‹‹ለሀገራችን ከምክክር የተሻለ አማራጭ የለም››- አቶ እውነቱ አለነ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ

የፖለቲካ ቁርጠኝነት ከሚታይባቸው ነገሮች መካከል የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ አንዱ ነው:: ለግንባታው ደግሞ ነፃና ገለልተኛ እንዲሁም ጠንካራ ተቋማት መገንባት የሚጠይቅ ተግባር መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ መንግሥት በአሁኑ ወቅት በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ያለ ከመሆኑም በላይ የዴሞክራሲ ሥርዓቱ መገለጫ የሆኑ ተቋማትንም በማደራጀት በኩል ሰፊ ኃላፊነትን ወስዶ እየሠራም ይገኛል::

ለአብነት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት የሆኑ ሕጎች እንዲሻሻሉ የማድረግ፤ የሚዲያ ተቋማት ሥራዎቻቸውን በአግባቡ መሥራት እንዲችሉ በተቻለ መጠን ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሠላማዊ መንገድ በመታገል ለሕዝብ አማራጭ ሃሳብን እንዲያቀርቡ የማድረግ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን ከምንም በላይ ደግሞ እንደ ሀገር ባለያዩን ጉዳዮች ላይ የጋራ አረዳድና ግንዛቤ እንድንይዝ ብሎም እንደ አገር ተመካክረን ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ እንድንፈታ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው::

የአገሪቱ ዜጎች ብሔርና ብሔረሰቦች፡ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሚዲያ አካላት፣ መንግሥት እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ተንቀሳቅሰው ተመካክረውና በችግሮቻቸው ላይ የጋራ መግባባትን ይዘው መንቀሳቀስ እንዲችሉም ከዴሞክራሲ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሙ ላለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

የዴሞክራሲ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በፖለቲካና በሃሳብ መሪዎች መካከል በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነትና አለመግባባት ከመፍታት ጎን ለጎን ሰፋፊ ሀገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የራሱን ጥረትም እያደረገ ነው::

አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን ማድረግ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ይፈጥራል ብሎ ያመነው ኮሚሽኑ በሂደትም የመተማመንና ተቀራርቦ የመሥራት ባሕልን ለማጎልበት እና የተሸረሸሩ ማኅበራዊ እሴቶችን ለማደስ ጠቀሜታው የጎላ ነው:: ይህ ጥቅሙም ስለታመነበት ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ በተሳለጠ ሁኔታ ይካሄድ ዘንድ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት እንዲሁም ነፃና ገለልተኝነቱ ተረጋግጦለት በመንቀሳቀስ ላይ ነው::

በ2017 ዓም በሀገራችን እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየትን ራዕዩ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ኮሚሽኑ ለተፈጠሩት ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና ሕዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ ተግባራዊነቱንም መከታተያ መንገድ በመዘርጋት አመርቂ ውጤት ለማምጣትም እየሠራ ይገኛል ::

እኛም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ እውነቱ አለነን ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ምን አከናወነ? ምንስ ይቀረዋል? በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ::

አዲስ ዘመን ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ ካሉ የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል አንዱ ነውና የሥራ ሂደቱን እንዴት ይገልጹታል?

አቶ እውነቱ፦ በሀገራችን በርካታ የተግባባንባቸው አብረው እያኖሩን ያሉ ጉዳዮች ቢኖሩም በዛው ልክ ደግሞ ያልተግባባንባቸውም ጉዳዮች ብዙ ናቸው:: በዚህ ምክንያት ደግሞ እዚህም እዚያም በርካታ ግጭቶችና አለመግባባቶችን እያስተናገድን ነው:: እነዚህ ነገሮች ደግሞ ተከማችተው በሄዱ ቁጥር እንደ ሀገርና ሕዝብ አደጋ ላይ የሚጥሉን ናቸው::

በመሆኑም ይህችን ታላቅ ሀገርና ሕዝብ ወዳልተገባ ሁኔታ የሚወስዱ ነገሮችን እንመርምር፤ በማያግባቡን ነገሮች ላይ ሥራዎችን እንሥራ፤ እንመካከር በማለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ትን በማውጣት ወደ ሥራ ገብቷል:: በዚህ ሂደትም ኮሚሽኑ እስከ አሁን ድረስ የቅድመ ዝግጅት ወሳኝ የሆኑ ሥራዎችን ሠርቷል::

በእነዚህ የሥራ ሂደቶቹ ውስጥ ደግሞ በርካታ ፈተናዎችም አጋጥመውታል:: ይህም ቢሆን ግን የዴሞክራሲ ተቋማት የሚገጥሟቸው ችግሮች ብዙ በመሆናቸው ችግሮችን እንደ አመጣጣቸው እያለፈ ሁሉንም አካታችና አሳታፊ የሚያደርጉ ሥራዎችንም በመሥራት በኩል ብዙ ርቀቶችን ተጉዟል:: ለእኔም የሚሰማኝ ይህ ሥራው ወደፊት ሀገራችን ላይ የሚመጣው ለውጥና አንድነት ከፍ ያለ መሆኑ ነው::

በሌላ በኩልም የኮሚሽኑ ሥራ ብዙ ብሎም ከጫፍ እስከ ጫፍ ተጉዞ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል አጠቃሎ መሥራትን የሚጠይቅ ነው:: ኮሚሽኑ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ተቋቁሞ በአስር ክልሎች የተሳታፊና የተባባሪ አካላት ምርጫ አካሂዷል:: ሥልጠና ሰጥቷል:: እነዚህ ሥራዎች በተጠናቀቁባቸው ክልሎች ደግሞ አጀንዳ የመቅረጽ በተቀረጹት አጀንዳዎች ላይም ምክክር አድርጎ የመቋጨት ሥራም ይኖራል::

በሌላ በኩልም በቅርቡ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ ከግንቦት 21 ጀምሮ እስከ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ አጀንዳ ማሰባሰብ ይካሄዳል:: ይህ ሂደት ደግሞ በርካታ ልምዶች የሚቀመሩበት ለሠላምና እርቅ የተመረጠው ዘዴ ትክክል መሆን አለመሆኑ የሚታይበትና የሚቃኝበት ነው:: ከሞላ ጎደል ሁሉም ሃሳብ አለኝ የሚል የኅብረተሰብ ክፍል ሃሳቡን ያለምንም ገደብ የሚሰጥበትና በመደማመጥ ጉዳዮች እልባት የሚያገኙበት ይሆናል ተብሎ ይታሰባል:: ይህ ሁኔታ ደግሞ በቀጣይ ወደ ሌሎች ክልሎችም እንዲሰፋ የሚደረግ ነው::

በተለይም ወደሌሎች ክልሎች ተሞክሮውን የማስፋት ወይም ሥራን የመሥራት ሂደቱ ሲካሄድ የፀጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችም ከሞላ ጎደል መንግሥትም ጣልቃ ገብቶ በአካባቢው ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ችግሩን እንፈታለን ብለው የተነሱትም ኃይሎችም ችግራቸውን በውይይት ለመፍታት መሞከር አለባቸው:: ከዛ ውጪ ያለው ነገር የአሸናፊነትና የተሸናፊነት ጉዳይን ያመጣል ይሆናል እንጂ ዘላቂ መፍትሔን የሚያመጣ አይደለም ብለው በማሰብ ወደምክክር ዓውዱ ቢመጡ ጥሩ ነው::

ምክንያቱም እድሜ ልካችንን አንዱ ችግር እፈታለሁ ሌላ ደግሞ ሌላ ችግር እፈታለሁ እያለ በተነሳ ቁጥር ከላይ እንዳልኩት አሸናፊና ተሸናፊ ይፈጠር ይሆናል እንጂ እንደ ሀገር አንድ ሆኖ መኖር ብሎም ዘላቂነት ያለው የሠላም አየር መተንፈስ የማይታሰብ ይሆናል:: በመሆኑም የጊዜ ጉዳይ ይሆንና ዛሬ አንዱ ነገ ደግሞ ሌላው እያሸነፈ በግጭት አዙሪት ውስጥ ከመቆየት ያለፈ ነገር ካለመኖሩም ባሻገር ተግባሩም ሀገራችንን የሚመጥን አይደለም::

በመሆኑም የጀመርነው ሂደት ሌላ አማራጭ እንኳን ቢኖረንም ከምክክር የተሻለ ግን ሊሆን አይችልም::  በመሆኑም በምክክር ችግሮቻችንን መፍታት መጠቅለል አስፈላጊ ነው::

አዲስ ዘመን፦ አለመግባባቶቻችንንና ችግሮቻችንን በሀገራዊ ምክክር መፍታት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ይወስደናል ሲባል ምን ማለት ይሆን ?

