የተመዘገበው የማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት የሀገር በቀል ኢኮኖሚው ስኬት ማሳያ ነው !

በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7 ነጥብ 9 በመቶ እንደሚያድግ ከኢትዮጵያ መንግሥት በተጨማሪ የዓለም ገንዘብ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም የተጋሩት ትንበያ ነው፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ይኸው ትንበያ ሊሳካ እንደሚችል የሚያሳዩ በርካታ የማክሮ ኢኮኖሚ አመላካች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ግብርና አንዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገቱ ማሳያ ነው፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም በግብርና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ የታየ ሲሆን፤ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በዋናዋና ሰብሎች ላይ የ100 ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ ታይቷል፡፡ በበጋ ስንዴ ልማትም አይነተኛ ለውጥ የታየ ሲሆን፤ አምና በዘጠኝ ወራት ከነበረው የ47 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በዘንድሮው ዓመት ወደ 80 ሚሊዮን ኩንታል ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይም የሩዝ ምርትን አምና በዘጠኝ ወር ውስጥ ከነበረው የ8 ሚሊዮን ኩንታል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ 38 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ከአምናው አንጻር ወተት በሁለት ቢሊዮን ሊትር፣ እንቁላል በአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን፣ ስጋ በ200 ሺህ ቶን ብልጫ ተገኝቷል፡፡

በአጠቃላይ የግብርናው ዘርፍ ያሳየው እምርታ ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ያስቀመጠችውን 7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት ለማሳካት አቅም እንዳላትና የተቀየሰውም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲም ፍሬ እያፈራ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፉም የማምረት አቅም፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የኢነርጂ አጠቃቀም እና የብድር አቅርቦቱ መሻሻል አሳይቷል፡፡

በአገልግሎት ዘርፉም መሻሻሎች የታዩ ሲሆን፤ በተለይም ኢትዮጵያ አየር መንገድ 25 በመቶ በገቢና ተያያዥ ዘርፎች እምርታ አሳይቷል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ካጓጓዛቸው መንገደኞችና ዕቃዎች 5ነጥብ 8ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ወደ ውጭ ከተላኩ ሸቀጦችም 2ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት የታቸለ ሲሆን፤ በበርካታ ችግሮች ተተብትቦ የነበረው የማዕድን ዘርፉም መሻሻሎችን አሳይቷል፡፡ከወርቅ ንግድ ብቻ 275 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ከቅባት እህሎችም 264 ሚሊዮን ዶላር ገቢም ተመዝግቧል፡፡ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትም የተገኘው ገቢ 2ነጥብ 8 ቢሊዮን ደርሷል፡፡

ሆኖም ኢኮኖሚው ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የተገኙበት ቢሆንም ከሥራ ዕድል ፈጠራ፤ ከዋጋ ግሽበትና ከውጭ ዕዳ ተጋላጭነት አንጻር አሁንም ያልተቀረፉ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ቢቻልም አሁንም ካለው ሰፊ የሥራ ፍላጎት አንጻር ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ግድ ይላል፡፡

በሌላ በኩል የዋጋ ግሽበት አሁንም ትልቁ የሀገሪቱ ፈተና ነው፡፡ አሁን ያለው የዋጋ ንረት አምናና ካቻምና ከነበረበት የ33 በመቶ ደረጃ ወደ 23 ነጥብ 3 በመቶ ዝቅ ቢልም አሁንም የኑሮ ውድነቱን በማባባስ ረገድ ፈተና ሆኖ ዘልቋል፡፡ በተለይም የምግብ ዋጋ ንረት 27 በመቶ መሆኑ ችግሩ ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ ነው፡፡

ይህንን ችግር ለመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ጥረት መደረጉ ፤የገንዘብ ዝውውሩን ለመቀነስ የገንዘብ እና ፊሲካል ፖሊሲ በጥብቅ መተግበሩና ነዳጅን በመሳሰሉ ቀጥተኛ የኑሮ ውድነትን በሚያስከትሉ ሸቀጦች ላይ ድጎማ መደረጉ የኑሮ ውድነቱ አሁን ካለበት እንዳይጨምር አስተዋጽኦ ያደረጉ ቢሆንም ካለው የኅብረተሰባችን የመግዛት አቅም አንጻር በቀጣይ በርካታ ጥረቶችን በማድረግ የዋጋ ግሽበቱ ከተቻለ እንዲቀንስ ካልሆነ ባለበት እንዲቆም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ያለባት የውጭ ዕዳ ተጋላጭነት አሁንም ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በተለይም ባለፉት መንግሥታት ጭምር የተወሰዱ እዳዎችን መንግሥት የመክፈል ግዴታ የወደቀበት በመሆኑ ለመደበኛ እና ለካፒታል ዘርፎች ከሚያወጣው ወጪ በተጨማሪ በየዓመቱ ለውጭ አበዳሪ ሀገራትና ተቋማት የሚከፍለው ዕዳ ከፍተኛ ነው፡፡ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታትም ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመክፈል የሀገሪቱን የዕዳ መጠን ለመቀነስ ችሏል፡፡

በአጠቃላይ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መተግበር ከጀመረ ወዲህ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እያስመዘገበችው ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት አበረታች ነው፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተመዘገበው ውጤትም የሚያሳየው ይህንኑ በመሆኑ በተለይም በ2016 በጀት ዓመት የተቀመጠውን የ7ነጥብ9 በመቶ ዕድገት ትንበያ ሙሉለሙሉ ለማሳካት የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል!

አዲስ ዘመን ግንቦት 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You