“የ66ቱም ሆነ የ83ቱ ክስተት – ለውጥ ወይስ አብዮት…!?”

መርገም እንበለው አለመታደል የሚያግባባን የጋራ ሰንደቅ አላማ፣ ታሪክ፣ ትርክት፣ ጀግና፣ ሀገራዊ ምልክት፣ ትውፊት፣ ባህል፣ ወዘተረፈ የለንም። ሀገሪቱ በምትመራበት ፍኖተ ካርታም ሆነ ራዕይ ላይ አንስማማም። ጥንታዊ የሀገረ መንግሥት ታሪክ ቢኖረንም፤ ሉዓላዊነታችንና ነፃነታችን የታፈረና የተከበረ ቢሆንም፤ ነገረ ሥራችን ግን ትላንት ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ የጎረቤት ሀገራት ያነሰ ነው።

ዛሬም ሀገረ መንግሥቱ ተሰርቶ አላለቀም። እንደ ሀገሬ ልጃገረድ ስፌት ገና በውጥን ላይ ነው። ሌላው ይቅርና ሊቃውንት አብዮትን በመበየንና በመለየት ዛሬም ድረስ አይግባቡም። አብዮት ለመባል የመደብ ሹም ሽርና መሠረታዊ ለውጥ መምጣት አለበት። ለውጡ ሁሉ አብዮት አይደለም ሲሉ የ2010 ዓ.ም ለውጥ በአብነት ያነሳሉ። አብዮት የ1966 እና የ1983 እንጂ ሌላው ለውጥ ነው ሲሉ ይሞግታሉ። የለም አብዮት የ1966 ዓ.ም እንጂ ሌላው ለውጥ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

ወደ ሊቃውንቱ እሰጥ እገባ ከማለፌ በፊት ታዋቂው የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሊቅ ደራሲና የCNN GPS ፕሮግራም አዘጋጅና በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ያተኮሩ ጹሑፎች አምደኛ ፋሪድ ዘካሪያ ሰሞኑን ለንባብ ባበቃው፤ “Age of Revolution” በተሰኘው መጽሐፍ፤ ስለ አብዮት ቀደም ብሎ የነበረንን አረዳድ እንድንፈትሽ አስገድዶናል። የ424 ዓመታትን አብዮት ቀንበብ አድርጎ በጥቂት መቶዎች በሚቆጠሩ ገጾች አስነብቦናል። ባለፉት 200 ዓመታት የእኛውን የ66ቱን አብዮት ጨምሮ 160 አብዮቶች ተካሂደዋል። ለፋሪድ ዘካሪያ እነዚህ ሁሉ አብዮቶች አብዮት አይደሉም። የቻይናው ሆነ የራሽያው የጥቅምት አብዮት፣ የአሜሪካ አብዮት የፈረንሳይ አብዮት አልያም የማህተመ ጋንዲ ጸረ ቅኝ ግዛት አብዮት ወይም የሄይቲው ጸረ ባርነት አመጽ ለፋሪድ አብዮት አይደለም።

ለእሱ አብዮት ከላይ ወደ ታች በሕዝብ ላይ የተጫነ ሳይሆን ከታች ከሕዝቡ ፈንቅሎ ወጥቶ በሕዝብ ዘንድ የሚቆጠር የሚታይ አዎንታዊ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው። የመጀመሪያውና የሁለተኛው የኢንዱስትሪ አብዮቶች በማህበረሰቡ ዘንድ መዋቅራዊ ለውጥ የመጡ ስለሆነ ለፋሪድ አብዮት ናቸው። ለእነዚህ አብዮቶቹ መሠረቶቻቸው ደግሞ የሆላንዱ አብዮት እና የብርቴኑ የግሎሪየስ አብዮት ናቸው።

ከዚህ አንጻር የ66ቱ አብዮት በልሒቃን ከላይ ወደ ታች የተጫነ ከመሆኑ ባሻገር ጨቋኝን አስወግዶ ሌላ ጨቋኝ በእግሩ የተካ ስለሆነ፤ የ1983ቱም በጣት በሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ልሒቃን መጀመሪያ በትግራዋይ በኋላም በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተጫነ ከመሆኑ ባሻገር አምባገነናዊ አገዛዝ በሌላ አምባገነን የተካ፤ የብሔርና የመደብ ጥያቄን አጃምሎ ቢነሳም ዛሬም ሳይፈታ በእንጥልጥል ቀርቷል። ከ30 ዓመታት በኋላ ዛሬም በልኩ ያልተመለሰ ጥያቄ ነው።

ስለሆነም በፋሪድ ዘካሪያ መከራከሪያ እንደ የ66ቱም ሆነ የ83ቱ ለውጥ ለአቅመ አብዮት አልደረሰም። ፋሪድ በአአዩ ጉባኤ በአካል ተገኝቶ መከራከሪያውን አቅርቦ ባይሞግት ከፍ ብሎ በገለጽሁት መጽሐፉ ትንተና ግን የ66ቱም ሆነ የ83ቱ ለውጥ አብዮት አይደለም። እነ ፕሮፌሰር ስለ አብዮት ያነሱትን መከራከሪያ ከፋሪድ ዘካሪያ መተርጉም ጋር እያነጣጠርን እንመልከት።

በዚያ ሰሞን ለትውልድ የተሸጋገሩ የ1966 ዓ.ም አብዮት ትሩፋቶችና ዕዳዎችን የተመለከተ ጉባዔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዶ ነበር። አጀንዳዎቹም የብሔር ፖለቲካ፣ ትክክለኛው የኢትዮጵያ አብዮት የትኛው ስለመሆኑ፣ የመሬት ጥያቄና አብዮቱ፣ አብዮቱ ያመጣቸው ለውጦች፣ በዴሞክራሲና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ምን ዓይነት በጎና ጎጂ ተፅዕኖዎች እንዳሳረፈ የሚገመግም 50ኛ ዓመቱን ያስቆጠረውን የ1966 ዓ.ም. አብዮት ትሩፋቶችና የተሸጋገሩ ዕዳዎች የተመለከቱ ነበሩ፡፡

ይሄ ጉባኤም የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁር ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር)፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አቶ ዘገዬ አስፋው፣ የፓርላማ አባሉ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርኼ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም ታደለች ኃይለ ሚካኤል (አምባሳደር) በተገኙበት እና ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደ ልዩ ጉባዔ ነበር፡፡ በወቅቱም ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ስንት አብዮት ተካሂዷል?›› በሚለው ጥያቄ ላይ ውይይት ተደርጓል።

ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር) ውይይቱ ሲጀመር የአብዮቱ ቁልፍ መንስዔዎች፣ የተማሪው እንቅስቃሴ፣ መጪው ትውልድ ከተማሪው ንቅናቄና ከአብዮቱ ምን ሊማር ይገባል በሚሉ መነሻዎች ባቀረቡት ጽሑፍ፣ የሕዝብ ጥያቄንና ንቅናንቄ መሠረት ያደረገ ነበር በማለት የኢትዮጵያ አብዮት በ1966 ዓ.ም. እና በ1983 ዓ.ም. መካሄዱን አስታውሰዋል። በውይይቱ ወቅት በሰጡት ማብራሪያም፣ ‹‹አብዮት የመደብ ሹም ሽር የሚደረግበት ነው፣ ለውጥ ሁሉ አብዮት አይባልም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

አረጋዊ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባህሩ (ፕሮፌሰር) መጀመሪያ ሲናገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉ አብዮቶች የ66 ዓ.ም. እና የ83 ዓ.ም. እንደሆኑ መጥቀሳቸውን ገልጸው፣ እሳቸው ግን “ሦስተኛ አብዮት የሚጨመር አለ፣” በማለት “የ2010 ዓ.ም፤” ብለዋል። ሃሳባቸውን የማይቀበሉ እንደሚኖሩ የገለጹት አረጋዊ (ዶ/ር)፣ በውይይት ልንፈታው እንችላለን፤›› ሲሉ ሦስተኛ አብዮቶች ነበሩ ያሉበትን ምክንያት አስረድተዋል። ‹‹የ2010 ዓ.ም. ትልቅ ንቅናቄ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ተቃዋሚ ኃይል ነበር፡፡ ሕወሓት እንደምታውቁት አፋኝ ሥርዓት ነበር። ከደርግ ያላነሰ ግን ደግሞ ቀስ እያለ ሰርስሮ እየገባ ብዙ ነገር ነው ያበላሸው፤›› ብለው፣ ‹‹ያ ሥርዓት የፈጠረው አመፅ ሀገሩን በሙሉ ያዳረሰ፣ በተለይ በወጣቱ በተለያዩ ቦታዎች አመፅ ያስነሳ፣ ሕወሓቶች መግዛት እስኪያቅታቸው ድረስ የሆኑበትን ሁኔታ የፈጠረ ስለሆነ ለእኔ አብዮት ነው፤›› በማለት ምክንያታቸውን አቅርበዋል።

የ2010 ዓ.ም. ለውጥ አብዮት ሊባል አይችልም ሲሉ የተከራከሩት ባህሩ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ‹‹አብዮትና ለውጥ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፣ ለውጥ ሁሉ አብዮት አይባልም፤›› ሲሉ ገልጸዋል። ‹‹ለውጥ በምንም መንገድ ሊከሰት ይችላል፣ አብዮት ግን የመደብ ሹም ሽር የሚካሄድበት ነው። ገዥ የነበረው ወይ ተገዥ ይሆናል ወይ ደግሞ ይወገዳል። ምንም ይሁን ምን በሚወሰደው ርምጃ በአብዮት አገዛዙ ሙሉ ለሙሉ ይቀየራል፣ ይህ ነው እንጂ ለውጥ ሁሉ አብዮት አይባልም፤›› ብለዋል።

