ደሞ ሶስተኛ ሳተላይት !

ሀገራችን ሶስተኛዋን ሳተላይት ወደ ሕዋ ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ መሆኗ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋ ማድረጉ ለዛሬው መጣጥፌ መነሻ ሆኖኛል። በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሕይወት፣ ኑሮ፣ ትምህርት ፣ ምርምር ፣ ልማት ፣ እድገት ፣ ብልፅግና ያለ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን እና ያለ እስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ሊታሰብ አይችልም:: በእነ ግብፅ ናይል ሳትም ሆነ አረብ ሳትና ሌሎች ሳተላይት ላይ ጥገኛ ሆኖ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ብሎ መመጻደቅ ልግጫ ነው የሚሆነው:: በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ሦስተኛዋን ሳተላይት ወደ ሕዋ ለማምጠቅ በዝግጅት ላይ መሆኗን የሀገሪቱ ሕዋ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዚያ ሰሞን ማስታወቁ ፤ ለዛሬው መጣጥፌ እርሾ ሆኗል።

ETRSS-2 ተብላ የምትጠራው ሦስተኛዋ ሳተላይት ከዚህ ቀደም እንደመጠቁት ሳተላይቶች ሁሉ የመሬት ምልከታ ታደርጋለች ። ሳተላይቷ ከሌሎቹ የተሻለ የምስል ጥራት እንደምትልክም ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ETRSS-1 እና ET-Smart-RSS የተሰኙ ሳተላይቶችን ማምጠቋ የሚታወስ ነው። ከሦስት ዓመት በፊት የመጠቀችው ሳተላይት በሕዋ ላይ የመቆየት እድሜዋ 2 ዓመት ተኩል ቢሆንም ፣ እስካሁን ድረስ አገልግሎት እየሰጠች እንደሆነ ፤ ሁለተኛዋ ሳተላይት ግን በ6 ወሯ ገደማ እድሜዋን ጨርሳ አልፋለች ይለናል ቢቢሲ በዘገባው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነችውን ETRSS-01 ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ሕዋ የላከችው ከሦስት ዓመት በፊት ነበር። ሳተላይቷ ለግብርና፣ ለማዕድን፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ጥበቃ እና ለመልከዓ ምድር ጥናት የመረጃ አገልግሎትን እስካሁን ድረስ እየሰጠች ትገኛለች። ሳተላይቷ በቻይና መንግሥት የተገነባች ሲሆን፣ በግንባታው ሂደትም በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ከቻይና አጋሮቻቸው ጎን ተሰልፈው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ከሕዋ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተገኘ መረጃ ያወሳል። ሦስተኛዋ ሳተላይት ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው። የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያ ሳተላይት ከቻይና በልገሳ በተገኘ 6 ሚሊዮን ዶላር እንደተገናባች እና በአጠቃላይ 210 ሚሊየን እንደፈጀች በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ሦስተኛውን ሳተላይት ለማምጠቅ ያስፈለገበት ምክንያት የአገልግሎት እድሜዋን አልፋ እስካሁን አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለችውን ሳተላይት ለመተካት መሆኑ ኢንስቲትዩቱ ይገልጻል። ይህንንም ዕቅድ ለማሳካት የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት መካሄዱን እና ለግንባታው የሚያስፈልገው ዝግጅትም እየተደረገ ነው። የተሻለ የምስል ጥራት ትልካለች የተባለችውን ET-Smart-RSS ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከዚህ ቀደም የመጠቁ ሳተላይቶች ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለግብርና እና ለከተሞች ልማት እንዲሁም ለሌሎች ተቋማት ሥራ ጠቃሚ የሆኑ የተለያዩ ምስሎችን ልከዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን ሳተላይት ከማምጠቋ በፊት እነዚህን መረጃዎች ሳተላይት አምጥቀው ፎቶ ከሚያስነሱ ሀገሮች በመግዛት ትጠቀም ነበር። በዚህም ሳቢያ የሳተላይት መረጃውን ለመግዛትም በዓመት 250 ሚሊየን ብር ስታወጣ የቆየች ሲሆን ይህም ከዓመት ዓመት ይጨምር እንደነበር የዘርፉ ባለሙያዎች ከዓመታት በፊት የተሠራ ጥናትን በመጥቀስ ይናገራሉ። አፍሪካ ውስጥ ካሉ ሀገራት በሕዋ ጥናት ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ እና ግብፅ ጥሩ ስም መገንባት የቻሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ከእነርሱ አንጻር ገና ጀማሪ ናት።

የሕዋ ጥናት በዓለም ላይ በፍጥነት እየዘመኑ ካሉ ዘርፎች መካከል ይጠቀሳል። የሰው ልጅ እስከሚኖርባት ምድር ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ካለው ፍላጎት ባሻገር ሕዋን አብጠርጥሮ ለማወቅ ጥረት እያደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ ሳተላይቶች ዋነኛ መሳሪያዎቹ ናቸው። ከህዋ ላይ በመሆን መሬትን ማሰስ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ተግባር ነው። ሳተላይቱ መረጃ ሲሰበስብ ይህ ቀረህ አይባለውም። ከግዙፍ ክንውኖች እስከ ጥቃቅን እንቅስቃሴዎች ይመዘግባል።

እንደ ባለሙያዎች አባባል ሳተላይቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው። የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት አስቀድሞ ለመተንበይ፣ ደኅንነትን ለመጠበቅ እና ለሌላም ይውላል። የአየር ንብረት ለውጥ የመላው ዓለም ስጋት በሆነበት በዚህ ዘመን፤ አንዳች ተፈጥሯዊ አደጋ ከመድረሱ በፊት አስቀድሞ መረጃ ማግኘት የበርካቶችን ሕይወት ለመታደግ ያስችላል።

ለአብነትም በአንድ አካባቢ ያሉ የዛፎችን ቁጥር፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች መረጃዎች ከተሰበቡ በኋላ እንደ ጎርፍ ያሉ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት መተንበይ የሚቻልበት ዕድል አለ። ግብርና ቀዳሚ መተዳደሪያ በሆነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የቱ አካባቢ ምርታማ ነው? የአየር ንብረት ለውጥ ሊኖር ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች በቀላሉ ለመመለስ የሳተላይት መረጃ አስተማማኝ ና አስፈላጊ ነው።

አንድ የግብርና አካባቢን የሚያሳይ የሳተላይት ፎቶግራፍ ስለ እርሻ መሬቱ ፣ ስለ ውሃው፣ ስለ አፈሩ ዝርዝር መረጃ ይሰጣል። መረጃዎቹን በመጠቀም ምርታማ የሆኑ አካባቢዎችን መለየት እና የሚገኘውን የምርት መጠን በትክክል ማወቅም ይቻላል። በተጨማሪም ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ ፋብሪካዎች የት መገንባት አለባቸው? ለሚለው ጥያቄ ከሳተላይት የሚገኙ መረጃዎች ጠቃሚ ናቸው።

ሳተላይት ማምጠቅ ብዙ ትርጉምና አንድምታ እንዳለውና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያደጉ ሀገራት የዕድገት ሚስጥርም መነሻው ይህ ነው። ይህ ጅምር ለኢትዮጵያ ዕድገት ትልቅ ትርጉም አለው ይላሉ የዘርፉ ልሒቃን። በዜጎችና ምሁራን ዘንድም አዲስ ነገር ለመፍጠር ትልቅ መነሳሳት ይሆናል። የምትመጥቀው ሳተላይቷ ለከተማ እና ገጠር መሬት አስተዳደር፣ ማህበራዊ ጉዳዮች፣ ሕዝብ አሰፋፈር፣ ምርጫና ሕዝብ ቆጠራ፣ ለማህበረሰብ ልማቶችና ተያያዥ ጉዳዮች መረጃ ለመሰብሰብ ትልቅ ድርሻ ይኖራታል። በድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ተላላፊ ወንጀሎች፣ ሕገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በሀገሪቱ የሚከናወኑ ታላላቅ የልማት አውታሮችን ለመጠበቅና ከጥቃት ለመከላከልም አበርክቶዋ የጎላ ነው።

ማዕድናት፣ መሬት፣ ውሃና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀም፣ የገጠርና የከተማ መሬት አያያዝና አጠቃቀምና ፍትሃዊ አሠራርን መሠረት ለማስያዝ ብሎም አዳዲስ ፖሊሲዎችን ለማርቀቅም ከሳተላይት የሚገኘው መረጃ የላቀ ሚና አለው። እንደ ዘርፉ ምሁራን ገለፃ፤ አሁን ባለው ጅምር ኢትዮጵያ በስፔስ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ በቀላሉ ትገባለች። ይህም በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ የመወሰንና የመደራደር ሚና ይኖራታል። ኢትዮጵያ የሌሎች ሀገራት መረጃ ስለሚኖራት በመተባበርና በመከባበር እንድትሠራ ያግዛታል። ሉዓላዊ ሀገራትን መብት እንዳይጣስም ሌሎች ሀገራትም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ከማገዙ ባሻገር የመደራደር አቅም ስለሚፈጥርላት ተሰሚነቷ ይጨምራል።

