ለአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ7 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል

አዲስ አበባ፦ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከሰባት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራና ሰው ሰራሽ ደን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አበሩ ጠና ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን ባለው ሂደት ከሰባት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በማዘጋጀት ከእቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል፡፡

አሁን ላይ የችግኝ ማፍላት ሥራው ተጠናቆ የተከላ ቦታና ጉድጓድ የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዝግጅት ምዕራፉ የችግኝ ተከላ ቦታዎች ልየታ መከናወኑን አመላክተዋል።

በ115 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች ችግኝ የማዘጋጀት ሥራ ሲከናወን መቆየቱን አስታውቀው፤ ለፍራፍሬ፣ ለመኖ፣ ለውበትና ለደን ልማት የሚውሉ ችግኞች ተለይተው መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከል ሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮኑ ለደን ልማት አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውን መሪ ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ ለከተማ ውበት የሚውሉ 48 ሚሊዮን ችግኞች ለተከላ መሰናዳታቸውን ገልጸው፤ እንዲሁም ከ75 ሚሊዮን በላይ የቀርከሀ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አንስተዋል። የተቀሩት የፍራፍሬ፣ የመኖና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ለአግሮ ፎረስትሪ ልማት የሚረዱ ችግኞች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የሚከናወንበት ወቅት እየተቃረበ በመሆኑ የዝግጅት ምዕራፉ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም የችግኝ ተከላ ቦታ ልየታ፣ የጉድጓድ ዝግጅት፣ ችግኞቹን በየዘርፋቸው የማደራጀትና የማጓጓዝ ተግባራት የሚከናወኑ በመሆኑ ሕዝቡና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You