በአንድ ሀገር እውን እንዲሆን ለሚጠበቅ ሁሉን አቀፍ ዕድገት እና ብልጽግና፤ እንደ ሀገር ካለው የመልማት አቅም ባሻገር፤ ዘመኑን የሚመጥን አሠራር ዘርግቶ መተግበር፤ ዘመኑን ያማከለ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በልካቸው ተገንዝቦና አልምቶ መጠቀምን አብዝቶ ይሻል።
ምክንያቱም በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ እንዳለ ሕዝብና ሀገር፤ ይሄንን ተለዋዋጭነት በልኩ መረዳት፤ ራስን ከሁኔታው ጋር አላምዶ መራመድ የግድ ይላል። በተለይ ዘመኑ ዓለም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች እሽቅድምድም ውስጥ የገባችበት ከመሆኑ አኳያ፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ራሳቸውን ወደዚህ የዓለም አውድ ውስጥ አስገብተው ተወዳዳሪ ለመሆን ይሄን መሰል አካሄድ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል።
ይሄ ማለት ግን ያለ ምንም እውቀትና ግንዛቤ የበለጸጉት ዓለማት ያበለጸጉትን ሁሉ ተቀብሎ መሄድ ማለት አይደለም። ይልቁንም ጊዜው የሰጠንን ዕድል በመጠቀም፤ የትኛው ቴክኖሎጂ ይጠቅመናል? የትኛውስ ለችግር ያጋልጠናል? የሚሉ ጉዳዮችን ለይቶ እና ከሀገራዊው አቅምና አውድ ጋር አጣጥሞ ከዓለም ጋር ለመራምድ የሚያስችል የራስ መንገድን መተለም ማለት ነው።
በዚህ ረገድ ቴክኖሎጂዎችን ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና አቅም ከማዋል አኳያ ለዘመናት ከኋላ ቀርተን ኖረናል። ይሄ ደግሞ አንድም ከመሪዎች ቸልተኝነት፤ ሁለትም፣ ከሕዝቡ የአመለካከት (ከባህልም ሆነ እምነት ጋር በተያያዙ) ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ይሄ ግን እንደ ሀገር ወደኋላ እንድንጎተት፤ እንደ ሕዝብም ዓለም በደረሰበት የእውቀትና ፈጠራ ከፍታ እንዳንደርስ አድርጎን ቆይቷል።
ከ2010 ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ግን፣ የዜጎችን ሁሉን አቀፍ ለውጥና ተጠቃሚነት፣ የሀገርንም ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና ከማረጋገጥ፤ አልፎም የሀገርን ሉዓላዊነትና ደኅንነት ከማስጠበቅ አኳያ፤ እነዚህን ዘመን አፈራሽ የፈጠራ ውጤቶች በልካቸው ተገንዝቦ መጠቀም በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሠራ ይገኛል።
በዚህም እንደ ሀገር በአስር ዓመት ሊተገበር ለተተለመው ስትራቴጂክ ተግባራት መካከል አንዱ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ነው። ይሄ ደግሞ እንደ ሀገር ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥራዎች እና ለፈጠራ ትኩረት የሚሰጥ ሲሆን፤ በተለይ ዲጂታላይዜሽንን እውን ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ኢትዮጵያ አቅጣጫ ተነድፎ እየተተገበረ ይገኛል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ በተለይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ተደግፎ እንዲራመድ በሚያስችል መልኩ የተቃኘ፤ እንደ ሀገር እንዲሳኩ የሚፈለጉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የሰላምና ደኅንነት ተግባራት እንዲሳለጡ ማስቻልንም ታላሚ ያደረገ ነው።
በዚህ ረገድ የግብርና ልማቱም፣ ጤናው አገልግሎትም፣ የገቢ አሰባሰብ ሂደቱም፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥርዓቱም፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ተግባሩም፣ የሀገር መከላከያና ደህንነት ተቋሙም፣ የባንክና ተያያዥ ተቋማት አሠራርም፣… ሁሉም በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራን እንዲተገብሩ የሚያስችል ነው።
ዛሬ ላይ የግብርና ልማቱን ለማሳደግ የሚከናወኑ ጉዳዮችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ለማሰባሰብ፤ የጤና ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮች ለማቃለል፤ የገቢ አሰባበሱን ጨምሮ የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን፣ የዜጎች የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደትን ከምሬት ለማውጣት በተወሰዱ ርምጃዎች፤ እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ እንቅስቃሴዎች እየተገኙ ያሉ መልካም ጅምሮችም የዚህ እሳቤ ትግበራ ውጤቶች ናቸው።
ከሰሞኑም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተመረቀውና የዲጂታል ኢትዮጵያ አንድ አካል የሆነው የፌዴራል ፖሊስ የዜጎች መረጃ ማዕከል መተግበሪያ፤ ፖሊስ ከሕብረተሰቡ ጋር በተቀላጠፈ መልኩ ተባብሮ ወንጀልን ለመከላከል ለሚያደርገው ሥራ በእጅጉ አቅም የሚፈጥርለት ነው።
ይሄን መሰል ተግባር ታዲያ ኢትዮጵያ እውን ልታደርገው ለምትተጋለት ሁሉን አቀፍ ብልጽግና መሳካት የሚኖረው ሚና እጅጉን ወሳኝ ነው። ምክንያቱም እንደ ሀገር ቴክኖሎጂን አውቀን እና አፍልቀን ስንጠቀም፤ ቴክኖሎጂን ባለመጠቀማችን ምክንያት ስናጣቸውም፤ ስናባክናቸውም የነበሩ አቅሞችንና ሀብቶችን ማሰባሰብም፣ መቆጠብም ያስችለናል።
ለምሳሌ፣ የ “ፋይዳ” ብሔራዊ መታወቂያ በዲጂታል መልኩ መቅረቡ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ነው። ይሄም በአንድ በኩል ዜጎች ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ የማግኘት መብትን በቀለጠፈ መልኩ እውን የማድረግ አካሄድ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ወንጀልን የመከላከል ሂደቱን የማገዝ ብሎም በሀገር እድገት ላይ አዎንታዊ ውጤት መፍጠር ማለት ነው።
በዚህ መልኩ የተቃኙ አያሌ ተግባራት ተከናውነዋል። የፌዴራል ፖሊስ የዜጎች መረጃ ማዕከል መተግበሪያ ምርቃት መርሃ ግብር ላይም፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ከ500 በላይ ሰርቪሶች አውቶሜት ሆነዋል” ሲሉ የገለጹትም ይሄንኑ ነው።
በመሆኑም እንደ ሀገር እውን ለማድረግ የሚተጋለት ሁሉን አቀፍ ብልጽግና እንዲሳካ ካስፈለገ፤ በየተቋማት የሚካሄዱ ተግባራት ሁሉ በዲጂታል ሥርዓት ሊታገዙ፤ አገልግሎቶች ሊዘምኑ ይገባል። ለዚህ ደግሞ እንደ ሀገር ያለንን ሁሉን አቀፍ አቅም ጭምር ለይቶ መጠቀም ይገባል። ምክንያቱም የበለጸገች ሀገርን እውን የማድረጉ ሂደትም፣ ፍጻሜም በልኩ ያደገ ቴክኖሎጂን ይፈልጋልና!
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም