ለስድስት ዓመታት የተደበቀው ቀብር

ተጋብተው አብረው መኖር የጀመሩት በ2004 ዓ.ም ነበር። በፍቅር ተሳስበው በጓደኝነት ቆይተው በመጨረሻም በሀገር ወግ ሽማግሌ ተልኮ ነበር የተጋቡት። የሚዋደዱ የሚመስሉ ባልና ሚስቶች ነበሩ። ስሞቻቸውን በቁልምጫ መጠራራት መለያቸው ነበር። ከቁልምጫ አልፎ በስም መማማል የየእለት ተግባራቸው ነው። ሲደነግጡ እንኳን ‹‹እገልዬ ድረስ፤ ድረሽ›› የሚለው ከአፋቸው አይጠፋም። መዋደዳቸውን በአደባባይ የሚያሳዩት ባልና ሚስት ቤታቸው ሲገቡ ግን በተቃራኒው ወደ ንዝንዝና ጭቅጭቅ ዓለም ይገባሉ።

በውሃ ቀጠነ ጠብ የሚቀናቸው እነዚህ ሰዎች ለመጣላትም ለመታረቅም አፍታ የማይቆዩ ዓይነት ባልና ሚስቶች ነበሩ። እሷ የቤት እመቤት እሱ ደግሞ ለፍቱ አዳሪ ቋሚ ሥራ ያልነበረው ሰው ነበር። ያገኟትን ተካፍለው በልተው በመደሰት ፈንታ መጣላት፤ ወዲያው ደግሞ ታርቆ መሳቅ የየእለት ተግባራቸው ነበር።

ባልየው ሥራ ሲወጣ ሚስቱን በጥርጣሬ ስለሚመለከት በሂደት ሥራ እርግፍ አድርጎ ወደ መተው ተቃረበ። ሥራ ወጣሁ ቢልም መለስ ብሎ ሚስቱን ሲሰልል ስለሚውል የእለት ገቢያቸው ተመናምኖ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ሕይወት ውስጥ ገቡ። ያን ጊዜ ሚስትየው “እኔ አረብ ሀገር ሄጄ ሰርቼ ልምጣ” በማለት ለመሄድ ተዘጋጀች።

ቤተሰብ የሚወዳት ወጣት አግብታ፤ ወልዳ፤ ከብዳ ትኖራለች ብለው ሲያስቡ ባገባች ማግስት አረብ ሀገር ለመሄድ ማሰቧ በጣም ቢያስከፋቸውም ውሳኔዋን ላለመጫን ዝምታን መረጡ። የአረብ ሀገር ጉዞዋን ለመጀመር ከቤት ስትወጣ ግን ባለቤቷ ለያዥ ለገናዥ አስቸግሮ ነበር። በእንባ የተሸኛኙት ባልና ሚስት ጠባቸውን ርግፍ አድርገው በፍቅር ማውራት ጀመሩ። ሚስትም ወደ አረብ ሀገር አቀናች::

ከአረብ ሀገር መልስ

በሸገር ከተማ አስተዳደር ገላን ክፍለ ከተማ አንዶዴ ወረዳ ውስጥ አቶ ከተማ አልዩ እና ወይዘሮ ይቅናሽ ባይሳ የተባሉ ጥንዶች ከ2004 ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ አንድ ልጅ አፍርተው በትዳር አብረው ይኖሩ ነበር።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ2004 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ሚስት ወይዘሮ ይቅናሽ ወደ አረብ ሀገር ሄዳ ነበር:: አረብ ሀገር በሄደችበት ወቅት የሰራቸውን እየላከች ባለቤቷም እያጠራቀመ ጥሪት አፍርተው ነበር። ከአረብ ሀገር ስትመለስም በደስታ ተቀብሏት በሞቀው ቤታቸወ መኖር ጀመሩ። ባልየው ቋሚ ሥራ ባይኖረውም የተቻለውን ያህል እየሞከረ የተጠራቀመው ገንዘብ እስኪያልቅ ድረስ በደስታ ኖሩ።

በዚህ መካከል ትዳራቸው በልጅ ተባረከ። አንድ ወንድ ልጅ ወላጆች ሆኑ። ልጅ ሲመጣ ፍላጎቶቻቸው ሲጨምሩ እጅ ማጠር ጀመረ። ወትሮም በውሃ ቀጠነ የሚጣሉት ባልና ሚስቱ ማጣት ሲጨመርባቸው ጭቅጭቃቸው ስር እየሰደደ ለከፋ ፀብ መዳረግ ጀመሩ።

በዚህ መካከል ነው ወይዘሮ ይቅናሽ ማጣት ከሚያጣላን ተመልሼ አረብ ሀገር ሊሂድ የሚል ሃሳብ ያነሳችው። ወልደው ከብደው በኖሩባት ጎጆ ውስጥ ሰላም ማጣት ከሚሰፍን ያለውን ችግር ብቀርፍ ይሻላል በማለት ሃሳቧን ለባለቤቷ ተካፍላለች። ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ነው ምሽት ላይ ሚስት በድጋሚ ኮንትራት ስላላት ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ ሃሳብ ብታቀርብም ባል ግን በዚህ ፍቃደኛ አልሆነም::

ያላለቀ ኮንትራት ስላላት በቀላሉ ሄዳ በሁለት ዓመታት ውስጥ እንደምትመለስና እስከዛ ልጃቸውን ተንከባክቦ እንዲያሳድግ ልታግበባው ብትሞክርም በምንም ሁኔታ ፍቃደኛ ሊሆን እንደማይችል በቁጣ ይናገራል።

ከሀገር መውጣት እንደማትችል እና እዚሁ አብረን መኖር አለብን በማለት በሃሳቧ እንደማይስማማ ያሳውቃታል፤ በዚህ ከፍተኛ ጭቅጭቅ ውስጥ ይገባሉ። “ቤትህን በአግባቡ መምራት ሳትችል ከምሄድበት ልታስቀረኝ አትችልም” የሚል ንግግር ሚስትየው ስትናገር ጭቅጭቁ እና አለመግባባቱ ከሮ ወደ ከፋ ፀብ ተቀየረ።

ባል ሚስቱ ብሶቷን እያነሳች ስትናገር ንዴቱን መቆጣጠር የተሳነው ባል አካፋ አንስቶ የሚስቱን ጭንቅላቷን ይመታታል። ሚስት በአንድ ምት ወድቃ ስትዘረር ባል በሕይወት ትኑር አትኑር የሚለውን ሳያረጋግጥ ቤት ውስጥ ጭቃ ለመመረግ የተቆፈረ የአፈር ጉድጓድ ውስጥ ከተታት::

የቤተሰብ ጥያቄ

ሚስት ከባሏ ጋር ስለነበረው ጭቅጭቅ ለቤተሰቦቿ ከመናገር ተቆጥባ ኖራለች:: ወላጆቿ ይጨነቃሉ በማለት የሆዷን በሆዷ ይዛ ቆይታለች:: በየእለቱ በትዳሯ ደስተኛ እንደሆነች ስለምታስመስል ልጃችን ክፉ ነገር ይገጥማታል ብለው አስበው አያወቁም ነበር።

በእለቱም ሁለት ዓመት ያለፈውን ልጇን ይዛ ቤተሰቦቿ ጋር ነበር የዋለችው። ወላጆቿ “እዚሁ እየሰራሽ ኑሪ ሰው ሀገር መሄድ የለብሽም” እያሉ ሲመከሯት ስለነበር የሆዷን በሆዷ ይዛ ምንም ሳትላቸው ትውላላች። ማታ ቤት ስትገባ ባሏ ሥራ እንዳጣና ምንም ገንዘብ እጁ ላይ እንደሌለ ሲነግራት ነበር፤ አረብ ሀገር የመሄዱን ሃሳብ ያነሳችው።

ማጣት ደስታቸውን ከሚነጥቃቸው ልጇን ወላጆቿና ባለቤቷ እንዲያሳድጉት እሷ ደግሞ አማራጭ ያለችውን የአረብ ሀገር ሥራ ለመሥራት ወሰነች።

ውሳኔዋ ከባሏ ጋር ቢያጣላትም ነፍሴን ያሳጣኛል ብላ አላሰበችም ነበር። ለቤቷ ምሶሶ የሆነች መልካም ሚስትና እናት ለመሆን በማሰብ ልሥራ ማለቷ የትዳር አጋርዋን አስከፍቶት እጁን ያነሳብኛል ብላ አላሰበችም ነበር። ባል በደም ፍላት ሚስቱን በአካፋ መጥቶ ሲጥላትና ትኑር ትሙት ሳያረጋግጥ ከወደቀችበት አንስቶ ወደ ጉድጓድ ሲጨምራት ዓይኑን አ ላሸም ነበር።

ሚስቱን ቀብሮ ምንም እንዳልተፈጠረ ከልጁ ጋር ገብቶ የተኛው ይህ ሰው ከወንጀሉ ነፃ መውጣቱን እንጂ የልጅነት ሚስቱን ማጣቱ አልከነከነውም ነበር። የሚኖሩበት አካባቢ ቤተሰቦቿ ከሚኖሩበት ቦታ ትንሽ ራቅ ይል ስለነበር ሶስት ቀናት ቆይቶ ራሱን ካረጋጋ በኋላ ወደ ቤተሰቦቿ ሄደ።

ከሶስት ቀን በኋላ ወደ ቤተሰቦቿ በመሄድ ልጃቸው ወደ አረብ ሀገር እንደሄደች ይነግራቸዋል፤ ቤተሰቦቿም ‹‹እንዴት ሳትነግረን ሄደች?›› የሚል ጥያቄ ላቀረቡለት ጥያቄ ‹‹እንዳትሄድ ስለከለከላችኋት ነው ተደብቃ የሄደችው›› ብሎ ያሳምናቸዋል:: እነሱም ይቅናት በማለት ጉዳዩን ይተውታል።

የተወለደው ልጅም እያደገ ሄደ። ቀን ቀንን እየወለደ ሲሄድ ልጃቸው ወደ ቤቷ አለመመለሷ ወላጆች ይጨነቁ ጀመር። አረብ ሀገር ሄደች ከተባለ በኋላ ለ6 ዓመት ያህል ቤተሰቦቿ ስለሷ ምንም ዓይነት ስልክ አግኝተው አያውቁም ነበር። የወላጆቿ ፍቅር የሚያንሰፈስፋት ይች ሴት ሳትሰናበታቸው መሄዷ ሳያንስ ድምጿን ሳይሰሙ ለዓመታት መቆየታቸው ከነከናቸው።

ስለ ልጃቸው ምንም ዓይነት መረጃ ባለማግኘታቸው ተጠራጥረው ባልን ይጠይቁታል፤ ባልም እሱ ጋር እንደምትደውል እና የቤት እና የመኪና መግዣ እስኪሞላላት ወደ ሀገር እንደማትመለስ ይነግራቸዋል::

ያች እንኳን ወልዳ ይቅርና ሳትወለድ እንስፈስፍ የሆነችው ልጃቸው አንድም ቀን ስልክ ሳትደውል መቅረቷ ግራ ያጋባቸው ወላጆች ምላሹ አላረካቸውም:: ይህን ጉዳይ በደንብ ማጣራት እንዳለባቸው ይወስናሉ።

ቤተሰቦቿም በሁኔታው በድጋሚ ጥርጣሬ ውስጥ ስለገቡ ለፖሊስ ያመለክታሉ። ፖሊስም ጉዳዩን ለማጣራት ኢሚግሬሽን እና ዜግነት ምዝገባ አገልግሎት ያመለክታሉ፤ በዚህም ወይዘሮ ይቅናሽ ወደ ሀገር ውስጥ መመለሷን እንጂ ከሀገር መውጣቷን የሚያመላክት መረጃ እንደሌለ ለፖሊስ መረጃው ይደርሰዋል::

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ ኢሚግሬሽን እና ዜግነት ምዝገባ አገልግሎትን መረጃ ከያዙ በኋላ ምርመራ ጀመረ። የምርመራ ጅማሬው በቀጥታ ባለቤቷን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ማጥራት ነበር። ምርመራው ሲጀመር አቶ ከተማ ሚስቱን ለስድስት ዓመታት ቆፍሮ መቅበሩን እና ቤተሰቧን ሲያታልል እንደነበር ቃል ይሰጣል:: በዚህ መሠረትም የግለሰቧ አስክሬንም ተቆፍሮ እንዲወጣ የኦሮሚያ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል ክትትል በማድረግ ለጳውሎስ ሆስፒታል ፓቶሎጂስቶች አስክሬኑን እንዲመረምሩ በመደረጉ የአስክሬንም ምርመራው ለፖሊስ ይደርሰዋል:: ፖሊስም ምርመራውን አጠናቅሮ ክስ ይመሰረት ዘንድ ለሸገር ከተማ ዓቃቤ ሕግ ይልካል።

የዓቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

የሸገር ከተማ ፖሊስ እና የገላን ከተማ ፖሊስ ባደረጉት ምርመራ ባል ጥፋተኛ መሆኑ በመረጃ በመረጋገጡ የምርመራ መዝገቡን ለሸገር ከተማ ዓቃቤ ሕግ ተልኳል:: ዓቃቤ ሕግም በአቶ ከተማ ላይ ከባድ የግድያ ወንጀል ክስ መስርቶበታል።

ዓቃቤ ሕገ በክስ ዝርዝሩ እንዳስረዳው በሸገር ከተማ አስተዳደር ገላን ክፍለ ከተማ አንዶዴ ወረዳ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ጥንዶች ከ2004 ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ አንድ ልጅ አፍርተው በትዳር አብረው ይኖሩ ነበር ።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ2004 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም ሚስት ወደ አረብ ሀገር ሄዳ ነበር:: ከአረብ ሀገር ስትመለስ አንድ ልጅ ወልደው በመኖር ላይ ሳሉ ከቆይታ በኋላ ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ነው ምሽት ላይ ሚስት በድጋሚ ኮንትራት ስላላት ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ ሃሳብ ታቀርባለች ባል ግን በዚህ ፍቃደኛ አልሆነም::

ከሀገር መውጣት እንደማትችል እና እዚያው አብረን መኖር አለብን በማለት በሃሳቧ እንደማይስማማ ያሳውቃታል፤ በሁኔታው ወደ ከፍተኛ ጭቅጭቅ ውስጥ ይገባሉ፤ ጭቅጭቁ እና አለመግባባቱም ከሮ ባል አካፋ አንስቶ የሚስቱን ጭንቅላቷን ከመታት በኋላ በሕይወት ትኑር አትኑር ሳያረጋግጥ ቤት ውስጥ ጭቃ ለመመረግ የተቆፈረ የአፈር ጉድጓድ ውስጥ ይቀብራታል::

ባል ከሶስት ቀን በኋላም ወደ ቤተሰቦቿ በመሄድ ልጃቸው ወደ አረብ ሀገር እንደሄደች ይነግራቸዋል፤ ቤተሰቦቿም እንዴት ሳትነግራቸው እንደሄደች ላቀረቡለት ጥያቄ እንዳትሄድ እናንተ ስለከለከላችኋት ተደብቃ ሄዳለች ብሎ ያሳምናቸዋል እነሱም ይቅናት በማለት ጉዳዩን ይተውታል::

በዚህ ሁኔታ ግን ለ6 ዓመት ያህል ቤተሰቦቿ ስለሷ ምንም ዓይነት መረጃ ባለማግኘታቸው ተጠራጥረው ባልን ይጠይቁታል ባልም እሱ ጋር እንደምትደውል እና የቤት እና የመኪና መግዣ እስኪሞላላት ወደ ሀገር አልመለስም እንዳለችው ለቤተሰብ ይናገራል::

ቤተሰቦቿም በሁኔታው በድጋሚ ጥርጣሬ ውስጥ ስለገቡ ለፖሊስ ያመለክታሉ። ፖሊስም ጉዳዩን ለማጣራት ኢሚግሬሽን እና ዜግነት ምዝገባ አገልግሎት ያመለክታሉ:: በዚህም ሚስት ወደ ሀገር ውስጥ መመለሷን እንጂ ከሀገር መውጣቷን የሚያመላክት መረጃ አልተገኘም።

የሸገር ከተማ ፖሊስ እና የገላን ከተማ ፖሊስ ባደረጉት ምርመራ ባል ጥፋተኛ መሆኑ በመረጃ በመረጋገጡ የምርመራ መዝገቡን ለሸገር ከተማ ዓቃቤ ሕግ ተልኳል:: ዓቃቤ ሕግም በአቶ ከተማ ላይ ከባድ የግድያ ወንጀል ክስ መሰረተበት።

ውሳኔ

የሸገር ከተማ ፖሊስ እና የገላን ከተማ ፖሊስ ባደረጉት ምርመራ ባል ጥፋተኛ መሆኑ በመረጃ በመረጋገጡ የምርመራ መዝገቡን ለሸገር ከተማ ዓቃቤ ሕግ ተልኳል፡፡ ዓቃቤ ሕግም በአቶ ከተማ ላይ ከባድ የግድያ ወንጀል ክስ መሰረተበት።

ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው የችሎት ውሎ ላይ ተከሳሽ ከተማ በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

አስመረት ብስራት

 

አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You