ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ሁሉም የድርሻውን ይወጣ!

የአንድ ሀገር ሕዝቦች ለጋራ ዕድገት፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት፣ በጥቅሉም ለሁለንተናዊ ደኅንነትና ብልጽግናቸው በጋራ የመቆማቸውን ያህል፤ በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ምክንያት የማይግባቡባቸው ሁኔታዎች ይፈጠራሉ:: እነዚህ ያለመግባባቶች ደግሞ በሕዝቦች በዋናነትም የጉዳዩ አቀንቃኝና አራማጆች ችግሮቹን ቁጭ ብሎ ለመወያየትና ለመፍታት ባላቸው እሳቤና ቁርጠኝነት ልክ በአጭሩ ሊፈቱ፤ አልያም ወዳልተፈለገ ልዩነት ሊያመሩ ይችላሉ::

በዚህ ረገድ አለመግባባቶችን መክረው ወደመፍትሔ የደረሱ ሕዝቦች የመኖራቸውን ያህል፤ አለመግባባቶቻቸው ወደ ልዩነት፤ ልዩነቶችን ወደ ግጭትና የእርስ በእርስ ጦርነት ያስገባቸው ሕዝቦች ስለመኖራቸውም የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: ይሄ አለመግባባት ወደ ልዩነት፣ ልዩነቱም ወደ ግጭትና ጦርነት ያመራባቸው ሀገራት ሕዝቦች ደግሞ፤ አንድም በድህነትና ኋላ ቀርነት ውስጥ የሚዳክሩ ሲሆኑ፤ ካልሆነም የጥንካሬያቸው ምንጭ የሆነውን አንድነታቸውን አላልተው ተበታትነዋል::

ኢትዮጵያም እንደ ሀገር፤ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ በዚህ መልኩ ሊገለጡባቸው የሚችሉ በርካታ ጉዳዮች አሉባቸው:: ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን በአንድ ቆመው ወራሪን አሳፍረው ነፃነትና ሉዓላዊነታቸውን አጽንተዋል:: እውቀቶቻቸውን ደምረውም በዓለም ሥልጣኔ (በባሕል፣ በሥነጥበብና ሥነ ሕንጻ፣ በሥነጽሑፍና ሥነፈለክ፣ …) ውስጥ የሚጠቀስ ተግባርን ፈጽመዋል፤ ይሄንኑ የሚናገር ዐሻራንም አኑረዋል::

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የፍላጎትም ሆነ የአስተሳሰብ ልዩነትን በልኩ አጣጥሞ ከመጓዝ ጋር በተያያዙ የተፈጠሩ ቅራኔዎች አሉ:: እነዚህ ቅራኔዎች ደግሞ የርስ በርስ ግጭትን ብሎም ጦርነትን እንድናስተናግድ እያደረጉን ዛሬም ድረስ ዘልቀዋል::

እነዚህ አለመግባባቶች፣ ልዩነትና ቅራኔዎች ደግሞ ወደ ግጭትና ጦርነት የማምራታቸው ምክንያት፣ በችግሮቹ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መነጋገርና መፍታት ባለመቻላችን ነው:: ዛሬም በዚህ መልኩ ለችግሮቻችን መነጋገርና መመካከርን ባለማስቀደማችን፤ አንዳንዶች ችግሮችን በጠብመንጃ መፍታት ይቻላል የሚል እሳቤን ይዘው ዘልቀዋል:: ለዚህም እንደ ሀገርም፣ እንደ ሕዝብም ከጦርነት አዙሪት መውጣት ተስኖናል::

ይሄን ከፍ ያለ ችግር፣ ከትናንት እስከ ዛሬም ዋጋ እያስከፈለን ያለ ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ተሸክመነው ልንጓዝ አይገባም:: ይሄ ደግሞ የሕዝቦች ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ከፍ ያለ ፍላጎት ያለበት ጉዳይ ነው:: ለዚህም ነው ከለውጡ ማግስት ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን በኅብረ-ብሔራዊ የደመቀን አብሮነትና አንድነት አጽንቶ ለማዝለቅ ባለ መሻት ምክንያት፤ ኢትዮጵያውያን በልዩነቶቻቸውና ችግሮቻቸው ላይ ቁጭ ብለው እንዲመክሩ፣ ችግሮቻቸውን ፈትተው፣ ልዩነቶቻቸውንም አቻችለውና አጥብበው እንዲጓዙ የሚያስችላቸውን ዓውድ ለመፍጠር እንዲቻል ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ ተወጥኖ ወደ ተግባር የተገባው::

