ኖርዌይ፣ አየርላንድ እና ስፔን ለፍልስጥኤም የአገርነት እውቅናን በይፋ እንደሚሰጡ አስታወቁ

ኖርዌይ፣ አየርላንድና ስፔን በእስራኤልና በፍልስጤማውያን መካከል የሚካሄደውን ንግግር ያግዛል በሚል ለፍልስጥኤም የአገርነት እውቅናን እንደሚሰጡ አስታወቁ።

ስፔንና አየርላንድ ለፍልስጤም ዕውቅና የመስጠት ውሳኔያቸው ከእስራኤል በተቃራኒ በመቆም ወይም ሐማስን በመደገፍ ሳይሆን፣ ሰላምን ለመደገፍ ነው ብለዋል።

እስራኤል በሀገራቱ ውሳኔ ላይ ቁጣዋን ገልጻ በአካባቢው የበለጠ አለመረጋጋትን ይፈጥራል በማለት በሦስቱ ሀገራት ውስጥ ያሉ አምሳደሮቿን ጠርታለች።

ፍልስጤማውያኑ ሐማስ እና ተቀናቃኙ የፍልስጤም ባለሥልጣን የሀገራቱን ውሳኔ በአውንታዊነት ተቀብለውታል።

የሦስቱ ሀገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ትናንት ይፋ እንዳደረጉት ለፍልስጤም የሀገርነት እውቅናን በመስጠት የሁለት ሀገራት መፍትሄን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይመን ሃሪስ፣ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋሀርና የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በሰጡት መግለጫ፤ አገሮቻቸው ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት መወሰናቸውን አስታውቀዋል።

የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ደግሞ በጋዛ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት ለፍልስጤም ጥያቄ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ግልጽ አድርጓል ብለዋል።

አክለውም ለፍልስጥኤም አውቅና በመስጠት ‘የሁለት አገራት መፍትሄ’ የፍልስጥኤም አስተዳደርን ማዕከል ማድረግ ለእስራኤልም ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍልስጤምን የአገርነት ዕውቅና መስጠት ያለውን ችግር ለመፍታት ብቸኛውን “ጎን ለጎን በሰላም እና በመረጋጋት የሚኖሩ ሁለት ሀገራት” መፍጠርን ተግባራዊ ማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋሀር የኖርዌይ ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠት ሌሎችም ሀገራት ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያደርግ “ጠንካራ መልዕክት ነው” ሲሉ የሀገራቸውን ውሳኔ አላማ አስረድተዋል።

የሦስቱ ሀገራት ለፍልስጤም ዕውቅና የመስጠት እርምጃ በአካባቢው አለመረጋጋትን ያባብሳል ስትል እስራኤል ተቃውሞዋን አሰምታለች።

በሀገራቱ ውሳኔ የተቆጣችው እስራኤል በአየርላንድ እና በኖርዌይ ላሉት ዲፕሎማቶቿ “ለአስቸኳይ ምክክር” በሚል ጥሪ አድርጋለች።

የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢዝራኤል ካትዝ ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት ለወሰኑት ሀገራት “ግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፤ እስራኤል ሉዓላዊነቷን የሚፈታተኑትን እና ደኅንነቷን አደጋ ላይ የሚጥሉትን ከመጋፈጥ አታፈገፍግም” ብለዋል።

እስራኤል የሀገራቱን ውሳኔ በዝምታ እንደማታልፈው እና ከበድ ያለ ውጤት እንደሚያስከትል ገልጸው፤ በተለይ “ስፔን ለፍልስጤም እውቅና መስጠቷን ዕውን የምታደርገው ከሆነ፤ ተመሳሳይ እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን ሲሉ አጸፋው በስፔን ያለውን የተገንጣይነት እንቅስቃሴን በተመለከተ ይሁን ወይም ሌላ በግልጽ ያሉት ነገር የለም።

የሦስቱ ሀገራት ውሳኔ “ለፍልስጤማውያንና ለዓለም ሽብርተኝነት ውጤት እንዳለው የሚገልጽ መልዕክት ያስተላልፋል” በማለትም እርምጃው “በአካባቢው የባሰ ሽብርተኝነትን እና አለመረጋጋትን በማስከተል፤ ለሰላም ያለ ተስፋን አደጋ ላይ ይጥላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ጋዛን የሚቆጣጠረው እና በአሁኑ ወቅት ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኘው ሐማስ ሦስቱ ሀገራት ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት መወሰናቸው “በፍልስጤም ጉዳይ ላይ ያለውን ዓለም አቀፍ አቋም የሚለውጥ ነው” ብሏል።

ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን የሆነው ባሲም ናይም ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል በሰጠው ቃል የፍልስጤማውያን “ቆራጥ ትግል” ለሀገራቱ ውሳኔ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

የፍልስጤም አስተዳደር፤ ኖርዌይ፣ ስፔንና አየርላንድ “ፍልስጤማውያን የዘገየውን ፍትህ እንዲያገኙ የማያወላውል ቁርጠኝነታቸውን አሳይተዋል” ሲል ውሳኔያቸውን አወድሷል።

በቅርቡ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተጻፈ ደብዳቤ እንዳመለከተው፤ ቢያንስ 140 የዓለም ሀገራት ለፍልስጤም ዕውቅናን ሰጥተዋል።

ይህም በተባበሩት መንግሥታት የአረብ ሀገራት ስብስብ የሆኑትን 22 ሀገራትን ጨምሮ፣ 57 የእስላማዊ ትብብር ድርጅት አባል ሀገራት እንዲሁም 120 የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ አባላትን ያካተተ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ለፍልስጤም በይፋ ዕውቅናን ካልሰጡ ሀገራት መካከል የሚገኙ ናቸው።

እስራኤል የፍልስጤምን አገርነት ዕውቅና የማትሰጥ ከመሆኗ ባሻገር ሌሎች አገራትም እንዳይሰጧት ትከላከላለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የሚመራው የወቅቱ የእስራኤል አስተዳደርም በጋዛ እና በዌስት ባንክ ውስጥ የፍልስጤም መንግሥት እንዲቋቋም አይፈልግም።

ለዚህም ምክንያቱ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የፍልስጤማውያን ሀገር የሚቋቋም ከሆነ ለእስራኤል ህልውና አደጋ ነው ሲል አጥብቆ ይከራከራል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You