እአአ በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ላይ በ10ሺ ሜትር አራተኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀ በኋላ በተካሄዱ ኦሊምፒኮች ሳታይ ቆይቷል፡፡ በእርግጥ ከዚያ በኋላ ያሉትን ዓመታት ያሳለፈው ከታወቀበት የመም ሩጫ ወጥቶ በማራቶን ተወዳዳሪነት ነው፡፡ ከአስደሳች ብቃቱ እኩል አሳዛኝ ጉዳቶችን በተደጋጋሚ ማስተናገዱ ደግሞ የአትሌቲክስ ቤተሰቡ ለማየት የሚጓጓለትን ምርጥ አሯሯጥ እንዳይመለከት እንቅፋት ሲሆነው ነበር፡፡ በ25 ዓመታት የአትሌቲክስ ህይወቱ ስሙ የሩጫ ትርጓሜ እስኪመስል ድረስ ሳይነጣጠሉ የቆዩት ቀነኒሳ በቀለ እና የረጅም ርቀት ሩጫ የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ በድጋሚ ሊገናኙ ተቀጣጥረዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም የኦሊምፒክ ዶት ኮሙ ዘጋቢ ኢቭሊን ዋታ ከአትሌቲክስ ንጉሱ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር፡፡ 4 የኦሊምፒክ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀው፣ የ5 ጊዜ የዓለም ቻምፒዮናው፣ የሀገር አቋራጭ ተሳትፎ ክብረወሰንን አርቆ የሰቀለው የምንጊዜም የአትሌቲክስ ስፖርት ጀግና አትሌት ቀነኒሳ በቀለ አሁንም የብቃቱ ጫፍ ላይ አለመድረሱ የበርካቶች እምነት ነው፡፡ ይህን ሃሳብ የሚጋራው ቀነኒሳ ‹‹በማራቶን አሁንም የመጨረሻውን አቅሜን አላሳየሁም፤ ምክንያቱም ከረጅም ጊዜ ጉዳት ጋር ትግል ላይ ነበርኩ፡፡ ጠንካራ ልምምድ ባደርግም በጉዳት ምክንያት መጨረስ አልችልም፡፡ አእምሮዬ የሚነግረኝ ግን በማራቶን አሁንም የተሻለ ብቃት ማሳየት እንደምችል ነው፡፡ በርካታ ግቦች አሉኝ፤ ከእነዚህ መካከል የሆነው የፓሪስ ኦሊምፒክ ምናልባትም የመጨረሻ የመድረኩ ተሳትፎዬ ሊሆን ይችላል›› ሲልም ያብራራል፡፡
ቀነኒሳ ከስኬታማ የአትሌቲክስ ህይወቱ ባለፈ የሚያስተናግደው ተደጋጋሚ ጉዳት አገግሞ ወደ ልምምድና ውድድር ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት ለበርካቶች ትምህርት የሚሆንም ነው፡፡ በመም የሩጫ ዘመኑ ማብቂያ አካባቢ በጉልበት ጉዳት ሲሰቃይ የቆየ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የተረከዝ፣ የጀርባ፣ የባት፣ የሽንጥ እና የጡንቻ መሳሳብ ጉዳቶች ገጥመውታል፡፡ አስደናቂውን የሩጫ ህይወቱን ይበልጥ ፈታኝ ያደረገበት ደግሞ ጉዳቱ ከአንዱ የአካል ክፍሉ ወደሌላኛው ስለሚዘዋወር እንደሆነም ይጠቁማል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ የማራቶን ተሳትፎዎቹን እንደታሰበው ሳይሆን እንዲያቋርጥ ሲያስገድደው ቆይቷል፡፡ ይሁንና በአሸናፊነት የተቃኘው መንፈሱ በዚህ ሁኔታ ወደኋላ ከመመለስ ይልቅ በጥንካሬ ሁሌም ከፊት እንዲሰለፍ አድርጎታል፡፡
ጽናትን የሚፈልገው ማራቶን በእርግጥም በቀነኒሳ ጽናት ተፈትኗል። ‹‹የማራቶን ልምምድ እጅግ ከባድ ነው፤ በእያንዳንዱ ዕለት የሚኖረው ልምምድ ረጅም ርቀትን የሚሸፍንና አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህንን በምትፈልገው ልክ አለማጠናቀቅ ደግሞ ይበልጥ ከባዱ ነገር ነው›› ም ይላል፡፡ ከጉዳቱ ባለፈ ቀነኒሳ ባለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች(የ2016ቱ የሪዮ እና 2020 የቶኪዮ) ከጉዳት ነጻ እና በጥሩ ብቃት ላይ ሆኖም በብሄራዊ ቡድን ሳይካተት ቆይቷል፡፡ በዚህም ቅሬታውን ሲያሰማ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ በማራቶን ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት 2:01:41 ያለው አትሌቱ በቅርቡ ቫሌንሲያ እና ለንደን ማራቶን ላይ ባስመሰከረው ብቃቱ ደግም በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ ሀገሩን እንዲወክል አስችሎታል፡፡ ኢትዮጵያን በኦሊምፒክ ለመወከል አስቸጋሪ መሆኑን የሚያነሳው ጀግናው ቀነኒሳ ‹‹በጥንካሬና በፍጥነት ተቀራራቢነት ኦሊምፒክ ላይ መሳተፍ የሚያስችላቸው በርካታ አትሌቶች በመኖራቸው ምርጫውን ከባድ ያደርገዋል›› ይላል፡፡
የአንጋፋውን የኦሊምፒክ ጀግና ምሩጽ ይፍጠር በ42 ዓመት የኦሊምፒክ ማራቶን ተሳትፎ ክብረወሰን የሚጋራው ቀነኒሳ፤ ለጥቂት ዓመታት በሩጫው እንደሚቀጥልም ከድረ ገጹ ጋር በነበረው ቆይታው ጠቁሟል፡፡ ፓሪስ ላይ የሚኖረው ፉክክር ቀላል እንደማይሆንም ‹‹በርካታ ጠንካራ አትሌቶች የሚካፈሉበት ውድድር ስለሆነ ፈጣን ሩጫ ይሆናል፤ ይህም በስፖርት ቤተሰቡ ያለውን ግምት ያንረዋል፡፡ ለእኔም ከጉዳት መልስ ፈታኝ ነው፤ ነገር ግን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኜ መገኘት እፈልጋለሁ፡፡ ለተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ያለኝን አቅም አውጥቼ ውጤታማ ለመሆን እጥራለሁ፡፡ ለወደፊት ክብረወሰንን መስበር ጨምሮ በርካታ ግቦች አሉኝ›› ሲልም ያስረዳል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም