንዲሆኑም ክብረበዓሉ ቀደም ብሎ መጀመሩን አባ ጌታሁን ገልፀዋል።

የአንድ መቶኛ ዓመት ክብረ በዓል እስከ ጥር ወር 2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል አመላክተው፤ በነዚህ ጊዜያትም የገቢ ማሰባሰቢያ፣ የፖናል ውይይቶች፣የስፖርታዊ ውድድሮችና የፎቶግራፍና የስዕል አውደ ርዕዮችን ጨምሮ የተለያዩ መርሀግብሮችን እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለፁት፤ ትምህርት ቤቱ በተለያዩ አካላት የተላለፈውን ትውልድን የማነጽ የዘመናት ቅብብሎሽን ለማስቀጠልና ተደራሽነቱን ለማስፋት የትምህርት ቤቱ ቁጥር ሁለት ቅርንጫፍ ከመክፈት ጀምሮ የሁለተኛ ክፍለ ዘመን ጉዞን ለማሳካት ሰፊ ሥራ ይሠራል።

የላዛሪስት ካቶሊክ ትምህርት ቤት ስመጥርና ረዥም ታሪክ ያለው በመሆኑ ትምህርት ቤቱ በሚገኝበት አካባቢ በማህበረሰቡ በተለምዶ የላዛሪስት መንገድና ሰፈር ስያሜ የሚጠራ ሲሆን ፤ በትምህርት ቤቱ ፊትለፊት የሚገኘው የአስፓልት መንገድም በላዛሪስት ስም እንዲሰየም ለአዲስ አበባ ከንቲባ ፅህፈትቤት ጥያቄ ቀርቦ ውጤቱን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የትምህርት ቤቱ መስራች የሆነው የማህበረ ልዑካን ላዛሪስት ገዳም የበላይ አለቃ አባ መኮንን ሉካ በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቱ በአካባቢው የትምህርት እድል ያላገኙ ዜጎችን ለማስተማር ታስቦ በላዛሪስት ገዳም አባቶች የተመሠረተ መሆኑን አንስተዋል።

የእውቀት ችቦ እንዲበራ ያስቻሉትና በትምህርት የእድገት ጉዞ ውስጥ የእራሳቸውን ዐሻራ ያሳረፉ የገዳሙ አባቶች፣ መምህራን ፣ ወላጆችን ማሰብና ማመስገን እንደሚገባ ተናግረዋል።

በቀጣይም የትምህርት ማህበረሰብቡ ለሁለተኛ ክፍለ ዘመን ጉዞ የበኩሉን እንዲወጣ ና በ100 ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ እስከመዝጊያ መርሀ ግብር ድረስ እንዲሳተፍ አባ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል።

በመክፈቻው በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ የትምህርት ቤቱ ሃላፊዎች፣ መምህራንና ሃላፊዎች እንዲሁም የቀድሞ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You