የወለጋ ሕዝብ ፍላጎት- “መድማት ሳይሆን መልማት”

የሰላም እና የልማት ጥያቄዎች በኢትዮጵያ በየትኛውም ጫፍ ባሉ ማኅበረሰቦች ዛሬ ሳይሆን ለዘመናት ሲቀርቡ የነበሩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ናቸው። በሀገራችን እነዚህን ጥያቄዎች ታሳቢ ያደረጉ የለውጥ ንቅናቄዎችም በተለያዩ ወቅቶች ተከናውነዋል። ከአምስት ዓመት በፊት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሲዳማ፣ በሶማሌና በሌሎችም ክልሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ‹‹የሚፈሰው የአንዳችን ደም የሌላችን ደም ነው›› በማለት በታሪክ ጉልህ ሥፍራን የያዘ ጠንካራ ትግል አካሂደዋል ።

በመጨረሻም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለተከታታይ ዓመታት የተካሄዱ ተቃውሞዎች በኢህአዴግ ውስጥ በተፈጠረው ተራማጅ ኃይል ታግዘው ሀገራዊ ለውጥ እንዲወለድ አድርገዋል። በለውጡ መንግሥት ሁሉንም ሕዝብ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆኑም ፤ አንዳንዶች ሰላማዊ የለውጥ መነቃቃቱን ለማደብዘዝ እንቅልፍ አጥተው በሚፈጽሙት ጸረ ሰላም ተግባር የተወሰኑ አካባቢዎች ከለውጡ ፍሬ እንዳይቋደሱ አድርገዋል።

እነዚህ በሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች እንቆረቆርለታለን የሚሉትን ሕዝብ ለውጥ ለማዘግየት ብዙ ለፍተዋል። ስለ ሕዝብ እና ሕዝባዊነት እያወሩ የሕዝቡን የልማት ሥራዎች ከማደናቀፍ ጀምሮ የልማት መሻቱን የሚገዳደሩ ተግባራትን በአደባባይ እያከናወኑም ይገኛል። ‹‹የኦሮሞን ሕዝብ ነጻ አወጣለሁ›› የሚል ኋላቀር አስተሳሰብ ይዞ የሚንቀሳቀሰው አሸባሪው ቡድን ሸኔ ሕዝቡን በማሳደድ ፣ በማፈን፣ በመዝረፍ እና በመግደል ለከፋ ችግር መዳረጉም የአደባባይ ምስጢር ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ስምን ምሽግ ያደረገው አሸባሪው ሸኔ በተለይ የወለጋን ሕዝብ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል።

በወለጋ ዞን ለዓመታት የነበረው የሰላም እጦት የአካባቢውን ሕዝብ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ ከማንም የተደበቀ አይደለም። ለረጅም ጊዜ የዘለቀው የሰላም እጦት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተለይም በንግድ፣ በጤና እና በትምህርት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። አቃፊና ሁሉን ወዳጅ የሆነው የወለጋ ሕዝብ በሸኔ ምክንያት ሰላምን ተርቧል።

እንደሚታወቀው በኦሮሚያ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች የጋራ ትግል ለመጣው ለውጥ የወለጋ ሕዝብም እርሾ ነበር። አንዳንድ የፖለቲካ ልሂቃን ነን ባዮችና ‘የተንሸዋረረ አመለካከት ‘ ያላቸው ጥቂት ግለሰቦች የወለጋ ሕዝብ የእኩልነት ፣ የፍትሃዊነት እና የልማት ጥያቄዎቹ እንዳይመለሱለት አድርገውታል፤ ከለውጡ ቱሩፋት ተጠቃሚ እንዳይሆንም ጋሬጣ ሆነውታል። በወለጋ ሕዝብ ስም ጦርነት ከፍተው ለውጡን በሕዝብ ስም በማንገጫገጭ ተፈጥሯዊ የጉዞ ፍጥነቱን እንዳይጓዝ ተግዳሮት ሆነውታል ። ይህ ሕዝብ ሰላማዊ ኑሮውን ለመኖር ከተቸገረ አምስት ዓመታትን ተሻግሯል ።

የነፍጥ ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚደረግ እንቅስቃሴ የአንድን ሕዝብ ሰላማዊ የለውጥ መነቃቃት የሚያደበዝዘው የሕዝብን የዛሬ ሰላማዊ የለውጥ መነቃቃት ብቻ አይደለም። በልማት ተስፋ የሚያደርጋቸውን ብሩህ ነገዎችን ጭምር የሚያጨለም ነው። በወለጋ ዞን ያለው ሁኔታ ይሄንኑ ይነግረናል። የወለጋ ዞን የአካባቢው መሬት በለምነቱና መልምላሜው የሚታወቅ ቢሆንም ፤ በሰላም እጦት ከልማት ወደ ኋላ ቀርቷል። ለሀገር የሚተርፈ ሀብት ያለው መሬት ሳይታረስ ጦሙን እያደረም ይገኛል። የሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት በስሙ በሚነግዱ የጥፋት ሃይሎች ደብዝዞና አካባቢው ከልማት ወደ ኋላ ቀርቶ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቋል።