አቶ እውነቱ ፦ አለመግባባቶችን በሀገራዊ ምክክር በመፍታት ወደ ተሻለ ምዕራፍ መጓዝ አለብን ማለት እንግዲህ ሂደቱ ሁሉን ያማከለ፣ ግልፅና ውጤታማ መሆን አለበት ማለት ሲሆን ሁሉም አካላት የበኩላቸውን የሚሳተፉበትም ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው።

በሌላ በኩል አሁንም ይሁን ከአሁን በፊት በነበሩት ጊዜያት እንዲሁም ወደፊት ያላግባቡንን የማያግባቡንን ነገሮች እልባት እየሰጠን መስመር እያስያዝን ሄድን ማለት ነው:: እንዲሁም እነዚህን አለመግባባቶቻችንን በውይይት ከፈታን በኋላ ወደቀጣይ ምዕራፍም ለመሸጋገር ድልድይ እናገኛለን፤ ለምሳሌ ሕዝበ ውሳኔ የሚጠይቁ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፍን መፍጠርም ሊያስፈልግ ይችላል፤ ተቋማት እንዲዋቀሩም የሚጠይቁ ሥራዎች ይኖራሉ::

ዋናው ግን ምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመበትንና ያስፈለገበትን ነገር መጀመሪያ ማጠናቀቅ ቀጥሎም ቀጣይ ሥራዎችን በመሥራት ሀገራችን ተጨማሪ ፈተና እንዳይኖርባት ማድረግ ስለሚጠቅም ሂደቱን ችግር ፈቺ አድርጎ መመልከቱ ይጠቅማል::

አዲስ ዘመን፦ እንደ አገርና ሕዝብ በኮሚሽኑ አመሠራረትና የሥራ ሂደት ላይ ያለውን አረዳድ እርስዎ እንዴት ያዩታል?

አቶ እውነቱ፦ የምክክር ጉዳይ አሁን ከለውጡ ጋር የመጣ አጀንዳ አይደለም፤ ከዛም በፊትም ሲነሳ ሲጠየቅ የነበረ ጥያቄ ነው:: ሁላችንም እንደምናስታውሰው ከለውጡ በፊት ብሔራዊ ምክክር እናድርግ የሚሉ ድምፆች በተደጋጋሚ ይሰሙ ነበር:: ይህንን ጥያቄ ደግሞ በወቅቱ የነበረው መንግሥትም ሆነ ፓርቲ መመለስ ተስኖት ቆይቷል:: ከዛ ይልቅ ጥያቄዎችን በሌላ መንገድ የመመለስ አዝማሚያዎችም ታይተዋል:: ግን ደግሞ ይህ ያልተገባ አካሄድ ምን ዓይነት ውጤትን እንዳመጣም አይተናል::

ነገር ግን ከለውጡ በኋላ ሌሎች በርካታ አንገብጋቢ ችግሮች ቢኖሩብንም ቅድሚያ ለሀገራዊ ምክክርና መግባባት እንስጥ በሚል ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደተቋቋመ ይህንን አዋጅ አውጥቶ ነው ወደ ሥራ ያስገባው::

እውነት ለመናገር ሂደቱ አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እንደሚፈቅደው ከሆነ ኮሚሽነሮችን መሾም የነበረበት ጠቅላይ ሚኒስትሩና አስፈጻሚው አካል ነው፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከፍ ያለ መግባባትን የሚጠይቅና ገለልተኝነትንም የሚፈልግ ስለሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ራሱ ኮሚሽነሮችን እንዲመለምልና እንዲመርጥ ዕድል የሰጠ ዓውድ ነበረው::

