ተጠቃሚ ማፍራትን የሚጠይቀው ተኪ ምርቶችን የማምረቱ ሥራ!

መንግሥት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል ተኪ ምርቶች ላይ አተኩሮ የሚከናወነው ተግባር ይጠቀሳል። የገቢ ምርትን ለመተካት በሚከናወን ሥራ 30 በመቶ ሆኖ የቆየውን የሀገር ውስጥ ምርት የገበያ ድርሻ ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ አቅዶ እየሠራም ነው። ለእዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየወጣባቸው ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን ጨምሮ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮ መስራቱን ተያይዞታል።

በተኪ ምርቶች ማምረት ላይ ለውጦች መታየት የጀመሩትም ይህን ሁሉ ተከትሎ ነው። በዚህ ተግባር ከተከናወኑት መካከልም በየዓመቱ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ እየወጣበት ከውጭ እንዲመጣ ሲደረግ የኖረውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የተቻለበት ሁኔታ ይጠቀሳል፤ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያገለግሉ ማሽኖችና መለዋወጫዎችም እንዲሁ በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ እየተደረገ ሲሆን፤ በአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ዘርፍም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የሚያስንቁ አልባሳትን ማምረት እየታቸለ ነው።

ይህ ሁሉ ተኪ ምርቶችን የማምረቱ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተራመደ መሆኑን ያመለክታል። በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የሚያወጡ ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ መመረታቸው በተኪ ምርቶች ላይ ጥሩ ሥራ እየተከናወነ ለመሆኑ ሌላው ማሳያ ነው።

ከዚህ ሁሉ ጋር አብሮ ማደግ ያለበት ተኪ ምርቶችን የሚጠቀመው ማኅበረሰብ ቁጥር መጨመር ነው፤ ይሁንና በሸማቾች በኩል አሁንም ብዙም የአመለካከት ለውጥ አለመምጣቱ እየተጠቆመ ይገኛል። አምራችና ሸማችቾን በማስተሳሰር ላይ ክፍተት ስለመኖሩም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሀገሪቱ ቀደም ሲል አንስቶ ዜጎች ለሀገራቸው ምርት ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ ‹‹ በሀገሬ ምርት እኮራለሁ›› የሚል መፈክር በማንገብ ጭምር ሠርታለች። የሀገራቸው ኢንዱስትሪዎችን ምርቶች በመጠቀም ራሳቸውንም ሀገራቸውንም እንዲጠቀሙ ለማድረግ ተሞክሯል። ዜጎች ለውጭ ምርቶች ያላቸው ፍላጎት አሁንም ከፍተኛ መሆኑ ሲታሰብ ጥረቱ ውጤታማ ነው ተብሎ አይወሰድም።

ሀገሪቱ አሁንም ለዜጎች ጥሪ እያቀረበች ትገኛለች። በቅርቡ በተካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤክስፖ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶ/ር/ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያን በተሻለ ፍጥነት ለማሳደግ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የግድ መጠቀም ይገባል።

ተኪ ምርት ማምረት ፋይዳው ትልቅ ነው። ምርቶቹ ዜጎችና አምራቾችን ብቻ አይደለም የሚጠቅሙት። ሀገርንና መንግሥትንም ነው፤ ይህ ታምኖበትም ነው ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሻለ ፍጥነት ሀገርን ለማሳደግ ተኪ ምርቶችን በግድ መጠቀም እንደሚገባ ያስታወቁበትንም ሁኔታ ከዚሁ አኳያ ተመልክቶ እንደ ዜጋና እንደ ተቋም ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል።

ይህን ለማድረግ በቅድሚያ አሁንም ሸማቾች ለሀገር ውስጥ ምርቶች ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ ላይ መሥራት ያስፈልጋል። በተኪ ምርት መጠቀም ላይ ያለው ለውጥ ሀገር በምትፈልገው ልክ እንዲደርስ ለማድረግ የውጭ አልባሳት አምላኪ ዜጎች አመለካከትን ለመቀየርና በሀገራቸው ምርቶች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ በስፋት መሥራት የግድ ያስፈልጋል። ይሄ በዜጎች ዘንድ ስር የሰደደ ኋላ ቀርና ለሀገር የማይበጅ አመለካከት በመሠረታዊነት መቀየር ይኖርበታል።

የሀገር ውስጥ ምርቶችን ባለመጠቀም በኩል አምራች ኢንዱስትሪዎችም ይጠቀሳሉ። በቅርቡ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ማሽነሪ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማስተሳሰር ባካሄደው መድረክ ላይ እንደተጠቆመው፤ ተቋማትም ተኪ ምርቶችን ያለመጠቀም ችግር ይታይባቸዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንዳመለከተው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ለአምራቾች በማሽነሪ ሊዝ ከተላለፉት 32 ሺ የማምረቻ ማሽኖች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው በሀገር ውስጥ የተመረቱት። ይህ የሆነው ደግሞ በሀገር ውስጥ ማሽኖችን የማምረት አቅሙ በጥሩ ደረጃ ላይ ባለበት ሁኔታ ነው ይሄ የሆነው። ይህን ችግር ራሱን የቻለ አሠራር በማስቀመጥ እንዲሁም ጥናት ላይ በመመስረት መፍታት ይገባል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካይነት ለተኪ ምርቶች ማምረት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ በስፋት እየተሠራ ባለበት ሁኔታ ዜጎችና ተቋማት ምርቶቹን እንዲጠቀሙ ማድረግ ላይም በስፋት መሥራት ያስፈልጋል። ተኪ ምርቶችን ዜጎችና ድርጅቶች ምን ያህል እየተጠቀሙ ስለመሆናቸው እንዲሁም ምርቶቹን የማይጠቀሙ ዜጎችና ድርጅቶች ምክንያታቸው ምን እንደሆነ በጥናት መለየትና መፍትሔ ማመላከትም ያስፈልጋል።

በሀገሪቱ አልባሳት በስፋት እየተመረቱ ዜጎች ልባሽ ጨርቆች ሲመርጡ በውድ ዋጋ የውጭ አልባሳትን ሲገዙ ይታያሉ። ችግሩ ከማስተዋወቅና ከምርቶቻችን ጥራቶች ጉድለት መሆን አለመሆኑ መለየትና ችግርም ካለ መፍትሔ ማስቀመጥ ይኖርበታል። ሀገሪቱ በተኪ ምርት ማምረት እደርስበታለሁ ብላ የያዘችው እቅድም የተኪ ምርት ተጠቃሚዎችን አሀዝ በእጅጉ ማብዛትን ይጠይቃል!

አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You