የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገጠር መሬት አስተዳደር አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ የመሬት ይዞታን በማስያዝ ብድር ማግኘት የሚያስችል ድንጋጌ ተካቶበት የቀረበውን አዋጅ ከሰሞኑን አፅድቋል።
በረቂቅ አዋጁ እንደተብራራው አርሶና አርብቶ አደሮች ከመሬታቸው ያለ መፈናቀል መብታቸውን ማስከበር አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት፣ በመሬት የመጠቀም መብትን በማስያዝ ብድር ማግኘት እንዲችሉ ከሀገሪቱ የመሬት ፖሊሲ ጋር በማጣጣም በጥንቃቄ ታስቦ የተዘጋጀ አዋጅ እንደሆነም ተገልጿል።
የገጠር መሬትን ዋስትና አድርጎ ማስያዝን የሚመለከት የሕግ ድንጋጌ እስካሁን አለመኖሩ በረቂቁ ተገልጿል። በዚህም በአሁኑ ጊዜ በአሠራር እየታዩ ያሉ የአነስተኛ የገንዘብ ተቋማት የገጠር መሬት ይዞታ መብትን በመያዝ ብድር የመስጠት ተግባር፣ ለሕጉ መሻሻል አስፈላጊ መሆኑ በረቂቁ ተመልክቷል። የገጠር መሬት ባለቤት የመጠቀም መብቱን በየክልሉ በሚወጡ ሕጎች በሚወሰን የጊዜ ገደብ አማካይነት፣ ለፋይናንስ ተቋማት ለብድር ዋስትና ማስያዝ እንደሚቻል ተገልጿል።
በተጨማሪ ባለይዞታዎች በመሬታቸው የመጠቀም መብታቸውን በማስያዝ፣ የዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችና ግብዓቶችን የሚያገኙበት አሠራር ማመቻቸትን ያለመ ስለመሆኑ በረቂቁ ተብራርቷል። አበዳሪዎች ሕጋዊ የፋይናንስ ተቋማት ብቻ ሲሆኑ፣ አራጣ አበዳሪነትን ለመከላከል ግለሰቦች በሕጉ መሠረት አበዳሪ ሆነው በመሬት የመጠቀም መብትን እንደ ማስያዣ ሊይዙ እንደማይችሉ በረቂቁ ተደንግጓል። ግብዓት ለመግዛት የገንዘብ እጥረት የሚያጋጥማቸው መሬታቸውን ያከራዩ የነበሩ ባለይዞታዎች፣ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን በማስያዝ ብድር ወስደው አምርተው ብድራቸውን እንዲመልሱ የሚያስችል መብት ስለመሆኑም በረቂቁ ተጠቁሟል።
በአዋጁ እንደተቀመጠው ባለይዞታው ብድሩን መመለስ ባይችል ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ አበዳሪው በመሬቱ የሚጠቀምበት የጊዜ ጣሪያ ከአሥር ዓመት መብለጥ የለበትም። ክልሎች እንደ ክልላቸው ተጨባጭ ሁኔታ ከአሥር ዓመት ማሳነስ አይችሉም። ከአሥር ዓመት ከበለጠ ግን ውሉ ሕገወጥ እንደሚሆን ተደንግጓል። የመሬት ባለይዞታ የመጠቀም መብቱን በየክልሉ በሚወጡ ሕጎች በሚወሰን የጊዜ ገደብ ለፋይናንስ ተቋማት ለብድር ዋስትና ማስያዝ እንዲችሉ የሚያደርግ ስለመሆኑ ተጠቅሷል።
ይህንን አዋጅ በተመለከተ ለአዲስ ዘመን አስተያየታቸውን የሰጡት የሲዳማ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ሐጢያ እንደሚናገሩት፤ ከዚህ በፊትም በብሔራዊ ባንክ በተቀመጠው መመሪያ መሠረት አርሶ አደሮች የብድር አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ አሠራር ነበር። ነገር ግን ባንኮች ኪሳራን በመፍራት ለግብርና ዘርፍ የሚሰጡት የብድር መጠን ከሌላው ዘርፍ አንፃር አነስተኛ ነው።
ባንክ በራሱ በኩል ለአርሶ አደሮች ብድር መስጠት እንኳ ባይችል በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በኩል አርሶ አደሮች የብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል አሠራር አለ። ያም ቢሆን ግን በተፈለገው ልክ ውጤታማ አይደለም። አዲሱ መመሪያ ይህንን በመቅረፍ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ይናገራሉ።
