አገራችን በለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ከገባች ስምንት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በነዚህ የለውጥ ጊዜያት ከዚህ ቀደም ያልነበሩ በርካታ ለውጦች ተከስተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም በአንድ በኩል ለውጡን ለማስቀጠልና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት፣ ብሎም በልማትና በመልካም አስተዳደር ግንባታ ሥርዓት ወደ ፊት ለመራመድ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡን በማደናቀፍ ጥቂቶች ብቻ የሚበለፅጉበትን አሠራር ለማስቀጠል በሚፈልጉ ኃይሎች መካከል ሰፊ ትግል ሲካሄድ ቆይቷል::
ከለውጡ በፊት የነበረውን የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት በርካታ የህብረተሰብ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች የሚስተናገዱበት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በተለይ በሰብኣዊ መብት አያያዝ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በሌብነት፣ ወዘተ ዜጎች ተማረው በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ቅሬታ የፈጠሩበት ወቅት ነበር፡፡ በሌላ በኩል በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች ለስደት የተዳገሩበት ሁኔታ ጭምር እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
በተለያዩ ተቋማት በነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ እና በሥራ አጥነት በመማረር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የህዝብ እምቢተኝነት በመበራከቱም ግጭቶች የተበራከቱበትና አገሪቷ የመበታተን አደጋ ውስጥ የወደቀችበት ወቅት ነበር፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞችና የውጭ ኃይሎች ጭምር ኢትዮጵያ ልትበታተን ነው የሚል ሥጋት ውስጥ የወደቁበት ሁኔታም ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡
መንግሥት ይህንን የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ በኃይል ለመቆጣጠር ያደረገው ሙከራም ምንም ፋይዳ ሊያመጣ አልቻለም፡፡ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅም ሠላምና መረጋጋትን ማምጣት ከባድ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይህንን የተረዳው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ በማድረግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት አድርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል ሥልጣኑን በመረከብ ሥር ነቀል ለውጦችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማከናወን ችሏል፡፡ የአገራችን ሕዝቦችም የመጣውን ለውጥ ከዳር እስከ ዳር በመደገፍ ከመንግሥት ጎን ለመቆም ተንቀሳቅሰዋል፡፡
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኃላፊነታቸውን ከተረከቡበት ማግስት ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከፍሎች በመገኘት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይት ከህብረተሰቡ ሰፊ ድጋፍ የተሰጣቸው ሲሆን እሳቸውም ፈጣን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማድረግ ቀንና ሌሊት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በአጭር ጊዜ መሰረተ ሰፊ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
በዚህ የለውጥ ሂደት ከተመዘገቡ ለውጦች ውስጥ የነበሩ ግጭቶችና ሁከቶች እንዲቆሙና ህብረተሰቡ ለአንድነትና ለጋራ ዕድገት እንዲሰለፍ የተደረገበት ሁኔታ ስኬታማ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር አካባቢያዊ ሠላምንም ለማረጋገጥ በተወሰዱ ፖለቲካዊ ውሣኔዎች ከሃያ ዓመታት በላይ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ዳግም እንዲስተካከልና ጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ በማድረግ በሁለቱ አገራት ሕዝቦች መካከል አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ መመለስ ተችሏል፡፡ የቀጣናውን አገራትም በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ለማጠናከር ከጎረቤት አገራት ጋር ውይይት በማድረግና በነዚህ አገራት መካከል ሠላም እንዲፈጠር በማድረግ የአካባቢው ሠላም ጤናማ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል፡፡ ከዚህም አልፎ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በተደረገው ውይይት የጋራ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ ለስደት ተዳርገው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም በሠላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡
በአገራችንም ተከስቶ የነበረውን የኢኮኖሚ ችግር ለማስተካከል ጠንካራ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና ፖለቲካዊ እርምጃዎችን በመውሰድ በአገራችን ላይ አንዣቦ የነበረውን የኢኮኖሚ ቀውስ ማስተካከል ተችሏል፡፡ በተለይ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በማስተካከል የውጭ ገበያውን ችግሮች ለመቅረፍ በተወሰዱ እርምጃዎች የአገራችንን ኢኮኖሚ ለጊዜውም ቢሆን ማረጋጋት የተቻለ ሲሆን በቀጣይም እነዚህን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚያቃልሉ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል ተጀምረው የነበሩና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ተቋርጠው ወይም ተጓትተው የቆዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች በአዲስ መልኩ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በከፊል ወደ ግል ይዞታ ተዘዋውረው አገራዊ ኢኮኖሚያችንን በሚያጠናክር ሁኔታ እንዲቀጥሉ፣ የማህበራዊ ተቋሞቻችን ተገቢውን አገልግሎት በሚሰጡበት ሁኔታ ዳግም እንዲዋቀሩ፣ ወዘተ ማሻሻዎች ተደርገዋል፡፡
ያም ሆኖ ግን አገራችን በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ብትገኝም በርካታ ፈታኝ ችግሮችም ከፊቷ ተጋርጠው ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች የሚከሰቱት ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀል ይጠቀሳሉ፡፡ ለምሣሌ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች፣ በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም ሰሞኑን ደግሞ በቤኒሻጉልና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶች የብዙዎችን ህይወት የቀጠፉና በርካታ ዜጎችንም ከአካባቢያቸው ያፈናቀሉ ናቸው፡፡
በተለይ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ማንኛውንም ጥያቄ ሠላማዊ በሆነ ሁኔታ ለመመለስ ጥረት እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት እንዲህ አይነት ግጭቶች መከሰታቸው ብዙዎችን ሠላም ፈላጊ ዜጎች ያሳዘነ ተግባር ነው፡፡
አብዛኛውን የአገራችንን ህዝብ ያስማማውና በጋራ ያንቀሳቀሰው የለውጥ ኃይል ከፍተኛ የህዝብ ይሁንታ ማግኘቱ ያልተዋጠላቸው አካላት መንግሥትን በኃይል በመጣል ለውጡን ለማደናቀፍ የመረጡት በዜጎች መካከል የዕርስ በዕርስ ግጭቶችን በመፍጠር ህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው ማድረግና መንግሥትን በማስጨነቅ በአቋራጭ ወደ ሥልጣን መመለስ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህንን ተረድቶ እንዲህ አይነት ሥራዎችን ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ለዚህ ተግባራቸው የሚመድቡት ገንዘብ በርካታ በመሆኑ ይህንን የሞት የሽረት ትግላቸውን ማስቆምም ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል፡፡ ሠላማችን በመጠበቅም በለውጡ የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠል ይጠበቅብናል፡፡