በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የድርሻችንን በመወጣት ለወገኖቻችንን አለኝታ መሆናችንን እናረጋግጥ!

የሰው ልጅ ከፍ ያለ ማንነቱ ከንግግሩ ባለፈ በተግባሩ ይገለጻል። ይሄ የንግግርም ሆነ የተግባር ፍሬው ደግሞ ከራሱ አልፎ በሌሎች ሕይወት ላይ በአዎንታዊ አልያም በአሉታዊ ገጹ ይከፈታል። በዚህም የሰው ልጆች ለሰው ልጆች የደስታም የመከራም ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉበት በርካታ አጋጣሚዎችን ተመልክተናል።

ምክንያቱም ከመልካም ሰዎች የሚወጡ ቃላት የተሰበሩ ልቦችን ሲጠግኑ እና ተስፋን ሲያስጨብጡ የመመልከታችንን ያህል፤ መልካም ያልሆኑ ቃላት የሰው ልጆችን ሕልምና ተስፋ ሲያጨልሙ ታዝበናል። ተግባሩም እንዲሁ ነው። መልካም ተግባር የሰው ልጆችን ከፍ ያለ ሀሴት ሲያጎናጽፍ፤ ክፉ ተግባርም የሰው ልጆችን ቀና መንገድ ሲንድና ከመዳረሻቸው በአጭር ሲያስቀራቸው አይተናል።

የሰው ልጅ ደግሞ የተሻለውን መምረጥ፤ ለራሱም ለሌሎችም የሚበጀውን መንገድ መከተል ከፈጣሪም የተሰጠው ከፍ ያለ ኃላፊነትና ግዴታው ነው። እናም ከክፋት ይልቅ ደግነትንና በጎነትን በቃልም፣ በተግባርም መምረጥና እሱን መከወን ከሰው ልጅ የሚጠበቅ የሰውነት መገለጫ ሊሆን ያስፈልጋል።

ዛሬ ላይ እንደ ሀገር የሚያሳዝኑን በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም፤ እነዚያን አሳዛኝ ክስተቶች እንዳናስብ የሚያደርጉ የበዙ ተግባራትም አሉን። በተለይ ሰው ሆነን እንደ ሰው ለሰው ልጆች ለመድረስ የምናደርጋቸው ጥረቶች በእጅጉ ተስፋ የሚሰጡ፤ የወገኖቻችንንም እንባ አብሰው በፈገግታ የሚቀይሩ ናቸው።

በዚህ ረገድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ተጠቃሽ ናቸው። በጎ ፈቃድ ማለት አንድን ተግባር ለመከወን የማንንም ጉትጎታ፣ ግፊትና አስገዳጅነት ሳይጠብቁ፣ በራስ ተነሳሽነትና ፍላጎት የሆነን ጉዳይ ለመፈጸም መነሳሳት ነው። ይሄ መነሳሳት ደግሞ ወደ ትግበራ ያመራናል። እና የበጎ ፈቃድ ተግባራችን በራሳችን የውስጥ መሻትና መነሳሳት ተገፍቶ የሚገለጥ፣ የሚነገር፣ የሚታይ ተግባርን ለሌሎች በማድረግ ውስጥ የሚገለጥ ነው።

በተለይ በእኛ ሀገር እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ውስጥ የሚታይ ከፍ ያለ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያው ችግር ያለባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ባሉበት ሁኔታ፤ ይሄን መሰል በጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችለውን ሀሴት ለመገንዘብ ያለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን መመልከቱ ብቻ በቂ ነው።

በእነዚህ ዓመታት ከሀገር መሪዎች ጀምሮ በርካታ ልበ ቅኖች በበጎነት ሠርተው፣ የበርካታ ወገኖችን (አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ደጋፊ የሌላቸውን) ኀዘንና ትካዜ ወደ ደስታና ሀሴት መለወጥ ችለዋል። ተስፋ መቁረጣቸውን ሽረው ብዙህ ዕይታን እንዲጎናጸፉ አድርገዋል።

ለአብነት ያህል፣ እነዚህ በጎ ፈቃደኞች የድሆችን ቤት ጠግነውም፣ ገንብተውም ከብርድና ዝናብ ታድገዋቸዋል፤ ደም ለግሰው በደም እጦት የሚቀጠፉ ነፍሶችን ታድገዋል፤ ከትምህርት ቤት ዘልቀው የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት አለምልመዋል፤ ከማጀት ዘልቀው ወገኖቻቸው በልተው እንዲያድሩ አድርገዋል፤ ፈውስ የናፈቁ ወገኖችን ለፈውሳቸው ምክንያት ሆነዋል።

በተለይ ከለውጡ ማግሥት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስና የመገንባት የክረምት በጎ ሥራ ሂደት፤ በከተማ ደረጃ መነሳሳትን የፈጠረ፤ የዜጎችንም ተሳትፎ ያሳደገ እና የባለሀብቶችንም ልብ ወደዚሁ መልካም ተግባር እንዲቀላቀል ያነሳሳ ሆኗል።

ይሄው ተግባር ተጠናክሮ ዛሬ ላይ አስር ሺዎች ከመጠለያ አልባነት ወደ መጠለያ ባለቤትነት ተሸጋግረዋል። እንባቸው ታብሶም በፈገግታ ለሞልተዋል። ለዚህ ሁነኛ ማሳያው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ ስድስት ዓመት የበጎነት ውጥኑን ባኖሩበት አዋሬ አካባቢ ያለው ገጽ ነው። ይሄንን እውነትም “በየቦታው ብንተባበር፣ በየቦታው በቅንነት ብንተጋገዝ፣ ምን አይነት ለውጥ ልናመጣ እንደምንችል አዋሬ ማሳያ ነው።” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ያሉት ሰሞኑን በዚሁ አካባቢ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል አድርገው በያዙት የድሆችን ቤት የመሥራት መርሃ ግብር ባስጀመሩበት ወቅት ነበር። በወቅቱም፣ “ዛሬ በአዋሬ አካባቢ ከስድስት ዓመታት በፊት በጀመርነው የዝቅተኛ ወጪ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንቅስቃሴ ምናልባትም የመጨረሻው ሥፍራውን ለግንባታ ዝግጁ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። የመኖሪያ ሁኔታዎቹ ችግር የበዛባቸው ነበሩ። እጅግ ያረጁ፣ የተጠባበቁ፣ መፀዳጃ የሌላቸው መኖሪያዎች ነበሩ። ምቹ የመኖሪያ እና አረንጓዴ አካባቢ የሚያካትተው አዲሱን የመኖሪያ ህ ንፃ ግንባታ በመጪው መስከረም ወር ለ ማጠናቀቅ ዛሬ አስጀምረናል፤ ብለዋል።

አያይዘውም፣ ይሄን መሰሉ ሥራ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉትን ወገኖቻችንን ሕይወት ብቻ ሳይሆን የሪል ስቴት አልሚዎችንም የጠቀመ፤ በዚህ ፕሮጀክት የቀጣይነት መንፈስ የታየበትና ማጽናትም የተቻለበት ስለመሆኑ አስረድተዋል። በአካባቢውም የተከናወነው ተግባርም የመኖሪያ አካባቢዎችን ሊለውጥ፣ የነዋሪዎችን የኑሮ ዘይቤ እና ተስፋ ከፍ ሊያደርግ እንደሚችል ማሳያ ምልክት እንደሆነም ገልጸዋል።

የዚህ ዓመት የዝቅተኛ ቤቶች ግንባታ ወጪ በከፊል በቪዛ ፋውንዴሽን የተሸፈነ መሆኑን በመጠቆምም፤ “ሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች እና በጎ አድራጊዎች ለዜጎች ሕይወት እና ከባቢ መለወጥ ያለመታከት ልግስናቸውን እንዲዘረጉ ጥሪዬን አቀርባለው፤” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመሆኑም በዚህ መልኩ የታየው መልካም ጅምር ሊጠናከር፤ የዜጎች ስቃይና እንግልት እንዲወገድ፤ ለቅሶና ትካዜያቸው በፈገግታ እንዲለወጥ ማድረግ የቅን ልቦች ሃሴት ማድረጊያ፤ የመልካም ሰዎች መገለጫ ነው። በመሆኑም እኛም እንደ ዜጋ በዚህ መልኩ ራሳችንን ልንገልጥ ስለሚገባ፤ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሂደት ውስጥ የድርሻችንን በማበርከት በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን ዕንባ ማበስ እና ችግሮቻቸውንም መጋራት ይገባናል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You