ባንኮች ለአርሶና አርብቶ አደሮች ብድር መስጠት የውዴታ ግዴታቸው ነው የሚሉት አቶ ታደሰ፤ ባንኮች ከሚሰጡት ጠቅላላ ብድር አምስት በመቶ የሚሆነው ለግብርናው ዘርፍ ማዋል አለባቸው የሚል መመሪያ መኖሩን ይጠቅሳሉ። ከዚህ አኳያ አሁን ለዘርፉ የሚሰጡት ብድር አነስተኛ ስለመሆኑ ግልጽ መሆኑን ጠቁመው፤ የእዚህ ምክንያት ደግሞ ባንኮች ለብድር መያዣነት የሚጠይቁት ነገር በአርሶ አደሩ በኩል በቀላሉ መሟላት የሚችል አይደለም ይላሉ። አያይዘውም አዲሱ አዋጅ ይህንን አሠራር ማቅለል የሚችል ነው ይላሉ።
ባንኮች የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ኃይል እንደመሆናቸው የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ደግሞ ግብርናው በመሆኑ ለዘርፉ ብድር የማቅረብ የሞራል ግዴታ አለባቸው የሚሉት አቶ ታደሰ፤ የሲዳማ ባንክ ከተለያዩ ባለድርሻ አካለት ጋር በተለይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተወሰነውን ድርሻ የብድር ማስያዣ እየሰጡ በገጠር አርሶ አደሩ የባንክ ብድር ተጠቃሚ እንዲሆን እየሠሩ እንደሆነ ይናገራሉ።
ገበሬው በፋይናንስ ካልተደገፈ የሀገርን ኢኮኖሚ በሚፈለገው ልክ ማሳደግ አይቻልም የሚሉት አቶ ታደሰ፤ ገበሬው የፋይናንስ ድጋፍ አግኝቶ ማምረት ካልቻለ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ አይቻልም። ይህ ካልሆነ ደግሞ የኑሮ ጫነው እየበረታ ይሄዳል። ከዚህ አንፃር አርሶ አደሩ ግብርናው ዘመናዊ አድርጎ እንዲሰራ ባንኮች የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት የማዋጣት ግዴታ አለባቸው። አዲሱ አዋጅ ይህንኑ በማጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይናገራሉ።
አቶ ታደሰ ለአብነት ሲጠቅሱ፤ በተለያየ መልኩ ተደራጅተው ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የአቦካዶ ምርት እያቀረቡ ያሉ አርሶ አደሮች አሉ። እነዚህ ግለሰቦች እራሳቸውን የሚደግፉት በማይክሮ ፋይናንስ በኩል አነስተኛ ብድር እያገኙ ነው። ከዚህ አንፃር አዲሱ መመሪያ ባንኮች የአርሶ አደሩን መሬት በብድር መያዣ ይዘው ብድር ለገበሬው እንዲሰጡ በማድረግ ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነትና ለግብርናው መዘመን የሚኖረው አበርክቶ ቀላል አይደለም ይላሉ።
በልማት ባንክና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ለግብርናው ዘርፍ ብድር በማመቻቸት ረገድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ የሚሉት አቶ ታደሰ፤ አዲሱ መመሪያ ሌሎች ባንኮችም የግል ባንኮችም ለግብርናው ከዚህ በፊት ከሚሰጡት ብድር የተሻለ እንዲሰጡ የሚያበረታታ እንደሆነ ይገልፃሉ።
አርሶ አደሩ የፋይናንስ ተጠቃሚ ሆኖ ግብርናው እንዲዘምን የአርሶ አደሩ ተንቀሳቃሽ ያልሆኑ ንብረቶች የሚመዘገቡበት ሥርዓት ጠንካራ መሆን አለበት የሚሉት አቶ ታደሰ፤ ብዙ ጊዜ ባንኮች ለአርሶ አደሩ ብድር እንዳይሰጡ የሚያደርገው የምዝገባ ሥርዓቱ ደካማ መሆን ነው ይላሉ። ለምሳሌ ከተማ ላይ ያለ ቤት ወይም መኪና አግባብነት ባለው መልኩ ተመዝግቦ ይቀመጣል። አንድ ሰው ይህንኑ ንብረቱን አስይዞ ብድር ያገኛል። የእዚህ ዓይነት አሠራር ግን በገጠር የለም። ይህ አሠራር መሻሻል እንዳለበት ያመለክታሉ።