ሀገራችን በሚቀጥሉት 15 ዓመታት የሳታላይቶቿን ቁጥር 11 ለማድረስ አበክራ በመሥራት ላይ መሆኗን ከኢንስቲትዩቱ ከመስማት በላይ ለዚህ ትውልድ ልብን በሀሴት የሚሞላ ምን ብስራት አለ !? ይሁንና ሀገራችን ከ3ና 4ሺህ ዓመታት በፊት በህዋ ምርምር ዘርፍ የዛሬዎቹን ልዕለ ኃያላን ከፊት ሆና ስትመራ እንደነበር የጥንት ብራና መጻሕፍትና ስንክ ሳሮች ዋቢ ከመሆናቸው ባሻገር ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ሕብረት በሀገራችን ልዕልት፣ ንግሥትና ንጉሥ ስም ሕብረ ከዋክብት constellations መሰየሙን ስንቶቻችን ይሆን የምናውቀው!? ስለ ቀደምት ኢትዮጵያውያን የሥነ – ፈለክ / የሕዋ / እውቀትና በዘመን አቆጣጠር ምን ያህል የተራቀቁ እንደነበሩ በማስረጃ የሚተነትነው የሮዳስ ታደሰና ጌትነት ፈለቀ (ሁሉም ፒ ኤች ዲ ሰርተዋል):: በጋራ በደረሱቱ ፤ “አንድሮሜዳ” መጽሐፍ 5ኛ ዕትም ላይ ፤”… ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ያሉ የውጭው ዓለም ታሪክ ፀሐፊዎች …ʿ ጥንታዊ ዘር ʾ በመባል የምትታወቀውን ኢትዮጵያን … አውሮፓና እስያ ባልሰለጠኑበት ዘመን …ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሑፍ ፣ ሒሳብ ፣ ግብርና ፣ ሕክምና ፣ የክዋክብት ጥናት … የኢትዮጵያውያን ነባር ሀገር በቀል እውቀቶች እንደነበሩ ተናግረዋል::… ” ይህ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለሥነ ፈለክ የማይናወጥ መሠረት እንደነበራቸው ያረጋግጣል::

ይሁንና ሀገራችን ከ3ና 4ሺህ ዓመታት በፊት በህዋ ምርምር ዘርፍ የዛሬዎቹን ልዕለ ኃያላን ከፊት ሆና ስትመራ እንደነበር የጥንት ብራና መጻሕፍትና ስንክ ሳሮች ዋቢ ከመሆናቸው ባሻገር ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ሕብረት በሀገራችን ልዕልት ፣ ንግሥትና ንጉሥ ስም ሕብረ ከዋክብት constella­tions መሰየሙን ስንቶቻችን ይሆን የምናውቀው!? ስለ ቀደምት ኢትዮጵያውያን የሥነ – ፈለክ / የሕዋ / እውቀትና በዘመን አቆጣጠር ምን ያህል የተራቀቁ እንደነበሩ በማስረጃ የሚተነትነው የሮዳስ ታደሰና ጌትነት ፈለቀ (ሁሉም ፒ ኤች ዲ ሰርተዋል):: በጋራ በደረሱቱ ፤ “ አንድሮሜዳ ” መፅሐፍ 5ኛ ዕትም ላይ ፤”… ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ያሉ የውጭው ዓለም ታሪክ ፀሐፊዎች … ʿጥንታዊ ዘርʾ በመባል የምትታወቀውን ኢትዮጵያን … አውሮፓና እስያ ባልሰለጠኑበት ዘመን …ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሑፍ ፣ ሒሳብ ፣ ግብርና ፣ ሕክምና ፣ የክዋክብት ጥናት …የኢትዮጵያውያን ነባር ሀገር በቀል እውቀቶች እንደነበሩ ተናግረዋል::… ” ይህ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለሥነ ፈለክ የማይናወጥ መሠረት እንደነበራቸው ያረጋግጣል::

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የጥንት ስልጣኔ ባለቤት መሆኗን እና ለሥነ – ፈለክ ምርምር ወረት፣ መነሻ እንደነበራት የሚያረጋግጡ የቀደምት ሊቃውንት እማኝነት ከፍ ሲል በተገለፀው መጽሐፍ እንደሚከተለው ተዘግቧል:: “60 ዓመት ቅድመ ልደት ክርስቶስ የነበረው ዲዎዶርስ ሴኩለስ የተባለ የታሪክ ሊቅ ‘ አውሮፓውያን ኋላ ቀር እድገት አኗኗር ላይ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ታላቅ ስልጣኔ ላይ የነበረች …ኢትዮጵያውያን ለግብጻውያን ስልጣኔ ያስጀመሩና እስከ ሕንድ ድረስ የገዙ ናቸው::

