በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሥራ ዕድል ፈጠራ የተጀመረው የቅንጅት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፡- በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የተጀመረው የቅንጅት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ (STRIDE Ethiopia 2024 Expo) ትናንት ተጠናቋል።

ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በመዝጊያ መርሐግብሩ እንደተናገሩት፤ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የተጀመረው የቅንጅት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ለፈጠራ ሥራ ትኩረት በመስጠት ያደገችና ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ በቅንጅት መሥራት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ሀገርን በመንግሥት አቅምና ጥረት ብቻ ማሳደግ አይቻልም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሀገራዊ የልማት ውጥኖችን ከግብ ለማድረስ የግሉን ዘርፍ የሚያሳተፍ የፖሊሲ ማዕቀፍ በመዘርጋት አስቻይ መደላድልን መፍጠር ይገባል ብለዋል።

እንደ ዶክተር በለጠ ከሆነ፣ የግሉ ዘርፍ ምርምር በማድረግ፣ ቀጣይነት ባለው ሀገራዊ ልማትና በሁሉም ዘርፎች በንቃት ሊሳተፍ ይገባል።

መንግሥትም የጋራ መድረክን መፍጠርና ወጣቱን ወደ ገበያ ማስገባት የሚችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንዳለበት ተናግረዋል።

ሥራን በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ለመሥራት የቴክኖሎጂ ሽግግር ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ የሥራ እድልና ሀብትን የሚፈጥር የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጥን በትብብር መሥራት የግድ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ቴክኖሎጂ ከውጭ ከማስገባትና ከመጠቀም ይልቅ የሀገር ውስጥ አቅምን፣ ፈጠራንና ቴክኖሎጂን በማሳደግ ሀገር በቀል ኢኮኖሚን መገንባት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የፈጠራ ሃሳቦችን በማገዝና እውቅና በመስጠት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየውን ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ 200 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች እንደጎበኙትና 105 ተቋማት ሥራቸውን እንዳቀረቡበት የተገለጸ ሲሆን፤ ኤክስፖው ሀገሪቱ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የደረሰችበትን ደረጃ ለመመልከትና በዘርፋ ተጨማሪ አቅምን ለመፍጠር ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

ለኤክስፖው አስተዋፅኦ ላደረጉና በቴክኖሎጂ ዘርፍ አመርቂ ውጤት ላስመዘገቡ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።

በማጠቃለያ መርሐግብሩ ሚኒስትሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You