ባንክ ብድር የሚያቀርበው ከሕዝብ የሰበሰበውን ገንዘብ ነው የሚሉት አቶ ታደሰ፤ ከሌላ ከየትም አያመጣውም፤ የተሰጠው ብድር በጊዜውና በሕግ አግባብ ሳይመለስለት ሲቀር በመያዣነት የያዘውን ንብረት ለሶስተኛ ወገን በመሸጥ የሰጠው ገንዘብ መመለስ የሚችልበት አሠራር መዘርጋት ተገቢ እንደሆነ ገለጸዋል። ይህ አካሄድ ካልተጠናከረ የባንኮችን መተማመን የሚሸረሽር በመሆኑ ውጤታማ አይሆንም ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዳኪቶ ዓለሙ በበኩላቸው፤ በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ በወጣው ሪፖርት በግልጽ እንዳስቀመጠው የንግድ ባንኮች ለግብርናው እየሰጡት ያለው የብድር መጠን በተለይ በገጠር ከሁለት በመቶ ያነሰ ነው። የንግድ ባንኮች ለሠራተኞቻቸው ከሚሰጡት ብድር መጠን ጋር ተመሳሳይ ነው ይላሉ።
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ላይ እንደተናገሩት፤ ንግድ ባንኮች ከተቋቋሙበት ዓላማ አንፃር የሚሰጡት የብድር መጠን ማነሱ ትክክል አይደለም ማለት አይቻልም ይላሉ። ዶክተር ዳኪቶ፤ የንግድ ባንኮች የተቋቋሙት በዋናነት ንግድን ለማሳለጥ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ፋይናንስ ለማቅረብ እንጂ ግብርናውን የመደገፍ ግዴታ የለባቸውም። ለምን ለአርሶ አደሩ ብድር አልሰጡም ተብለው ሊወቀሱ አይችሉም ይላሉ።
ዶክተር ዳኪቶ እንደሚናገሩት፤ ባንኮች ለምን ብድር አላቀረቡም ብሎ እነርሱን መውቀስ ተገቢ አይደለም። ዋናው ጉዳይ ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድ እንደ ሀገር በተለየ ሁኔታ የግብርናውን ዘርፍ የሚደግፍ የግብርና ባንክ ማቋቋም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አስፈላጊ ነው። ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን እንደ ባለሙያ ተነሳሽነት ወስደው እየደገፉ እንደሆነ ገልጸዋል።
አሜሪካንን ጨምሮ እንደ ቻይና፣ ህንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ ያሉ ሀገራትን ተሞክሯቸው እንደሚያሳየው፤ ሁሉም ሀገራት ላይ ትኩረቱን በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ያደረገ ባንክ አለ። እነዚህ ባንኮች ከሚሰጡት ብድር ሰማንያ ከመቶ የሚሆነውን ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እያበደሩ፤ የቀረውን ለሌላ ዘርፍ እያዋሉ ሥራቸውን የሚሰሩ ባንኮች አሉ። እነዚህን አሠራሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ለዘርፉ ውጤታማነት አስፈላጊ እንደሆነ ባለሙያው ያነሳሉ።
እንደ ዶክተር ዳኪቶ ማብራሪያ፤ እነዚህን ባንኮች ተነሳሽነት ወስዶ ከማቋቋም አንፃር የቻይና መንግሥት ኃላፊነቱን ወስዶ ይሠራል። በአሜሪካም በግል ተቋቁሞ ረዥም ዘመናት በውጤታማነት የዘለቀ ባንክ አለ። ከዚህ አንፃር ለዘርፉ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ግብርና ነው። ይህንን ዘርፍ በሚፈለገው ልክ በፋይናንስ መደገፍ ስላለበት ልዩ ትኩረትን ግብርና ላይ ብቻ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ባንክ ማቋቋም አለበት። ከዚህ ውጭ ይህ አሠራር ተግባራዊ እስኪደረግ ድረስ አሁን ያሉት የንግድ ባንኮች የተሻለ የብድር አቅርቦት ለአርሶ አደሩ ማቅረብ እንዲችሉ አዲሱ አዋጅ መንገድ የሚከፍት እንደሆነ ይናገራሉ።
ሁሉንም ሴክተር በፋይናንስ መደገፍ ወሳኝ ነው የሚሉት ዶክተር ዳኪቶ፤ ግብርና፣ ንግድም ሆነ የኢንዱስትሪ ዘርፍ በቂ በፋይናንስ ካልተደገፈ የትም ሊደርስ አይችልም፤ ግብርናው ደግሞ የሚያገኘው የብድር መጠን በጣም አነስተኛ ነው። ይህ ከሆነ ግብርናው በሚፈልገው ልክ ማደግ አይችልም፤ ስለዚህ ለማደግ የሚታስብ ከሆነ እራስን ለመለወጥ እና በምግብ እራስን ለመቻል ብሎም ዘመናዊ አሠራር በመከተል ከራስ አልፈን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል አቅም ለመገንባት ግብርናው በፋይናንስ መደገፍ ለነገ የማይባል ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ።
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ፤ የግብርና ባንክ ሲቋቋም አላማው ብር መስጠት ብቻ እንደሆነ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ትክክል አይደለም። ባንኮቹ ብር ከማበደር ባለፈ ተበዳሪ የሆኑትን ገበሬዎች የማማከር ሥራ ይሠራሉ፤ ምን ቢዘሩ በይበልጥ ውጤታማ ይሆናሉ? እንዴት ማረስ ይጠበቅባቸዋል? እንዴት ሀብታቸውን ማንቀሳቀስ ይችላሉ? ገንዘባቸውን እንዴት መጠቀም ይችላሉ? የሚለውን የማማከር ሥራ ስለሚሠሩ ይህ አካሄድ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ።
ግብርናው ዘመናዊ እንዲሆን በቂ የፋይናንስ አቅርቦት መኖር ወሳኝ በመሆኑ፤ አርሶ አደሩም ሆነ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚጠበቅባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ መንግሥት በተለይም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የግብርና ሚኒስቴር ከባለሙያ የሚተላለፉ ሃሳቦችን በባለቤትነት ወስዶ ይህ ባንክ እንዲቋቋም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ለተግባራዊነቱ መሥራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል። በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው ጥናት ለግብርና ሚኒስቴር የማንቂያ ደውል መሆን መቻል እንዳለበት አስረድተዋል።
ብሔራዊ ባንክ ከጥቂት ወራት በኋላ የሚያወጣው አዲስ የባንኮች አሠራርና መመሪያ ደንብ አለ የሚሉት ባለሙያው፤ ይህ በራሱ ጥሩ ጅምር ነው። እስከአሁን ድረስ ልዩ ባንኮችን ለማቋቋም የሕግ ማዕቀፍ አልነበረም። ይህ አካሄድ ከአሁን በኋላ አይቀጥልም። እነዚህን ባንኮች ማቋቋምን የሚደግፍ ሕግ መፅደቁ በራሱ ትልቅ እምርታ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የ2025 የዲጂታል ኢኮኖሚ እስትራቴጂ ተነድፎ እየተሠራ ነው የሚሉት ዶክተር ዳኪቶ፤ ይህንን እስትራቴጂ ወስዶ መመልከት ከተቻለ አራት ዘርፎችን በዋናነት ትኩረት ሰጥቶ ያስቀምጣል። ከእነዚህ መካከል ግብርና አንዱና ግምባር ቀደሙ ነው። በዚህ አካሄድ ቴክኖሎጂው ግብርናውን ዘመናዊ እንዲሆን ከሠራ ሕጉ ደግሞ ልዩ ባንኮች እንዲቋቋሙ ማድረግ ከቻለ፤ እነዚህ አንድ ላይ ሲደመሩ የሚታይ ውጤት እንደሚያመጡ ይናገራሉ።
በአጠቃላይ ባለሙያዎቹ እንደተናገሩት፤ የአዋጁ መፅደቅ አርሶና አርብቶ አደሩ የመሬት ይዞታውን በማስያዝ ብድር ማግኘት እንዲችል ማድረጉ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል። ነገር ግን ጉዳዩ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መመረት ያለበት በመሆኑ የአፈፃፀም ሂደቱ በጥንቃቄ መከወን እንዳለበት ተናግረዋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2016 ዓ.ም