የ1983 ዓ.ም የሥርዓት ለውጥ አብዮት ነው ያሉባቸውን ሁለት ምክንያቶችንም አስቀምጠዋል። በተቀዳሚነት የጠቀሱት፣ ‹‹ሃምሳ ዓመት የቆየ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት ነው የተለወጠው፣ 50 ዓመት በሀገር ግዛት ሚኒስቴር ሥር ይተዳደር የነበረ በክልል እንዲተዳደር ነው የተደረገው፣ ይህ መሠረታዊ ለውጥ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል። አያይዘውም ከኢሕአዴግ ከቀደመው የጠቅላይ ግዛት ሥርዓት ክልሎች የበለጠ ሥልጣን የተሰጣቸው ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።

ባህሩ (ፕሮፌሰር) በሁለተኛነት በአስተዳደር ደረጃ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ሁሉን ነገር በብሔረሰብና በኅብረተሰብ የማየት ነገር መከሰቱንም ገልጸው፣ ይህ አሁንም ድረስ ያስቀጠለው ችግር ያሉትን በምሳሌ ተናግረዋል። ‹‹በመጀመሪያው አብዮት ጊዜ ሰው ቢገደልም ቢሰቃይም፣ በርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ ወይም በመደብ ካልሆነ በስተቀር በማንነት አልነበረም። አሁን ግን ያለው በማንነት የምናየው ነገር ነው የሚደርሰው፡፡ መፈናቀልም ሆነ መገደል ማንነት ላይ የተመሠረተ ነገር ነውና ይህ መሠረታዊ ልዩነት ነው፤›› ብለዋል።

ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አብዮት ነው የተከሰተው፣ እሱም የ1966 ዓ.ም. ነው፤›› ብለው፣ ከዚያ በኋላ የመንግሥት ለውጦች መደረጋቸውን በመግለጽ የ1983 ዓ.ም. በጠመንጃ የተደረገ የትጥቅ ትግል ያመጣው ለውጥ እንጂ አብዮት ሊሉት እንደማይችሉ ተናግረዋል። የ2010 ዓ.ም. ለውጥ የሕዝቡ እንቅስቃሴ ታሳቢ ሲደረግ የአብዮት ባህሪዎች ቢያሳይም፣ የሥርዓት ለውጥ ግን ስላላመጣ አብዮት ሊባል አይችልም ብለዋል።

በውይይቱ ታዳሚ የነበሩት ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ለምሁራኑ ባቀረቡት አስተያየት፣ ‹‹ከፖለቲካ ፍጅት ወደ ዘር ፍጅት ተሸጋግረናል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎችና የክልሎች አደረጃጀት በማይስተካከልበት ሁኔታ ዘረኝነት እያሉ መቀጠል ይቻላል ወይ?›› የሚል ጥያቄም አቅርበዋል። አረጋዊ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ የዘር ፖለቲካ የሚለው ትክክለኛ አገላለጽ እንደማይመስላቸውና የብሔርን ትግል ለማጣጣል የሚጠቀስ ቃል ነው ብለዋል።

‹‹የብሔር ትግል የዘር አይደለም፣ የሚደራጀው የብሔር አድልኦ አለ ከሚል ነው፣ ሁላችንም እንደ አንድ ዜጋ እኩል እንታይ ከሚል የሚነሳ ነው፤›› ሲሉ ገልጸውታል። ‹‹በብሔሮች መካከል ሰፊ ልዩነቶች ነበሩ፣ አንዱ ብሔር ከሌላው ራሱን አብልጦ አይቷል፣ ብልጫ ከያዘ ደግሞ የራሱን ብሔር የሚያሰባስብ ነበር፣ ይህ ደግሞ የተለመደ ነበር፤›› ሲሉ በወቅቱ ነበረ ያሉትን ሁኔታ አብራርተዋል።

‹‹ከእነ ምሳሌውም ዘመድና መድኃኒት ሲጨንቅ ነው የሚፈለገው ይባላል። ምናልባትም ሥልጣን እንዳይነጠቁ ሲጨነቁ የራሳቸውን ወገን ያሰባስባሉ የሚል ዓይነት የዕሳቤ ዘንግ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፤›› ብለዋል። አንድ ብሔር ጥያቄ ሲያነሳ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የቋንቋና እንዲሁም ሌሎች ጥቅሞቹን ለማስከበር፣ ራሱን የሚገልጽበትን ሁኔታዎችን ለማስጠበቅ የሚደራጅበት ድርጅት ነው በማለት ሴቶችና ሠራተኞች ሲደራጁ ጥቅማቸውን ለማስከበር፣ ለተጎዱበት መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደ መሆኑ በብሔር መደራጀትም በዚያ መልክ ቢታይ ጥሩ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ትግል ትልቅ ኃይል ያለው እንቅስቃሴ መፍጠሩን የገለጹት አረጋዊ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህ መፈታት ያለበት ችግር ነው፣ ዕውቀትን መሠረት ባደረገና በሰከነ ውይይት መፈታት የሚችል ጉዳይ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል። ‹‹እንደ ሰጎን አንገታችንን ወደ አሸዋ ብንደብቅ ችግሩ ይፈታል ማለት አይደለም፣ የለም ብለን ስላወጅንም የሚፈታ አይደለም፤›› ብለዋል። የብሔር ፖለቲካ ችግርን ለመፍታት የሚያስችሉ ብዙ መንገዶች አሉ በማለት፣ ‹‹ፌዴራሊዝም አለ፣ ኮንፌዴራሊዝም አለ፣ ሌሎች ሀገሮች ችግሩን በፈቱበት አግባብ በመሄድም ሊፈታ የሚችል ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ባንሸሸው ጥሩ ይመስለኛል፤›› ብለዋል።

ዲማ (ዶ/ር)፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔርም ሆነ በፈለጉት መንገድ ቢደራጁ ምንም ችግር የለብኝም፣ ገደብ በማበጀት ስለማላምን ነው፤›› በማለት በፓርቲዎቹ ውስጥ ችግር ነው ያሏቸውን ጉዳዩች አንስተዋል። ‹‹በቅድሚያ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አደረጃጀት ከጅምሩ ብዙ ክፍተት አለው፣ አብዛኞቹ የተፈጠሩት ወይ በድብቅ ወይም በወታደራዊ እንቅስቃሴ መሆኑ የራሱ የሆነ ችግር አለው፤›› ብለዋል። ‹‹አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች የቡድን ጥርቅም ወይም ስብስብ ናቸው። አንዴ ከላይ ያሉ አመራሮች ይደራጁና ከዚያ ይመለምላሉ እንጂ፣ ለፖለቲካ ድርጅት አንድ ሰው በርዕዩተ ዓለሙና በፕሮግራሙ አምኖበት አባል ልሁን ብሎ ሄዶ ማመልከት የሚችልበት አስቻይ ሁኔታ ያለ አይመስለኝም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

አያይዘውም በብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጭ ያለው ችግር ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓት አለመኖር መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህም ሰፊ የሆነ ሕዝባዊ መሠረት እንዳይኖራቸው እንደሚገድባቸውና ሰፊውን ሕዝብ በፕሮግራማቸው ቀስቅሰውና አባል መልምለው ሰፊ መሠረት ሊያበጁ የሚችሉበት ሁኔታ በጣም የተወሰነ እንዳደረገው አብራርተዋል።

የክልሎች አደረጃጀት በዘር ላይ የተመሠረተ ነው ብለው እንደማያምኑና መሠረቱ ቋንቋ እንደሆነ የተናገሩት ዲማ(ዶ/ር)፤ ‹‹መጀመሪያ ክልሎች ሲቋቋሙ የተወሰደው መሥፈርት ቋንቋ ነው። ነገር ግን የተወሰኑ ክልሎች አንድ የሆነ ቋንቋ አላቸው፣ የተወሰኑ ደግሞ በብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎችና የተሰባጠረ ሕዝብ ያለባቸው ስለሆኑ፣ አንዱ ኢትዮጵያን እንዴት እናደራጅ የሚለው የሀገራዊ ምክክር አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ነው፤›› ብለዋል።

‹‹አብዛኛው ፖለቲከኛም ሆነ ከዚያም ውጭ ያለው ጥያቄ የኢትዮጵያን አስተዳደራዊ መዋቅር እንዴት ይሁን? ኢትዮጵያ በምን ዓይነት መንግሥታዊ መዋቅር ትደራጅ? ምን ዓይነት የፌዴራል አስተዳደራዊ መዋቅር ይኑራት? ወይስ ወደ ቀድሞ አኃዳዊ ሥርዓት እንመለስ? (አኃዳዊ ሥርዓት የራሱ የሆነ ጥቅም ስላለው) ግን ለኢትዮጵያ ይሆናል አይሆንም? የሚሉት ጉዳዮች ላይ መመካከር ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ሪፖርተር ጋዜጣ (የአማርኛውን) እና ሌሎች ምንጮችን ተጠቅሜያለሁ!

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You