ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር የረጅም ዘመናት የስልጣኔ እና የነጻነት ታሪክ ባለቤቶች ነን። በዚህም ትውልዶች አንገታቸውን ቀና አድርገው፤ በልበ ሙሉነት የሚራመዱባቸውን ረጀም ዓመታት መፍጠር እና መጓዝ ችለናል። ዓለም ምስክርነቱን በሚሰጥባቸው በእነዚህ ታሪኮቻችን ከበሬታ እና አንቱታም አትርፈናል።
በእነዚህ ረጅም ዘመናት ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ ብዝሃነታችን ለሀገረ መንግሥት ምስረታም ሆነ መጽናት ዋነኛ አቅም፤ ከዚያም አልፎ ውበት ሆነውናል። ልዩነቶቻችንን አቻችለን በሰላም የኖርንባቸው ብዙ ትናንቶች፤ በስልጣኔ መንገድ እንድንጓዝም የተሻሉ ዕድሎችን ፈጥረውልናል።
በየዘመኑ የነበሩ የአገዛዝ ሥርዓቶች ፤ዘመናቸውን በሚመስል መንገድ፤ሀገርን እንደ ሀገር ከመፍጠር ጀምሮ አጽንቶ ለማስቀጠል የነበራቸው አስተዋፅኦ በብዙ ተግዳሮቶች የተፈተነ ቢሆንም፤ በሕዝቡ ውስጥ የነበረው ከፍያለ የሀገር ፍቅር እስከአሁን ድረስ ጸንታ መቆም የቻለች ሀገር ባለቤት እንድንሆን አድርጎናል።
ይህም ሆኖ ግን ለቀደመው ስልጣኔያችንም ሆነ በየዘመኑ ለተፈጠሩ ሀገራዊ የለውጥ መነቃቃቶች ዋነኛ ችግር የሆነው ልዩነቶችን በንግግር ከመፍታት ይልቅ በኃይል እና በይዋጣልን መንገድ ለመፍታት የሄድንባቸው የጥፋት መንገዶች አብዛኛውን ትውልድ ያልተገባ ዋጋ አስከፍለዋል፤ዛሬም ያለውን ትውልድ እያስከፈሉ ነው።
ፉከራ እና ቀረርቶ ያልተለየው፤ለዘመናት በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት የተገዛው ሀገራዊ የፖለቲካ ባህላችን ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ ቃታ እንዲስብ በማድረግ ሀገርን የደም ምድር አድርጓል። በወንድም ደም ላይ ቆሞ በመፎከር ቂም እና በቀል ይዘን እንድንቆዝም አስገድዶን ኖሯል።
ይህ እውነታ ዛሬ ላለንበት ድህነት እና ኋላ ቀርነት ፣ ከዛም ባለይ የታሪክ ስብራት ምክንያት ነው። ሀገር እንደሀገር፤ ትውልዶችም እንደ ትውልድ ለውጥ ለማምጣት ያደረጉትን እልህ አስጨራሽ ትግል በማምከን፤ሀገር በየዘመኑ ያልተገቡ ትርምስምሶች እና ግራ መገባቶች እንድታልፍ አድርጓታል።
በብዙ ምጥ የተወለዱ የትውልድ እና የሀገር ተስፋዎች ረጅም መንገድ ሳይሄዱ መክነዋል። በዚህም እንደሀገር በቆምንበት እንድንረግጥ፤አንዳንዴም ከቆምንበት ወደኋላ ተንሸራተን የኋልዮሽ እንድንጓዝ የተገደድንባቸው ታሪካዊ ምዕራፎች ተፈጥረዋል ። ስለእነሱም የከፈልናቸው ያልተገቡ ዋጋዎች በቀላሉ የሚሰሉ አይደሉም።
በነዚህ ረጅም የታሪክ ሂደቶች ውስጥ መጥቶ የሄደ ትውልድ፤እንደ ትውልድ በብዙ ተስፋ ዓይኑን ከፍቶ ወደ ተስፋው ለመራመድ ያደረጋቸው እልህ አስጨራሽ፣በብዙ ፈተና የተሞሉ ርምጃዎች ፣በየዘመኑ የለውጥ ሾተላይ በሆነው የፖለቲካ ባህላችን ምክንያት ትርጉም አልባ ሆነው ከስመዋል።
በየዘመኑ ሀገራዊ ተስፋችንን እያመከነ ያለውን የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደ አንድ ትልቅ ሕዝብ ቆም ብለን መግራት መቻል ግድ ነው። ለአሮጌው አስተሳሰብ የሚሆን ማህበረሰባዊ የአስተሳሰብ ክፍተት መፍጠር ከሚያስችል መዘናጋት ራሳችንን መታደግ መቻል አለብን።
እንደ ሀገር አሁን ላይ የጀመርነው የለውጥ ሂደት በተመሳሳይ ፈተና ውስጥ ለማለፍ እየተገደደ ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ይዘነው የመጣነው የፖለቲካ ባህል “ሆ!” ብለን በብዙ ተስፋ በአደባባዮቻችን ያወደስነውን ለውጥ እያንገጫገጨ፤ እንደ ሕዝብ አላስፈላጊ ዋጋ እንድንከፍል እያስገደደን ነው።
የትናንት ገናና የስልጣኔ ታሪካችንን ታሪክ አድርጎ ያስቀረው ዘመናትን አብሮን እየተጓዘ ያለው ይህ ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን፤ ዛሬ ላይ በአግባቡ መግራት እና ማረቅ ባለመቻላችን ተስፋ ያደረግናቸውን ብሩህ ነገዎቻችን እየተፈታተነ ነው። አዕምሯችን ውስጥ የሳልናቸውን ብሩህ ነገዎችም እያደ በዘዘብን ነው።
ዛሬም ከትናንት ረጅም የግጭት ታሪኮቻችን መማር ያልቻሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች ባደጉበት ፉከራ እና ቀረርቶ፤ ትናንት ትውልዶችን ተስፋ ቢስ ባደረገ የይዋጣልን መንፈስ ተሞልተው፤ ሀገር እና ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሉ ነው። በገዛ ሀገራቸው ብሩህ ነገዎች ላይ ተግዳሮት ሆነው ተሰልፈዋል።
አሁን ላይ ካለንበት ከዚህ ሀገራዊ ችግር ለመውጣትም ሆነ፤ መጪዎቹ ዘመናት ከሚፈልጉት የአስተሳሰብ መታደስ አኳያ መላው ሕዝባችን ለተስፋችን ጸር የሆነውን ይህን የፖለቲካ አስተሳሰቡ ባለው ቋንቋ ማውገዝ ይጠበቅበታል። በአስተሳሰቡ ተወስደው ለጥፋት የቆሙትንም በቃችሁ ሊላቸው ይገባል።
ይህን ማድረግ እንደ አንድ ትልቅ ማህበረሰብ ራሳችንን ከጥፋት መታደግ የሚያስችለን ብቸኛ አማራጭ ነው። በዘመናት መካከል ትውልዶች በብዙ ተስፋ አድርገው ያለፉትን ሀገራዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ ምርጫ የሌለው ምርጫችን ነው። ለመጪዎቹ ትውልድ የተሻሉ ነገዎችን ለማውረስ በጎ ሕሊና እንዳለን ማሳያም ጭምር ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም