የሴቶች የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል እና የሴቶች ተጠቃሚነት

‹‹ረጅም ርቀት መጓዝ፤ በመኖሪያ ቤቴ ውስጥ መንቀሳቀስ አልችልም። ደረጃ መውጣትም ይቸግረኛል። በአጠቃላይ እጄን ለመዘርጋት ወይም በጉልበቴ ለመንበርከክ ካለመቻሌም ባሻገር ጣቶቼን ተጠቅሜ የሆነ ነገር እጅግ ያዳግተኛል። ነገር ግን እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ራሴን ችዬ ባልንቀሳቀስም በመጠኑም ቢሆን ሰውነቴ ይታዘዝልኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ብዙ ጊዜ ከቤት አልወጣም። ብወጣም በሸክም ነው። ዕድሜዬ እየጨመረ ሲመጣ በሸክምም ቢሆን መውጣቴ ቀረ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ትምህርት ቤትም መግባት አልቻልኩም›› በማለት ሃሳቧን ያጋራችን ወጣት የውብ ዳር ታሪኩ ናት።

ወጣቷ ወላጆቿ ትምህርት ቤት ያላስገቧት በአካል ጉዳተኝነት ምክንያት መሆኑን ትናገራለች። እቤት በመዋሏ በመጠኑም ቢሆን ይታዘዝላት የነበረው አካሏ መታዘዝ እየተሳነው መምጣቱን ትጠቅሳለች። አንዳንድ ትምህርት ቤቶች እንደ እኔ ዓይነት አካል ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች ለማስተማር የሚያስችል ምቹ ቦታና ሁኔታም እንዳልነበራቸው ወላጆቼ ነግረውኛል ብላናለችም።

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 41 ንዑስ ቁጥር 5 መንግሥት አቅም በፈቀደው መጠን ለአእምሮና ለአካል ጉዳተኞች እንክብካቤ ያደርጋል የሚል ሕግ መደንገጉን ወጣት የውብዳር ታስታውሳለች። በዚሁ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 1 ያለ ምንም ዓይነት ልዩነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው መጠን የትምህርት፤ የጤና እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ መሆን እንደሚችልም መስፈሩን ትገልፃለች። ሆኖም ትምህርትን በተመለከተ እሷን ጨምሮ በርካታ እንደ እሷ የእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸውና ሌሎች አካል ጉዳተኞች ለረጅም ዓመታት የትምህርት ዕድል ከማግኘት ተገልለው እንደቆዩ ታወሳለች። 20 ዓመት እስኪሞላት ድረስ እሷ የትምህርት ዕድል ሳታገኝ መቆየቷንም እንደ ማሳያ ትገልፃለች።

የየውብዳር ታሪክ የሴቶች ተጠቃሚነት በተሟላ መልኩ አለመከበሩን ማሳያ ነው። በተለይም አድሏዊ አመለካከት ገና ያልተቀረፈና የትኩረት ማነስም እንደተነፈጋቸው ማሳያ ነው። ሴቶች በሁሉም ማሕበረሰብ ሊባል በሚችል ደረጃ ለዘመናት አድሏዊ ልዩነት እየተደረገባቸው እና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሳይከብሩላቸው መቆየታቸውን ከታሪክም ሆነ ከየውብዳር ሕይወት መመልከት እንችላለን።

እነዚህን የመብት አለመከበር እና ፆታን መሠረት ያደረጉ ልዩነቶችን ለማስወገድ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ሀገር አቀፍ ሕጎች ቢኖሩም የሴቶችን መብቶች ሙሉ ለሙሉ ማረጋገጥ አልተቻለም።

እስከ ዛሬ በሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ዙሪያ በተሠሩ ሥራዎች የተነሳ ጉልህ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ሙሉ በሙሉ የፆታ እኩልነትን ለማስመዝገብ ታላቅ ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ በመቀጠል ላይ ነው። ሴቶች በተለያዩ የዓለም ሀገራት መድልዎ፣ ጥቃት፣ የትምህርትና የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት ውስንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ልዩነቶች ይደርስባቸዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በሴቶች እና በወንዶች ያለው የኢኮኖሚ ልዩነት ስንመለከት፤ ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በአማካይ ከወንዶች በ23 በመቶ ያነሰ ገቢ ያገኛሉ። የሴቶች በአመራር ቦታዎች ላይ ያላቸው ውክልናም ዝቅተኛ ነው። በፓርላማ ውስጥም መቀመጫ ማግኘት የቻሉት 24 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ብቻ ናቸው።

በኢትዮጵያም ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል የሚታይበት ቢሆንም አሁንም በርካታ ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉት እሙን ነው። ሆኖም ኢትዮጵያ የሴቶችን ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅናና ከለላ እንዲኖረው በማድረግ ጭምር በከተማና በገጠር የሚኖር ሴቶች መብታቸው ተረጋግጦላቸው እንዲኖሩ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው።

በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የሴቶችን ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃማነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። መንግሥት እንደ አዲስ ባዋቀረው ካቢኔ ውስጥ 50 በመቶውን ሴቶችን እንዲይዙ በማድረግ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ አርአያነት ያለው ተግባር ማከናወን ተችሏል።

የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ የተሠራውም ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው። ከጤና ጋር በተያያዘም ‹‹አንድም ሴት በወሊድ የተነሳ አትሞትም›› በሚል ሴቶች የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የጤና ተቋማትን ከማስፋፋት ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅምም ለማሳደግም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

ከእነዚህ ጥረቶች አንዱ በአዲስ አበባ አስተዳደር ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃው የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል አንዱ ማሳያ ነው። ማዕከሉ በዋነኛነት በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን በመቀበል ሙያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ፣ ክትትልና ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የሚያስችል ሲሆን በአንድ ዙር ብቻም 10 ሺህ ሴቶችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም ያለው ነው። “ለነገዋ” በሚል የተሰየመው ይኸው የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የሴቶችን እኩልነትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ሚና ይኖረዋል።

የሴቶች የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሴቶች ዕምቅ አቅማቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙ የሚያስችል ግዙፉ ማዕከል ነው። የማህበረሰባችን ግማሽ ያህል ቁጥር የሚሆኑትን ሴቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ያላደረገ ሰላምና ልማት ውጤት እንደማያመጣ የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተደራራቢ ችግሮቻቸውን በማቃለል ሕይወታቸውን ለማሻሻል አበረታች ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ከአዲስ አበባ አስተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በ53,700 ካሬ ቦታ ላይ ያረፈው ይህ ማዕከል የየራሳቸው ኪነ-ሕንጻዊ ውበት ያላቸው 16 ደረጃቸውን የጠበቁ የሕንጻ ብሎኮችን፣ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ፣ ግዙፍ ኤልኢዲ ስክሪን የተገጠመለት የመዝናኛ አምፊ ቴአትር፤ 4.1 ሄክታር በላይ ስፋት ላይ ያረፈ የአትክልት እርሻ ማሳ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው የራሱ የከርሰ ምድር ውሃ ያካተተ ራሱን ችሎ መንደር ተብሎ ሊጠራ የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

በአንድ ዙር 10,000 የጾታዊ ጥቃት ሰለባ እና ለማህበራዊ ቀውስ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ የምግብ ፣ የመኝታና አልባሳት ፣ ሌሎችንም ሁሉን አቀፍ መሠረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦ ከሶስት እስከ ስድስት ወራት የሚቆይ ሞያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ድጋፍና ስልጠናዎችን በመስጠት ለሥር-ነቀል ለውጥ እንደሚያበቃ የሚታመነው ማዕከሉ የሥነ-ውበት፣ የሞግዚትነት፣ የመስተንግዶ፣ የአሌክትሪክና የሸክላ እንዲሁም የእንጨት ሥራዎች፣ የጋርመንት ስልጠናዎች እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል።

ማዕከሉ ሁሉን አቀፍ ላብራቶሪዎች ፣ አልትራሳወንድ ፣ ኤክስሬይ ፣ እንዲሁም የማገገሚያ ማእከል (ሪሀቢሊቴሽን ሴንተር) ያካተተ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልነትን የሚያሟላ የሕክምና መስጫ ያለው ሲሆን ዘመናዊ ቤተ-መጻሕፍት ፣ የቤት ውስጥ ስፖርት ማዘውተሪያ ጂምናዚየም ፣ ምቹ የመመገቢያ ማዕከሎች እንዲሁም ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ አዳራሾችን የመሳሰሉ ክፍሎችም ተካተውበታል።

የልዩ ልዩ ሙያ ንድፈ ሃሳብ ስልጠና ፣ የተግባራዊ ልምምድና የሰርቶ ማሳያ ማዕከላት እንዲሁም የሕፃናት ማቆያና እንክብካቤ እና ሥነ-አዕምሯዊ እድገት ክትትልና ልህቀት ክፍሎችም በግዙፉ የሴቶች የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ተሰርተዋል።

የቴክስታይል ማሰልጠኛ፣ የምንጣፍ ጥልፍ ሥራ ስቱዲዮ ፣ የፀጉር ሥራ ፣ ኮስሞቲክስና ሜክአፕ ስቱዲዮ፣ የሸክላ፣ እንጨት ሥራ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ሥራ ስልጠና እና መሰል የንድፈ ሃሳብና የተግባር ልምምድ ሰርቶ ማሳያ ክፍሎች፣ በቂ ግብዓትና መርጃ መሳሪያዎች አቅርቦትም ተሟልተውለታል።

ሴቶች በማዕከሉ ቆይታቸው ከሚያገኙት የሥነ ልቦና ድጋፍ በተጨማሪ በሥነ-ውበት፣ በከተማ ግብርና፣ በምግብ ዝግጅት፣ በከተማ ውበት አጠባበቅና በኮምፒዩተር ሙያ ስልጠና በመውሰድ ወደ ሥራ እንዲገቡም ዕድል ይፈጥራል። ማዕከሉ በውስጡ የተሃድሶ ስልጠና የሚሰጥባቸው የክህሎት ማበልፀጊያ፣ የማሰልጠኛ ማዕከላት፣ የሥነ-ልቦና እና ምክር አገልግሎትንም ያቀፈ ነው።

ይህ ማዕከልም መንግሥት የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ካሉ ዘርፍ ብዙ ሥራዎች አንዱ ማሳያ ነው። የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጾታ ተኮር የሆኑ ፖሊሲዎች መተግበር አለባቸው፤ ከእነዚህም መካከል ሴቶች እኩል ክፍያ፣ ብድር የማግኘት ዕድል እና የሥራ ፈጠራ ድጋፎችን እንዲሁ ሊያገኙ ይገባል። የግል ሴክተሩም የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን እንዲያበረታታ እና አድሎአዊ ድርጊቶችን እንዲያስወግድ ማበረታታት አስፈላጊ ነው።

ሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ መሻሻሎች ቢታዩም አሁንም የተለያዩ ክፍተቶች አሉ። እነዚህን ክፍተቶች ለማጥበብም የሕግ ማሻሻያዎችን መተግበር፣ የትምህርት እና ግንዛቤን ማስበጫዎችን ማድረግ፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ በማብቃት፣ ጤናን እና ደህንነትን በማረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን በማጎልበት የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነትን ለማምጣት መሠራት አለበት። እያንዳንዷ ሴት መብቷን የምትጠቀምበት እና አቅሟን የምታሳይበት ማህበረሰብ እንዲፈጠር ግለሰቦች፣ ማህበረሰቦች እና መንግሥታት በጋራ መትጋት አለባቸው።

ከዚህ ማዕከል መገንባትና ወደ ሥራ መግባት ጎን ለጎንም ለዚሁ ጎን ለጎንም የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል ከሁሉም ክፍለ ከተማ ለተመለመሉ ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ ለሌላቸው አንድ ሺህ ሃምሳ አንድ ሴቶች ከአስር ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተስማሚ ቴክኖሎጂና የሥራ ማስጀመሪያ ድጋፍ በማድረግ ወደ ሥራ አስገብቷል።

ሰርተው ማደር ሲችሉ የሰው እጅ ተመልካች የሆኑት እነዚህ ሴቶች ይህንን ድጋፍ ማድረጋቸው ራስን የመቻል ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ከዚህም በላይ ከትዳር አጋር ጋር በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ግጭት ተወግዶ ልጆችን በሰላም ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።።

በተለይም መሥራት እየቻሉ ማጣት እግር ከወርች የታሰሩ ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ መደረጉ የሴቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ የሚጠቀስ ነው።

መስከረም ዮሐንስ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You