የወለጋ ሕዝብ ይሄንኑ የተጠራቀመ ብሶቱን ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም በወለጋ ስታዲየም ለውጡን በሚደግፈው ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ገልጿል። ሕዝቡ ከለውጡ በኋላ በሌሎች አካባቢዎች የተገኘው ሰላምና ልማት በወለጋ አካባቢም ዘላቂ እንዲሆን መሥራት እንደሚገባ አፍ አውጥቶ ጠይቋል። በዞኑ ለዓመታት በዘለቀው የሰላም እጦት ሕዝቡ ምን ያህል ዋጋ እየከፈለ እንደሚገኝ በአደባባይ ገልጿል ። የወለጋ ሕዝብ የመድማት ሳይሆን የመልማት ፍላጎት እንዳለው በግልጽ ቋንቋ ተናግሯል። ሞት ሰልችቶታል፤ ሰላም ርቦታል ፤ ልማት ናፍቆታል። የሕዝቡን ፍላጎት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር እንደሚከተለው ተጋርተውታል ።

“የወለጋ ሕዝብ በልማት በኩል ተጎድቷል። ይህም ደግሞ በሰላም እጦት ምክንያት ነው። ወለጋን መቀየር እንፈልጋለን ፤ ራዕይም አለን ። ይህ ሃሳባችን በመንገድ ላይ እንዳይቀር ሕዝቡ እድል ይስጠን። ሕዝባችን እኛን ይደግፈን” ሲሉ በሰላም እጦት ምክንያት ከልማት ወደ ኋላ የቀረውን የወለጋን ሕዝብ በትብብር የለውጡ ቱሩፋት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ይህን የሕዝብ ድምጽ አግባብ ባለው መንገድ ማድመጥና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ማበጀት ተገቢ እና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው። በአካባቢው ዘላቂ ሰላም በመፍጠር ሕዝቡ በሰላም ተረጋግቶ እንዲኖር ማድረግ እና ልማትን ማፋጠን ያስፈልጋል።

ከዚህ አንጻር ሁሉም አካል በመተባበር በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን አስፍኖ ሕዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር ማድረግ ይጠበቅበታል። በተለይ መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ ይገባዋል። በአካባቢው ሕዝቡ በሰላም ተረጋግቶ እንዲኖር ለማድረግ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። የፀጥታ አካላት በአካባቢው የተፈጠረውን የሰላም እጦት በመፍታት አካባቢውን ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሁኔታው ለመመለስ ሲሠሩ ቆይተዋል ።

መንግሥት በሠራቸው ሥራዎች በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም እንደሰፈነም ይታመናል ። በዚህም ሂደት የአካባቢው ማኅበረሰብ የነበረው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሕዝቡ ስለ ሰላሙ ፣ የሚፈልገውን ያህል መስዋዕትነት ከፍሏል። አሁንም ያለ አንዳች ስጋት በሰላም ተረጋግቶ መኖር የሚችልበትን ሁኔታ ከመንግሥት ጋር በመሆን መፍጠር ይኖርበታል።

ስለዚህ ሕዝቡ በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ ሕግን የማስከበር ርምጃዎችን እየደገፈ ዘላቂ ሰላሙን ማረጋገጥና ልማቱን ማፋጠን ይኖርበታል። ማህበረሰቡም ዛሬ ያለበት አንጻራዊ ሰላም ለራሱ ፣ ለልጆቹ እና ለልጅ ልጆቹ የተሻሉ ነገዎችን ለመፍጠር የሚያስችለው ፣ እንደ አንድ ትልቅ ማኅበረሰብ በለውጡ ውስጥ የነበረውን መነቃቃት በመመለስ የራሱን ዕጣ ፈንታ በራሱ እጅ የሚቀረጽበትን ዕድል የሚያጎናጽፈው ነው ።

ሀገራዊ ሰላም በእያንዳንዱ ዜጋ ነፍስ ፣መንፈስ እና አዕምሮ ላይ በጻፍናቸው ባህላዊ ፣ መንፈሳዊ / ሃይማኖታዊ እና ምሁራዊ የሰላም እውቀት የሚሰላ ነው ። ለዚህ ደግሞ በዋነኛነት ሰላማዊ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የቤተሰብ እና የማኅበረሰብ፣ የሃይማኖት እና የትምህርት ተቋማት ኃላፊነት ከሁሉም በላይ የላቀ ነው ። ከዚህ የተነሳ ሰላሙ ዳግም ከእጁ እንዳይወጣ የሰላሙ ባለቤት ሆኖ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ሊንቀሳቀስ ይገባል ። ማኅበረሰቡ ሰላምን በማስፈን ሂደት ላይ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ በመቀጠል የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል። ይህም አሁን ካለው ሰላም አንጻር በቀጣይ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን ፤ በዚህም ዜጎች የለውጡን ትሩፋት የሚያጣጥሙበትን ዕድል የሚፈጥር ይሆናል።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You