ይህ በጣም ተገቢነት ነበረው:: ምክንያቱም አስፈጻሚው አካል ሁልጊዜም በተገባም ባልተገባም መንገድ ተፅዕኖ ያደርጋል የሚሉ ድምፆች ስላሉ እነዚህን ለመቀነስ በተቻለ መጠን ጥቆማ አለኝ የሚል የኅብረተሰብ ክፍል ጥቆማ ሰጥቶበት በርካታ ተጠቋሚዎች ቀርበው ከፍተኛ የሆነ የማጥራት ሥራ ከተሠራ በኋላ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን 11 ኮሚሽነሮች ለመሾም ችለናል::

ኮሚሽነሮቹን ቀረብ ብሎ ላያቸው በእውቀትም፤ በልምድም፤ በእድሜም ከፍ ያሉ ሰዎች ናቸው:: አንዳንዶቹ እንደውም ተጨማሪ ጥረት ውስጥ ያሉ ለሀገሬ ምን ላበርክት ብለው ወደ ሥራው የገቡ ናቸው እንጂ በእድሜ ዘመናቸው ሊያከናውኑት የሚገባውን ሥራ አከናውነው አሁን በማረፊያ ጊዜያቸው ላይ የነበሩ ናቸው:: ነገር ግን መንግሥትና ሕዝብ በዚህ መልኩ ኃላፊነት ከሰጠን እንወጣለን በሚል ያለፉትን ሁለትና ከዚያ በላይ ዓመታት ያለዕረፍት እየሠሩ ነው::

ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በሁሉም አስቸጋሪ በሚባሉ ክልሎችና ወረዳዎች ሳይቀር ገብተው የኅብረተሰቡን የልብ ትርታ ቢሆን ብለው የሚመኙትን ነገር ለማዳመጥ እንዲሁም ምክክሩ እንዴት ጤነኛ በሆነ መንገድ መሄድ እንዳለበት የሕግ ማዕቀፍም የአሠራር ሥርዓትም ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል::

እስከ አሁን ተቋም እንዳንገነባ አድርጎን የቆየው ችግራችን የሆኑ እንከኖች ስህተቶች ተፈላልገው ሂደቱን ማጠልሸት ነው:: ይህ ሁኔታ ደግሞ የተቋም ግንባታ ሂደታችንን ይጎዳዋል ያበላሸዋልም:: ተቋም እንፍጠር፤ እንገንባ፤ በተቋማት ላይ እምነት እናሳድር ተቋማት ጉድለት ሲያሳዩ ደግሞ ያለ ርህራሄ እናርማቸው የሚለውን ብንይዝ መልካም ነው::

አይ ብለን ግን የተሞካከሩ የተጀመሩ ነገሮችን ማጠልሸት ገና ከጅምሩ እንዲህ ሊሆን ስለተፈለገ ነው ብሎ አለመሳተፍ ችግር እንጂ መፍትሔን አያመጣም:: ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ተቋማቱ ገና ወደ ሥራ ሲገቡ ችግሮቻቸውን እያነሱ በር የሚዘጉ ተቃዋሚዎች እንዳሉም ስለማውቅ ነው:: በዚህ እሳቤያቸው ደግሞ እስከ አሁንም ወደሂደቱ ያልገቡ አሉ:: ለእነሱም ለሚደግፋቸው ሕዝብም የሚጠቅመው ግን ገብተው የሂደቱ አካል ሆነው እየተመካከሩ ሃሳባቸውን ማስቀመጡ ነው ::

አዲስ ዘመን፦ የምክክር ኮሚሽኑን ነፃና ገለልተኝነት እንዴት ይለኩታል ?

አቶ እውነቱ ፦ የምክክር ኮሚሽን ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መሄዱ መንግሥት በምንም ተዓምር መጋፋት ያለበት ነገር አይደለም:: ምክር ቤቱም በሕግ የተሰጠው ሥልጣን አለ፤ በዚህ በወጣው ሕግ መሠረት ሥራዎች መከናወናቸውን የመገምገምና ግብረ መልስ የመስጠትም ኃላፊነትም አለበት:: እንደ ምክር ቤት በእኛ በኩል ሕግ በሰጠን ኃላፊነት መሠረት የክትትል ሥራ እንሠራለን፤ ኮሚሽኑ እስከ አሁን የሄደበት ሂደት ምን መልክ አለው? ባቀደው ልክ እየሠራ ነወይ? ካልሠራስ ምክንያቱ ምንድን ነው? የሚለውን ተከታትለን ግብዓት የመጨመር ነገር ሕጉም ስለሚፈቅድለን እናደርጋለን:: ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅም በሕግም የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ስለሆነ ያደርጋል:: ነገር ግን ከዚህ አልፎ ሌሎች ሂደቶችን የማመሰቃቀል፣ እኔ በምፈልገው መንገድ ይሂድ የማለት ነገር ግን የለም:: እንዲህ እናድርግ ብንል ደግሞ የሚከሰተው ውድመት ከባድ እንደሆነ ስለምንገነዘብ ኮሚሽኑም በሕግ በተሰጠው ሥልጣን ልክ እንዲሠራ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም እንዲሁ በልኩ እንዲንቀሳቀስ የማድረግ ሥራ ነው እየተሠራ ያለው::

