የኮሪደር ልማቱ ከመንገድም ባሻገር

የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ምቹ ያልሆኑ ጎዳናዎች፤ ለተሽከርካሪ እንዲሁም ለእግረኞች አመቺና ከተማዋን በሚመጥኑ መንገዶች እየተተኩ ይገኛሉ። በዚህም ምክንያት ከቤቱ በእርምጃ ወደ ሥራ የሚያቀና አሊያም የሚመለስ፣ ለታክሲ እና አውቶቡስ ጥበቃ በሰልፍ የሚያባክነውን ጊዜ በእርምጃ የለወጡ ብዙዎች ከወዲሁ መታየት ጀምረዋል።

በእርምጃ እና በሩጫ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርግ፣ ለቀጠሮም ይሁን ጊዜ ለማሳለፍ በየካፍቴሪያዎቹ ተቀምጦ መዋልን የሚመርጥ ብዙ ሰው አሁን ላይ ባማሩ የመንገድ ዳር አረንጋዴ ስፍራዎች አረፍ ብሎ መታየት እየተለመደ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተለያዩ ቀረጻዎችና ሌሎች መርሀ ግብሮች መንገዶችን ምርጫቸው ያደረጉ ሚዲያዎችንም መመልከት እየቻለ ነው።

የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ ከሚያስችሉ ጎዳናዎች ዳር ለእግረኛ ምቹ፣ ሁሉንም የእድሜ እና የአካል ጉዳት ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ እንዲሁም ለእይታ ማራኪ የሆኑ የእግረኛ መንገዶችን ማዘጋጀት ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው። አስፈላጊነቱን አስቀድመው የተረዱ የዓለም ከተሞች ይህንን ታሳቢ አድርገው መንገዶች በመገንባታቸው፤ በእረፍት ሰዓታቸው የሚንሸራሸሩባቸው፣ የበጋ እና የጸደይ ወራትን ንፁህ አየር የሚቀበሉባቸው፣ ፌስቲቫሎችንና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን እንዳሻቸው የሚያስተናግዱባቸው ሆነዋል። ሰዎች ከአካባቢያቸው እና ከተፈጥሮ ጋር ያላቸው መስተጋብርም በዚህ ምክንያት እየጠበቀ እንደሚሄድ መገንዘብ ቀላል ነው።

አንዳንድ ያደጉና በቴክኖሎጂ የመጠቁ ሀገራት በበኩላቸው፤ ዜጎቻቸው ከእንቅስቃሴ ርቀው በዘመን አመጣሽና አርቴፊሻል ጉዳዮች ላይ በመጠመዳቸው እያደር ካመጣባቸው ጣጣ ተላቀው ጤናማ የኑሮ ዘይቤን ለመፍጠር ከፍተኛ ትግል ላይ ናቸው። ከከተሞች መዘመን እና ከትራፊክ መጨናነቅ የተነሳ ከዓመታት በፊት መንገዶች ‹‹ሃይዌይ›› በሚባሉት መተካታቸው ሰዎች ወደሚፈልጉት ቦታ ለመንቀሳቀስ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም የግድ ነው። በዚህም ምክንያት በቢሮዎች ውስጥ የሚከወኑ ሥራዎችን ጨምሮ የአካል እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎልና በዚህም የተነሳ ለዘርፈብዙ ችግሮች ሲጋለጡ ይስተዋላል።

ድብርት፣ ከልክ ላለፈ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ የተነሳ የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ ነገር ግን ገዳይ ለሆኑ የጤና ችግሮች ተጋላጭ እንደሚያደርጉ ተደጋግሞ ይነሳል። ይህም ያለእድሜ ለሚከሰት ሞትና አምራች ዜጎች መቀነስ ምክንያት በመሆኑ ለሀገር ትልቅ ኪሳራን ማስከተሉ እርግጥ ነው። የዘመናችን የማይተላለፉ ነገር ግን ቁጥር አንድ ገዳይ የሆኑ በሽታዎች በተራቀቀው ሳይንስ መፍትሔ ስላልተገኘላቸውም የዓለም የጤና ድርጅትን ጨምሮ ባለሙያዎች አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ብቸኛው የማምለጫ መንገድ መሆኑን ይጠቁማሉ።

በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል የተሠራው ጥናትም ይህንኑ ሃሳብ የሚያጠናክር ነው። ጀሚላ ዋርተን የተሰኙት የጥናት ቡድን መሪ 919 ለሚሆኑ አዋቂዎች በተደረገ ቃለምልልስ እንዲሁም በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ባደረጉት ምልከታ የእግረኛ መንገዶች ከአካላዊ እንቅስቃሴ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል። በተገቢው መንገድ ያልተሠሩና መሰናክል የበዛባቸው መንገዶች ለመራመድ ምቹ ባለመሆናቸው እግረኞች አስገዳጅ ከሆነ መተላለፊያነት ባለፈ ለእርምጃ አሊያም ለስፖርት እንቅስቃሴ የማይስቡ ናቸው።

በመሆኑም የመንገዶቹ ምቹነትና የሰውን ፍላጎት መሠረት አድርገው መገንባታቸው ዜጎች በእግራቸው እንዲጓዙ፣ ብስክሌት እንዲጋልቡ እንዲሁም ሩጫ እና ሌሎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አይነቶችን እንዲያዘወትሩ ይገፋፋቸዋል። ይህም ከአእምሮ እና የአካል ጤና ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ስለሚኖረው ምርታማ ዜጎችን ከማፍራት አንጻር ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው።

