ሀሳብን እንዴት መሰብሰብ ይቻላል?

አንዳንድ ግዜ ብዙዎቻችን ‹‹ሀሳቤን መሰብሰብ አልቻልኩም፣ አንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ አቃተኝ፣ ከቀልቤ አይደለሁም›› ስንል እንደመጣለን:: የሃሳብ መበታተንና አንድ ቦታ አለመሆን የብዙዎች ችግር ነው:: ይህ ችግር ሰዎችን በእምነት ቦታ፣ በሥራ ቦታና ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ሊገጥማቸው ይችላል:: አልፎ አልፎ ሰዎች ማታ በሚያመሹበት ሰዓት ላይ ሀሳባቸው ተበትኖ እንቅልፍም እስከማጣት የሚደርሱበት ሁኔታ ይፈጠራል:: ለመሆኑ የሃሳብ መበታተን የብዙ ሰዎች ችግር ነው ወይስ የጥቂቶች ብቻ?

ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከመስጠት በፊት ሃሳብና አዕምሮ ምን እንደሆኑ መረዳት ያስፈልጋል:: ሃሳብና አዕምሮ እንደማግኔትና ብረት ወይም እንደማግኔትና ማግኔት ናቸው:: ይሳሳባሉም፤ ይገፋፋሉም:: ይጠፋፋሉም፤ ይለማማሉም:: ለምሳሌ ሀሳብና የሌለው አዕምሮ ምንም ጥቅም ሊሰጥ አይችልም:: ሶፍትዌር እንደሌለው ኮምፒዩተር ሊቆጠር ይችላል:: ምክንያቱም አዕምሮ የፈጠረው ሀሳብን ለመቀበል፣ ለመረዳት፣ ለማስፋት፣ ለመጠቀም፣ ለመቀነስ፣ ለመጨረስ… ወዘተ ለተለያዩ በሃሳብ ላይ የበላይ እንድንሆን የተሰጠን የማንነታችን ክፍል ነው::

በሌላ በኩል ሀሳብ ደግሞ የራሱ ዓለም ያለው፤ ምን አልባት ከዚህ ከቁሱ ዓለም ጋር በተጓዳኝ የሚኖር አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የራሱ ዓለም አለው ብለው የሚያስቡት ነው:: በርግጥ ሌሎች ሰዎች አዕምሯችን የሚፈጥረው ነገር ነው እንጂ አዕምሮ በሌለበት ቦታ ሀሳብ የለም ብለው ያስባሉ:: በሌላ አቅጣጫ ደግሞ አይ አዕምሮ ባይኖርም የሃሳብ ዓለም ሁልግዜ ይኖራል:: ለምሳሌ ዓይናችን ስላለ አይደለም ብርሃን የኖረው:: ብርሃን አለ ግን ዓይናችን ባይኖር ብርሃንን አንረዳም የሚሉም አሉ:: እኛ ጆሮ ስላለን አይደለም ድምፅ የተፈጠረው:: ድምፅም እንደብርሃን ጉልበት ሆኖ ይኖራል ግን በጣም የተወሰነውን የድምፅ መጠን ነው የሚሰማው የሚሉም አልጠፉም::

እንደውም አንዳንድ የሳይንስ ሊኂቃን ‹‹ከ20 እስከ 20 ሺ ኸርዝ ነው የሰው ልጅ ሊሰማ የሚችለው ድምፅ፤ የማይሰማቸው ድምፆች ይበዛሉ›› ይላሉ:: ለዚህም ሬዲዮን፣ ቴሌቪዥን፣ ስልክና ሌሎችንም የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን ፋብሪካዎች የሰው ልጅ መስማት በሚችለው ልክ ቀይረው ወደ ገበያ የሚያወጡት:: በተመሳሳይም ብርሃንን በተመለከተም የሰው ልጅ የማያያቸው በርካታ ብርሃኖች እንዳሉ በሳይንስ ሊኂቃኑ ይነገራል:: ለምሳሌ በጨለማ ግዜ ሰዎች የሚያዩበት መነፅርና ሌሎችም አይነት መነፅሮች አሉ:: ዓይናችንን ሊያጠፉ የሚችሉ ብርሃኖችም በብዛትም በአይነትም አሉ::

ስለዚህ ይህን ሁሉ ለማለት የተፈለገው ሃሳብ የእኛን አዕምሮ የሚፈጥረው ወይም የሚፈበርከው ሳይሆን ከእኛ አዕምሮ ውጪ ያለ ነገር ነው:: ነገር ግን እኛ አዕምሮ ያለንና ማሰብ የምንችል ፍጡራን እንደመሆናችን ለቁሱ ዓለም በመንካት፣ በመቅመስ፣ በመዳሰስ፣ በማሽተትና በተለያዩ መንገዶች በአካላችን ግንኙነት እንፈጥራለን:: በተለያዩ መንገዶች ከቁሱ ዓለም ጋር ግንኙነት ፈጥረን የቁሱን ዓለም እውንነት እንረዳለን:: እኛ ስላለን የቁሱ ዓለም ይኖራልን ብለን አናስብም:: እኛ ብንሞትም ይቀጥላል:: እሱን እንዴት እናውቃለን ካላችሁ ብዙ ከእኛም በፊት የነበሩ ሰዎች ሞተው የቁስ ዓለም ቀጥሏል::

ልክ እንደዚሁ የሀሳብ ዓለምም ነዋሪ፣ ዘላቂና ቀጣይ ነው:: ማንም ሰው ሀሳብ እኔ ላይ ብቻ ነው የሚመሠረተው ማለት አይችልም:: ከዚህ አንፃር ወደዋናው ነጥብ ሲመጣ ይህ በሀሳብ መበታተን፣ በሃሰብ መጥፋት፣ ሀሳብ ውስጥ ገብቶ ጭልጥ ማለት ወይም ደግሞ ከአንድ በላይ ሀሳቦች በአዕምሯችን ላይ መመላለስ አልያም በሆነ ሃሳብ ላይ መሽከርከሩ የመሳሰሉት ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዴት ይመጣሉ? በምን መልኩስ እንከላከላቸዋለን? የሚሉትን ጥቄዎች መመለስ ያስፈልጋል::

እንግዲህ የመጀመሪያው የአዕምሯችንና ሃሳባችንን ተፈጥሮ መረዳት ያስፈልጋል:: እኛ በአብዛኛው ቁጥጥር ያለን ሃሳባችን ላይ ሳይሆን አዕምሯችን ላይ ነው:: ስለዚህ በአብዛኛው አዕምሯችን ላይ በምንሠራቸው ሥራዎች ነው ሀሳብን ልንገዛ፣ ልንመራ ወይም ልንጠቀምበትና በሃሳብ ብዙ ሳንናወጥ ለመኖር የምንችለው:: ወደአዕምሯችን ስንመጣ ደግሞ አዕምሯችን ሁለት አይነት ክፍሎች ይኖሩታል:: አንደኛው የአካላችን ክፍል የሆነው አንጎላችን ነው:: አንጎል ራስ ቅላችን ውስጥ ያለው ሁለት ኪሎ የሚጠጋ በመጠኑ ትንሽ የሆነ 2 ከመቶ ክብደት ያለው የሰውነታችን ክፍል ነው::

አንጎል የነርቭ ሴሎች ክምችት ነው:: ወደ 30 ቢሊዮን የሚሆኑ ሴሎች አሉት:: በኬሚካልና በኤሌክትሪካል ‹‹ኢምፐልስ›› የሚግባባ በጣም የረቀቅ የሰውነት ክፍልም ነው አንጎል:: የአንድ ሕፃን ልጅን አንጎል ወደ ኮምፒዩተር ለመቀየር ቢታሰብ ሦስት ፎቅ ኮምፒዩተር ያስፈልጋል:: ስለዚህ አንጎል በትንሽ ቦታ ላይ የተሰበሰብ ትልቅ ኃይል ያለውና በርካታ ነገሮችን መሥራት የሚችል የሰውነት ክፍል እንደሆነ ይነገራል:: ስለዚህ በዚህ አንጎላችን ላይ ባለው ሁኔታ ሃሳብ ይመሠረታል::

በሌላ በኩል ግን ይህ አንጎል ልክ እንደ ኮምፒዩተር ‹‹ሀርድዌር›› ነው:: ስንፈጠር ቋንቋ የለውም:: ነገር ግን ቋንቋ የመማር ብቃት አለው:: ሌሎች ነገሮችም እያደጉና እየሰፉ የሚመጡት ከዛ በኋላ ነው:: በዚህ በአንጎል ላይ ደግሞ አዕምሮ የሚባል አካል አለ:: አዕምሮ ደግሞ ሃሳብን ከመረዳት፣ ከመሳል ጀምሮ ሃሳብን በአመክንዮ እስከማብላላት፣ እውቀት እስከማከማቸት፣ ጥበብ እስከማዳበር፣ አመለካከትና መነሳሳትን እስከመፍጠርና ሌሎችንም የተለያዩ ሥራዎችን የሚያከናውን በአንጎላችን ላይ የሚገኝ፤ ከአንጎልም በላይ የረቀቀ የማንነት ክፍል ነው::

ይህ አንድ እይታ ቢሆንም ታዲያ አንዳንድ ሰዎች በሰውነት ውስጥ ያለው አንጎል ብቻ ነው:: አንጎል ራሱን የሚገልፅበት መንገድ ‹‹ማይንድ›› ይባላል:: ስለዚህ ማይንድ ሥራዎችን አከናዋኝ እንጂ ራሱን የቻለ ነገር አይደለም ብለው ይከራከራሉ:: ሌሎች በእምነት ረድፍ ውስጥ ያሉ ደግሞ አንጎል እኮ ስንሞት እንደሌሎቹ የሰውነት ክፍሎች ማለትም ጉበት፣ ጨጓራና ሳምባ ጋር የሚበሰብስ ነው:: ግን አዕምሮን አይሞትም:: ወደ ቀጣዩ ዓለም ስንሄድ አንጎላችንን እንጂ አዕምሯችንን ጥለን አንሄድም ብለው ያምናሉ:: በየትኛውም ጎራ ሆኖ ግን እነዚህን ነገሮች አለማሰብ አይቻልም::

ስለዚህ እግራችንን መራመድ፣ በአንደበታችን መናገር፣ እጆቻችን ለመፃፍ እንደምናስተምረው አንጎላችንን ካላሠለጠነው በቀላሉ በሃሳብ የሚነዳ የሃሳብ መጫወቻ ይሆናል:: አዕምራችን ወይም አንጎላችን ከሀሳብ በላይ እንዲሆን ሥልጠና ይፈልጋል:: ማሰብና በሀሳብ ጭልጥ ብሎ መሄድ ይለያያል:: በሀሳብ አዕምሯችን ተወጥሮ ወይም ተሽከርክሮ ምንም ነገር ሳያመርት ከቆየ እያሰብን ነው ማለት አንችልም:: ማሰብ ዲስፕሊን ነው:: አንድ ሰው ስለደከመው ሠርቷል እንደማይባለው ሁሉ አንድ ሰው በሀሳብ ስለተናወጠ አስቧል አይባልም::

ሁለት አማራጭ ግን አለ:: ወይ ሀሳቡን እኛ ገዝተን ከገባው ከገባው ሃሳብ ተቀነባብሮ የሚወጣው ሀሳብ የተሻለና የሚጠቅም መሆን ማሰብ ነው:: ከዛ ውጪ ግን ሃሳቡ ሲገባና ሲወጣ ምንም ለውጥ የሌለው፣ በመሐል እኛን ካደከመን ባዶ ድካም ነው የሚሆነው:: ለምሳሌ አንድ ሰው ምግብ ሲበላ ምግቡን ከበላ በኋላ ከአፍ ጀምሮ እየተብላላ ወደጨጓራ ሄዶ የተወሰነው ወደሰውነት ገብቶ በመፈጨት ሂደት ውስጥ ይቀጥላል:: መጨረሻ ላይ አብዛኛው ምግብ በተለይ ፕሮቲንና ቅባት ያለባቸው ጠንከር ያሉ ምግቦች ለመፈጨት እስከአንጀት ድረስ መሄድ አለባቸው:: ምግቡን ለመፍጨት ጉበት፣ ቆሽትና አንጀት በራሱ የሚያመነጯቸው ብዙ ኢንዛይሞች አሉ:: እነዛ ተጠረቃቅመው መጨረሻ ላይ ትንሹ አንጀት መጨረሻ አካባቢ ሲደርሱ ፋቱ ወደ ፋቲ አሲድ፣ ፕሮቲኑ ወደ አሚኖ አሲድ፣ ካርቦኃይድሬቱም ወደ ግሉኮስ እየተቀየረ ወደ ሰውነታችን ውስጥ ይገባል:: ከዛ ቀሪው የሚወጣ ነው:: እሱ ደግሞ ወደ ትልቁ አንጀት ከሄደ በኋላ የሚጣለው ከመጣሉ በፊት ውሃ ይፈልጋል:: ስለዚህ መጨረሻ ላይ ውሃውን ሰውነት ወስዶ የቀረው ይወጣል::

እንግዲህ ይህ ሂደት በጣም ረጅም ነው:: ብዙ የሰውነት አካላት ተሳትፈውበት ነው እውን የሚሆነው:: አንጎላችንም ብዙ ክፍሎች አሉት:: ስለዚህ አንድ ሀሳብ ወደ አዕምሯችን ሲመጣ እንደ አንድ ሊበላ እንደተዘጋጀ ምግብ መሆኑን ማሰብ አለብን:: አንጎላችን ሃሳብን ማብላላት ካልቻለ ለምሳሌ አንድ የሦስት ወር ሕፃን ክትፎ ቢበላ አሚኖ አሲድ ማውጣት አይችልም እንደማለት ነው:: ይታመማል:: ተቅማጥ፣ ትውከትና ቁርጠት ያመዋል::