አዲስ ዘመን፦ የምክክር ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን ይወጣ ዘንድ አገናኝ ድልድዩ ሚዲያ ነውና ሚዲያው በዛ ልክ ተንቀሳቅሷል ማለት ይቻላል?

አቶ እውነቱ፦ እንዲህ ዓይነት ሥራ ጀምሮ ለማጠናቀቅ የሚዲያ ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: ምክንያቱም ኮሚሽኑ የሚሠራቸው ሥራዎች አሳታፊ፣ አካታች መሆን አለባቸው፤ እንዲህ ለማድረግ ደግሞ የግንኙነት መስመሩ ያለው ሚዲያው እጅ ላይ ነው:: በመሆኑም እስከ አሁን የተሠራው ሥራ እንዳለ ሆኖ አሁንም ዓላማው ከግብ እስኪያደርስ ድረስ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው:: እስከ አሁን ባለው ሂደት የመንግሥት እና የግል ማኅበራዊ ሚዲያው እንዲሁም ባሕላዊ ሚዲያ እየተባሉ የሚጠሩት ሁሉ የኮሚሽኑን ሥራ ሕዝብ ዘንድ ለማድረስ ሰፋፊ ጥረቶችን አድርገዋል:: በተለይም ሥራዎችን በደንብ በእቅድ ይዘው በመሥራት ዶክመንተሪዎችን በማዘጋጀት ምክክሩ በኅብረተሰቡ ውስጥ የተሻለ ግንዛቤ እንዲያዝበት በማድረግ በኩል ክፍተቶች እንዳሉ ደግሞ እንገነዘባለን::

አሁን ላይ ከምክክር በላይ ለሚዲያና ለሕዝብ አጀንዳ ሊሆን የሚችል ነገር የለም፤ በመሆኑም ሁሉም ሚዲያዎች የሚሠሯቸው ሥራዎች ድባባቸው ራሱ ምክክር እየተደረገበት ያለ ሀገር ላይ እንዳለን እንዲሰማን ማድረግ ይገባል::

በጥቅምት ወር አካባቢ የተቋቋመ የሚዲያ ፎረምም አለ፤ እሱም በራሱ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ እየተመራ እቅድ የሚያዘጋጅበት ሥራዎችን የሚሠራበት የሚዲያ አካላቱም እኔ ቀረሁ ሳይሉ በሙሉ የሚሳተፉበት ሊሆን ይገባል::

በዚህ አጋጣሚ ማመስገን ካለብኝ የማመሰግነው ማኅበራዊ እንዲሁም የግል ሚዲያው በምክክር ኮሚሽኑ ሥራ ዙሪያ እያደረጉት ያለውን አስተዋፅዖ ነው:: አዎንታዊም አሉታዊም በሆነ መንገድ ስለ ምክከር ኮሚሽኑ በማውራታቸውና ይህ ሃሳብ ደግሞ ኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲቀር በመሆኑ በጣም ጥሩ ቢሆንም በቀጣይ ደግሞ ትኩረት ሰጥተው ቢሠሩ በርካታ ውጤቶችን እንደሀገር ማግኘት እንችላለን::

አዲስ ዘመን፦ ኮሚሽኑ ከተሰጠው የጊዜ ሰሌዳ አሁን ላይ 10 ወራት እንደቀሩት እየተነገረ ነው:: በእነዚህ ወራቶች ምን ዓይነት ተግባራት ናቸው መከወን ያለባቸው?