አዲስ አበባ እየተጋች የምትገኝበት የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ከዚህ ቀደም በተገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይም ይኸው ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶበት ተመልክተናል። ከተማዋ ተሽከርካሪ እና እግረኛ እኩል እየተጋፉ የሚጓዙበት፣ ለአደጋ የሚጋለጡበት፣ በንጽህና ያልተያዙ እና አብዛኛውን ጊዜ ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ መንገዶች መለያዋ ነበሩ።

ይህ ሁኔታም መልካም ገጽታዋን ከማጉደፉም ባለፈ ከዘመናዊው ዓለም ጋር የማያራምዳት፣ የከተማነት መስፈርትን ጭምር ያሟላ ለማለት አዳጋች ነበር። አሁን ግን ከተሽከርካሪ ጋር ንክኪ የሌላቸው፣ እጅግ ሰፋፊ፣ በአረንጓዴ እጽዋት የተዋቡና አረፍ ለማለት የሚመቹ መቀመጫዎች ባሏቸው የእግረኛ መንገዶች እየተተኩ ነው። ይህም እንደ ከተማ ብቻም ሳይሆን እንደ ሀገር የሚኖረው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሙ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በመልካም ገጽታዋ በዓለም ዙሪያ እንድትጠራና እንድትታወቅ ካደረጓት ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መካከል አንዱ አትሌቲክስ መሆኑ ይታወቃል። በኦሊምፒክና በሌሎች ትልልቅ የውድድር መድረኮች የሀገርን ሰንደቅ በክብር በማውለብለብ እንድንኮራ ያደረጉን ቀደምት ጀግኖች አትሌቶቻችን ድንቅ ተፈጥሮን በታደሉ መልክዓ ምድሮች ላይ መሠረታቸውን በማድረግ ለትውልድ የዘለቀ አሻራቸውን አሳርፈው አልፈዋል።

ዛሬ ላይ በእግራቸው ሀገርን ለማስጠራት የተተኩ ወጣት አትሌቶች ደግሞ ከከተማ መስፋፋትና ከሀገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አዲስ አበባን ማዕከል አድርገዋል። በእርግጥም በሀገሪቷ ካሉ ክለቦች መካከል 90 ከመቶ በላይ የሚሆኑት መቀመጫቸውን ያደረጉት አዲስ አበባ ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን ጨምሮ በቀላሉ ለልምምድና ለውድድር የሚሆኑ መሞችም በብዛት የሚገኙት በከተማዋ እና ዙሪያዋ ነው።

እነዚህን ጨምሮ በበርካታ ምክንያቶች የአትሌቶች ወደ ከተማዋ የሚደረግ ፍልሰት ከጊዜ ወደጊዜ በመጨመር ላይ ይገኛል። ታዲያ አትሌቶች በመም እና በጂምናዚየሞች ከሚያደርጓቸው ልምምዶች ባሻገር የጎዳና ዝግጅቶቻቸውም መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ከንጋት አንስቶ እስከረፋድ በአዲስ አበባ እና በመውጫዎቿ ባሉ አቅጣጫዎች በጋራ እና በተናጥል ሲሮጡ መመልከት የተለመደ ነው።

ታዲያ በከተማዋ ባለው የትራፊክ እና የመንገድ ሁኔታ በቀጥታ ለአደጋ ተጋላጭ ሲሆኑ ቆይተዋል። በቁጥር በርካታ የሆኑ አትሌቶች በመደበኛ የጎዳና ልምምድ ላይ ሳሉ በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ሲነጠቁና ለከፋ የአካል ጉዳት ሲዳረጉም ተመልክተናል። እንደሀገር እንቁ ለሆነን ብቸኛው ውጤታማ ስፖርታችን እና ለአትሌቶች በቂ የዝግጅትና የውድድር ስፍራዎችን ማዘጋጀት ባይቻልም አሁን ላይ እየተመለከትናቸው የሚገኙት ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም ለብስክሌት መጋለቢያነት የታሰቡ አቅጣጫዎች ስፖርቱን ከመጥቀም አንጻር አስተዋጽኦ አላቸው።

ከእግረኛ መንገዶች ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተገነቡ የሚገኙ ትልልቅ ፕሮጀክቶችና የቱሪዝም መዳረሻዎች ያቀፏቸውን የመም እና ሌሎች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም የሚዘነጉ አይደሉም። መቼም ሕፃናት ያለስጋት የሚቦርቁባቸው፣ አዛውንቶች አረፍ እያሉ የሚጓዙባቸው፣ አዋቂዎች የአካል ጤናቸውን የሚጠብቁባቸው፣ ከተማዋ ያፈራቻቸው ስፖርተኞች እንዳሻቸው ልምምድ የሚያደርጉባቸው እና ለአፍሪካ መቀመጫነት የማታንስ እንደስሟ አበባ የሆነች ከተማ እንድትኖረን የማይናፍቅ ዜጋ አይኖርም።

በእርግጥም የተገነቡትና በግንባታ ላይ የሚገኙት እንዲሁም በቀጣይ የማሻሻያ እቅድ ውስጥ የተያዙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ጠቀሜታ መንገድነት ብቻም አይደለም። ይልቁንም በአእምሮ እና በአካል ጤናው የተጠበቀ ዜጋና ትውልድን ማፍራት መሠረት ያደረጉ ተፈጥሯዊ መድኃኒቶች ናቸው። በመሆኑም ይህንን ተረድተን የእግረኛ መንገዶቻችንን በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ይገባል። መንግሥትም መሰል ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በማስፋቱ ረገድ እያከናወነ የሚገኘውን ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You