በዚህ ረገድ እንደ ሀገር የተከማቹ እና አሁንም ድረስ የሚታዩ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እና ለሕዝቦች አብሮነት መጠናከር ሀገራዊ ምክክርን እንዲያመቻች የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ፤ ኮሚሽነሮች ተመድበውለት እና አደረጃጀት ተፈጥሮለት ወደሥራ ገብቷል:: በዚህም የቅድመ ዝግጅት ተግባራቱን አጠናቅቆ፤ በዝግጅት ጊዜ ተግባሩም አጀንዳ መረጣ ለማካሄድ በሚያስችለው ደረጃ ላይ ደርሷል:: ይሄን ካደረገ በኋላም ተጠባቂውን ምክክር ያካሂዳል::

በመንግሥት ጽኑ መሻትና ቁርጠኝነት ተወጥኖ፤ በኮሚሽኑ ኃላፊነትን ለመወጣት ባለ መነሳሳት ተጉዞ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ታዲያ፤ ተጠባቂው ምክክር ሊደረግ እና ተፈላጊው ውጤት ሊመጣ የሚችለው በኮሚሽኑ ትከሻ ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ አይደለም:: ይልቁንም ከሁሉም ዜጋም ሆነ ተቋም ከፍ ያለ ሚናንም፣ ኃላፊነትንም መወጣት ይጠይቃል::

ኮሚሽኑም ቢሆን ይሄንኑ ስለሚገነዘብ፣ በምክክር ሂደቱ ያግዙኛል፣ ተልዕኮዬን እንዳሳካ አቅም ይሆኑኛል ያላቸውን ባለድርሻዎች አብረውት እንዲሠሩ በሚችለው ሁሉ እየጣረ ነው:: ቀርቦ ያማክራል፤ ሀሳብ ይሰበስባል፤ አቅም ይገነባል፤ በሕግና አሠራሮች ላይ ያወያያል፤ ሁሉም ዜጋና ተቋም ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ችግሮች መፈታት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ደጋግሞ ያሳስባል::

በዚህ በኩል በየደረጃው ያለው ሕዝብ፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የፖለቲካ እና የተለያዩ ሲቪክ ድርጅቶች፣… ሁሉም በየፈርጃቸው ከፍ ያለ ኃላፊነት አለባቸው:: ለምሳሌ፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሀገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ በማድረግ በኩል ከፍ ያለ ኃላፊነት አለባቸው:: በዚህም ዜጎች ግንዛቤ ኖሯቸው በምክክሩ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል መረጃ የመስጠት፣ የማስገንዘብ እና የመነጋገር ባሕልን ለማጎልበት የሚያስችሉ ዘገባዎችንና ፕሮግራሞችን መሥራት ይኖርባቸዋል::

በዚህ ረገድ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም፤ አሁንም ግን ከኮሚሽኑ ከፍ ያለ ተግባርና ኃላፊነት፣ ከጉዳዩም ክብደት አኳያ ሲታይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል:: በተለይ ኮሚሽኑ ተግባሩን ለማጠናቀቅ የሚቀረው ጊዜ የአስር ወራት እድሜ ከመሆኑ አኳያ፤ ከመገናኛ ብዙኃኑም ሆነ ከመላው ሕዝብና ተቋም ከፍ ያለ የቤት ሥራ ይጠበቃል:: ይሄን ማድረግ የሚቻለውም ሀገራዊ ምክክሩ ከችግሮቻችን መውጫ መሆኑን ሁሉም መገንዘብ ሲችል እንደመሆኑ፤ ለምክክሩ መሳካት ሁሉም በዚሁ መንፈስ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል!

አዲስ ዘመን  ግንቦት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You