‘… በ700 ዓ.ም የነበረው የቤዛንታይኑ እስቲፋንስ ባካሄደው ጥልቅ ጥናት ‘ ኢትዮጵያ መሬታችን ላይ የተመሰረተች የመጀመሪያ ሀገር ናት ‘ ሲል አርኖልድ ኸርማን ሉድዊግ የተባለ የጀርመናዊ የታሪክ ፀሐፊ ደግሞ ‘ ኢትዮጵያን የመሰለ ጥንታዊ ሀገር ወዴት ይገኛል!? ‘ ሲል ይሞግታል … ከ800 ዓመት ክርስቶስ ልደት በፊት የኖረው ሆሜር አሊያድና እና ኦዲሴይ በተባሉ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹ ኢትዮጵያውያን ‘ እስከ መሬት ጫፍ ድረስ የሚኖሩና ከአምላክ ጋር ቅርበት ያላቸው ‘ በማለት ይገልጻቸዋል::

የታሪክ አባት በመባል የሚታወቀው ሔሮዶቶስ ኢትዮጵያውያንን ‘ከሰሐራ በታች የሚኖሩ፣ ጥቁር ቆዳ ያላቸው …ብልሆች፣ በዓላቶቻቸውና ሀሴታቸውም ሳይቀር አማልክትን ስለሚያስደስት የአማልክት አምላክ እየሄደ በዓላቱን በደስታ አብሯቸው ያሳልፋል ‘ ብሏል:: …ዲዮዶር የተባለ የሮም ፀሐፊ ደግሞ ‘ከግብፅ በፊት ስልጡንና ገናና ነበረች:: ግብፅን ቀኝ ገዝታ 18 የኢትዮጵያ ነገሥታት ተፈራርቀውባታል:: …’ ይላል:: “መጽሐፉ ሀገራችን የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት መሆኗን በአደባባይ ካስመሰከረ በኋላ በዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ሕብረት የተሰጣትን ቦታ ይተነትናል :: “…ሕብረ ከዋክብት constellations ማለት በሰማይ ላይ የሆነ ዓይነት ቅርፅ የሚሰራ የከዋክብት ስብስብ ሲሆን ቅርጹም ከማይቶሎጂ ጋር በተያያዘ መልኩ የሰው፣ የእንስሳት ወይም ሕይወት የሌለው ነገር ሆኖ ሊገለጽ ይችላል::…ዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ሕብረት በ1930 ዓ.ም ከ88 ሕብራተ ከዋክብት ውስጥ ሶስቱን ማለትም አንድሮሜዳን ፣ ካሲዮፕያንና ሴፌውስን በኢትዮጵያውያን ስም መዝግቧል:: … አንድሮሜዳ የኢትዮጵያ ልዕልት ስትሆን ፤ ካሲዮፕያን ደግሞ የኢትዮጵያ ንግሥት ናት:: ሴፌውስ ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሥ ነው :: …”

ለስነ ፈለክ አርፋጅም ፣ ኮራጅም አይደለንም:: አልፋ ነን:: ለ4 ሺህ ዓመታት ተዳፍኖ የነበርን ፍም በETRSS – 1 ሳተላይት እፍ ብለን አፈገግነው እንጂ:: ከፍ ብለን እንደተመለከትነው በህዋ ጥበብ ፣ እውቀት ከበኩራን ተርታ ተሰላፊ ነበርን:: ለእልፍ አእላፍ ዓመታት የተጠናወተን አፍርሶ ከዜሮ የመጀመር አባዜ ብኩርናችንን ቢያስነጥቀንም:: የአክሱም ሀውልት ፣ የላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናት ፣ የፋሲል ግንብ ፣ የጥያ ትክል ድንጋዮች ሳያፈርሱ እንዴት እንዳቆዩን ይገርመኛል::

ለነገሩ ከላይ የተዘረዘሩት ቅርሶቻችን ወይራ፣ ኮሶ፣ ቀረሮ፣ ግራር ቢሆን ኖሮ ገነዳድሰው፣ ቆራርጠው፣ ፈላልጠው፣ ሙቀዋቸው፣ ምሰሶ፣ ግርግዳ አድርገዋቸው ነበር:: ለዚህ ትውልድም አይቆዩትም ነበር:: ከሶስት ዓመት በፊት ወደ መጠቀችው ሳተላይት ስንመለስ ከዛ ባለ ብዙ ገድላት የእነ ሴፌውስ ትውልድ ጋር ድልድይ ሆና እንደገና ታገናኛለች:: መንኮራኮር ሆናም በምናብ በምልሰት flash back 4ሺህ ዓመት ወደ ኋላ ትወስደናለች::

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You