አቶ እውነቱ፦ ቀሪዎቹ አስር ወራት ከፍተኛ የሆነ ሥራ የሚሠራባቸው ጊዜያት ናቸው፤ እስከ አሁን የነበረው ሥራ ቢያንስ በምክክሩ የሚሳተፉ ሰዎችን የመለየት ነው:: ይህ ሂደት በራሱ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ መውረድን የሚጠይቅ በመሆኑና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደፊት ማምጣት ስለነበረብን ረዘም ያለ ጊዜን ወስዷል:: ሌላው ፓርቲዎችን ወደዚህ ምክክር ማምጣቱ በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ስለቆየ ኮሚሽኑ ሰፊ ጊዜን እንደወሰደበት ምንም ጥርጥር የለውም::

ሌላው በሀገራችን ያለው የሠላም መደፍረስ ጉዳይ ሥራው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዳይሄድ እንቅፋት ሆኗል:: እስከ አሁን በትግራይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች ሥራውን ለማከናወን ችግሮች አጋጥመዋል:: በመሆኑም በቀሩት ጊዜያት መሰል ችግሮችን መልክ አስይዞ በፍጥነት ሁሉም ክልሎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደምክክር የሚመጡበትን ሁኔታ ከፈጠርን አስር ወራት ቀሪውን ሥራ ለማከናወን ያንሳል የሚባል ጊዜ አይደለም::

ጊዜ ሊወስድ የሚችለው አማራ ክልል ያለው ችግር ነው:: ነገር ግን አሁን ሥራው ተጀምሯል:: ትግራይ ክልልም እንደዚሁ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፤ በመሆኑም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ መልክ ማስያዝ ከተቻለ በቀሪዎቹ አስር ወራት በጣም ብዙ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል ሃሳብ አለኝ::

አዲስ ዘመን ፦ኮሚሽኑ በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ እንደ ሕዝብ ተሳትፏችን ምን መምሰል አለበት ይላሉ?

አቶ እውነቱ፦ በእውነቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ፈተናዎችን አልፏል፤ እናት ልጆቿን በጦርነት አጥታለች፤ በግጭት ሀገር ብዙ አምራች ኃይሏን አጥታለች፤ ንብረታችንን አውድመናል፤ በመሆኑም በሃሳብ መለያየት ምክንያት በኅብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረው ነገር እጅግ በጣም ከባድ ነው::

የእኛ ታሪክ የጦርነት የግጭት ታሪክ ሆኖ እንዲታይ ያደረገውን አጀንዳችንን ዘግተን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ መሸጋገር አለብን:: እንደማስበው ደግሞ ይህ ምዕራፍ በጣም ወሳኝ ምዕራፍ ከመሆኑም በላይ እስከ አሁን የመጣንበትን የታሪክ ትራጀዲ እስከመቀየር የሚደርስ ሥራ ነው::

በጠቅላላው በታሪኮቻችን እየተጋጨን መቀጠል አይገባንም ፤ ከዛ ይልቅ ከታሪኮቻችን እየተማርን የነገ ሁኔታችንን ማመቻቸት ይጠበቅብናል:: በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ሁኔታ ላይ መግባባትና መስማማት ያለበት ይመስለኛል:: ችግሮቻችንን የምንፈታው በምክክርና በውይይት ነው የሚለው መደምደሚያ ላይ ካልተደረሰ በስተቀር በኃይል ማንንም መልክ ማስያዝ አይቻልም:: ይህንን አካሄድ ደግሞ ለብዙ ዓመታት ሞክረነዋል ረዘም ያለ ዓመታቶቻችንንም ከጦርነት ጋር አሳልፈናል፤ ነገር ግን ያገኘነው ውጤት የለም:: ከዛ ይልቅ ከኋላችን የተነሱ ሀገራት በሃብት በሥልጣኔ ቀድመውን እንዲሄዱ ነው የሆነው:: በመሆኑም የአባቶቻችን የሥልጣኔ ሀገርን የመውደድ ታሪክ ወደፊት ለሚመጡት ልጆቻችን ማስተላለፍ ይጠበቅብናል::

አዲስ ዘመን ፦ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ::

አቶ እውነቱ ፦ እኔም አመሰግናለሁ

እፀገነት አክሊሉ

 

አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You