ስለዚህ ሃሳብም በመጀመሪያ ደረጃ ወደ አዕምሯችን የምናስገባውን ሀሳብ ነው መቆጣጠር ያለብን:: ከገባ በኋላ ልክ እንደማይስማማ ምግብ አዕምሯችን ላይ ብዙ ነገሮች ይፈጥራል:: የፈለግነውን ቪዲዮ እያየን፣ የፈለግነውን መጽሐፍ እያነበብን፣ ስናወራ እየዋልን አዕምሮዬ እምቢ አለኝ ልንል አንችልም:: ስለዚህ ሀሳብ ሃሳብን ለመሰብሰብ የመጀመሪያው ምክር የሚሆነው ወደ አዕምሮ የሚገቡ ሀሳቦችን መቆጣጠር ነው::

ብዙ ሰው ወደ አዕምሮው ምን እንደሚገባ አይቆጣጠርም:: ዝምብሎ በጆሮው፣ በዓይኑ፣ በተለያየ መንገድ የፈለገው ነገር ከገባ በኋላ አዕምሮው ሲያቅተው አዕምሮዬ ሀሳብን መቆጣጠር አቃተው ይላል:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ወደ አዕምሯችን የምናስገባቸውን ሀሳቦች መልክ መልክ ማስያዝ ያስፈልጋል:: ለምሳሌ ትምህርት ከሆነ በአቅማችን መማር አለብን:: በቂ እንቅልፍ ያስፈልገናል:: መርዛማና እንደ አልኮል የመሳሰሉ ነገሮችን መውሰድ የለብንም:: አዕምሯችንን ይበልጥ ከሚያጨናንቁና እንደ ኢንተርኔትና ሌሎችም ጌሞች ማራቅ ይኖርብናል::

በሌላ በኩል ደግሞ አዕምሯችን ራሱን እንዲገዛ ሳይሆን የምናስበውን ነገር ወረቀትና እስክርቢቶ ይዘን ማስፈር አለብን:: ለምሳሌ አንዳንድ ግዜ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የምናስበውን ሀሳብ ፅፎ ወደ ቁምነገር መቀየርና የመሳሰሉት ነገሮች የተበታተነ ሃሳብን ቦታ ለማስያዝ ይረዳሉ:: ከዚህ ውጪ ያልተፈቱ ጉዳዮች በተለይ ስሜት አዘል ሀሳቦች አዕምሮን በጣም የመቆጣጠር ኃይል አላቸው:: ቁጣ፣ ኅዘን፣ ፍርሃትና የመሳሰሉት ሌሎች ስሜት አዘል ሃሳቦችና ከግንኙነታችን ጋር ያልተፈቱ ግጭቶች፣ ስጋቶች፣ ያልተሠሩ ሥራዎች ካሉ ማወራረድና ማስተካከል ያስፈልጋል::

ከዚህ ባለፈ መንፈሳዊ ድጋፍም ስለሚያስፈልግ መንፈሳዊ መጽሐፍቶችን ማንበብ፣ ፀሎት ማድረግ አዕምሮን የማረጋጋት ባሕሪይ አለው:: ከሰዎች ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገርና አዕምሮን ትኩረት ሰጪ በሆኑ ነገሮች ላይ ማድረግን መማርም ጠቃሚና የተበታተነ ሃሳብን ወደ አንድ ለማምጣት የሚያግዝ መንገድ ነው:: አዕምሯችን ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት ነገሩን ማስቆም የሚቻልበት የተወሰነ ግዜ ይኖራል::

እንደዚህ አይነት በሀሳብ ጭልጥ ብሎ የመሄድና የሃሳብ መበታተን ችግርን በቶሎ ካላስቆምነው ብዙ ከሄደ በኋላ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ይሆናል:: ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት ለማስቆም ጥረት ማድረግም ያስፈልጋል:: ዋናው ነገር ግን አዕምሮን ቀስ እያሉ እያስተማሩ ወደሚፈለግበት ሁኔታ መመለስ ነው:: እንደድባቴና ሌሎች የአዕምሮ ችግሮች ከሆኑ ግን የጤና ባለሙያዎችን ማማከር ያስፈልጋል:: ያልተፈቱና ምክር የሚፈልጉ ጉዳዮች ካሉ ደግሞ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችን ቀርቦ ማማከር የግድ ይላል::

ከዛ በተረፈ በቂ እንቅልፍ አለመተኛት፣ ድካምና ሌሎችም ያልተዘጉ የሕይወት መዝገቦችም ለሃሳብ በመበታተንና በአንድ ሃሳብ ላይ ላለመፅናት ምክንያት ሊሆኑ ስለሚችሉና አሁን ያለንበት ዘመንም በጣም አዕምሮን የሚደበድብ ከመሆኑ አኳያ ለብቻ ሆኖ የጥሞናና የአርምሞ ግዜ መውሰድም ሌላኛው አማራጭ ነው:: የተወሰነ ግዜ ለብቻ መሆንም አዕምሮን ለማረጋጋት እድል ይሰጣል::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You