ግዴታቸውን ሳያውቁ መብት ብርቅ የሚሆንባቸው!

ኢትዮጵያ ውስጥ የመብት ነገር ግርም ይለኛል። በአንድ ጉዞ ላይ ካስተዋልኩት አስቂኝ ገጠመኝ ልነሳ። ከመገናኛ ወደ ኮተቤ እየሄድን ነው። ላምበረት አካባቢ ሲደርስ ልክ አደባባይ መዞሪያ ላይ አንዲት ወጣት ‹‹ወራጅ አለ›› አለች። ለወትሮው ‹‹እዚህ አይቻልም›› ይሉ ነበር ረዳቶች። ይሄኛው ሰልችቶት ይሁን አጠያየቋ በጣም ስላበሳጨው አላውቅም ሰምቶ ዝም አላት። ታሳፋሪው ራሱ ይታዘብ በሚል ይመስላል። መንገዱ የተዘጋጋ ስለሆነ በፍጥነት አይሄድም ነበርና አሁንም በአደባባዩ ዙሪያ ነው። ድምጿን ከፍ አድርጋ በቁጣ ‹‹ወራጅ አለ አይደል እንዴ የምልህ!›› አለችው። ደግነቱ ከረዳቱ ቁጣ በፊት ታክሲው ውስጥ ያለው ሰው መሳቅ ጀመረ። ረዳቱ የተሳፋሪውን ሳቅ ለሕጋዊነቱ መተማመኛ አድርጎ ይመስላል በምፀት ዞር ብሎ አይቷት ‹‹አይ ቆይ አደባባዩ ውስጥ እኮ ላስገባሽ ብዬ ነው!›› አላት። ከረዳቱ የምጸት ንግግር ይልቅ የተሳፋሪው ሳቅ ሳያናድዳትና ሳያሳፍራት አልቀረም። ካፈርኩ አይመልሰኝ እንዲሉ የምንተፍረቷን ‹‹መብቴ ነው›› አለች፤ ይሄኔ የባሰ ተሳቀባት።

እግረ መንገዱን ብዙ ነገር ስላስታወሰኝ እንጂ የልጅቷ ገጠመኝ ተራ ገጠመኝ ነው፤ ባለማወቅ የሚሆን ነው። ዳሩ ግን የብዙ ሰዎችን ስህተት ይነግረናል። በተለይ ይሄ ‹‹መብቴ ነው›› የሚባል ቃል የሚገባባቸውን ቦታዎች ስናይ የመብት ነገር ምን እንደሆነ ይጠፋብናል። እዚህ ሀገር መብቴ ነው የምንለው ነገር ሌላውን መጉዳት ነው። ለምሳሌ ልጅቷ መብቴ ነው ያለችው ሕግ ጥሳ ነው። መሆን የሌለበት ቦታ ላይ ካልሆነ ብላ ነው።

መብት ብርቅ የሆነብን ይመስላል። ከአስተዳደጋችን ጀምሮ ስንኖርም መብቶቻችን የሚረገጡባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። ለዚያም ነው ቃሉ ራሱ ብርቅ ሆኖ በጣም ሲደጋገም የምንሰማው። በአስተዳደጋችን ውስጥ የሆነ የቤተሰብ ጫና አለ። ይሄ ነገር ገጠር ብቻ እንዳይመስላችሁ፤ የአዲስ አበባ ልጆች ብዙ የቤተሰብ ቁጥጥር አለባቸው። መረን ለቀው ይደጉ እያልኩ አይደለም፤ ዳሩ ግን የቁጥጥሩ ዓይነት ይለያያል።

ከቤተሰብ ከወጣን በኋላም ይሄው ነው። ፖለቲካችን ሁልጊዜም የሚዘመርለት የመብትና ግዴታ ጭቅጭቅ ነው። ከትምህርት ቤት ጀምሮ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። የሳይንስ ምልክቶች፣ የሒሳብ ቀመሮች፣ የሀገራት ካርታ…. የመሳሰሉት ትምህርታዊ ነገሮች ከውጭ በኩል የሚለጠፉ ሲሆን ከክፍል ውስጥ የሚለጠፈው ‹‹የተማሪው መብትና ግዴታ›› የሚል ነው። በተለይም ‹‹የተማሪው ግዴታ›› በሚለው ሥር ያለው መዘርዝር ይበዛና ‹‹መብት›› ላይ ያለው አነስ ያለ ይሆናል። ስለዚህ ለምን መብት ብርቅ አይሆንብን? ግዴታ በሰፊው የሚዘረዘርበት ምክንያት በአስተዳደጋችንም ሆነ በአኗኗራችን ምክንያት መብት ብርቅ ሆኖብን ግዴታችንን ስለማንወጣ ነው።

‹‹ለምን ሆነ›› አልልም፤ ሥነ ምግባራችንም እንደዚሁ ነው። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያሉ ነገሮችን ከመጠቀም ይልቅ ማበላሸት ላይ ስለምናተኩር ግዴታዎች በዙ።

ይሄ ነገር አብሮን ያድግና ከትምህርት ቤት ያልፋል። ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ተቋማት ድረስ ‹‹ክልክል ነው›› የሚል ጽሑፍ ነው የምናየው። ከግል ንግድ ቤቶች ጀምሮ እስከ መንግሥት ተቋማት ድረስ የሚከለከሉ ነገሮች ይበዛሉ። ይሄ ማለት እንግዲህ ካልተከለከልን እናጠፋለን ማለት ነው። ‹‹ክልክል ነው›› የሚል ጽሑፍ ማየት በጣም የተሰለቸ ነው። ታዲያ ለዚህ ይሆን መብት ብርቅ የሆነብን?

የተማሩ ናቸው የሚባሉ፤ ሀገር ለመምራት የሚወዳደሩ፤ ትልልቅ የምንላቸውን ሰዎች ልብ በሉ። ስብሰባዎችንና ውይይቶችን አስተውሉ። የሚወራው ስለመብትና ግዴታ ነው።

ይሄ ‹‹መብቴ ነው›› የሚባል ነገር ይሉኝታም እያሳጣን ነው። ኧረ ሰው አይሰደብም፤ ‹‹በገዛ ስልኬ መብቴ ነው››፣ ይሄ እኮ ለሰው ፀያፍ ነው መንገድ ላይ አይጣልም፤ ‹‹መብቴ ነው››፣ ይሄ እኮ ሌላ ሰው ይወጋል መንገድ ላይ አይደረግም፤ ‹‹መብቴ ነው››… ታዲያ መብት ብርቅ አልሆነብንም? እንዲህ ትንሽ ትልቁን መብቴ ነው የሚሉ ሰዎች ድንገት የነቁ የመሰላቸው ሰዎች ናቸው።

አንዳንዱ መብቴ ነው ደግሞ ያስቃል። ራሱ ላይ ጉዳት የሚያደርስን ነገር ሲከለከል (ሲመከር) ሁሉ ‹‹መብቴ ነው›› ይላል። መድኃኒት እየወሰዱ እኮ አልኮል አይጠጣም፤ ‹‹መብቴ ነው››፣ ይሄ መጠጥ እንዲህ ስለሆነ ቢቀርብህ፤ ‹‹መብቴ ነው››፣ ይሄ ነገር መጥፎ ሱስ ነው፤ ለጤናም እንዲህ ዓይነት ጉዳት አለው ቢቀርብህ ‹‹መብቴ ነው›› ይሄ ልብስ እኮ የደም ዝውውርህን እንዲህ ያደርገዋል፤ ‹‹መብቴ ነው››፣ ብርድ ስለሆነ እንዲህ ባትለብሽ ‹‹መብቴ ነው››፤ ትልልቅ ሰዎች ጋ ስለሆነ የምትሄጂ እንዲህ ባትራቆች ‹‹መብቴ ነው››፣ ይሄ እንዲህ ነውና ባትቀቢው ‹‹መብቴ ነው››… እንዲህ ሆነናል እንግዲህ!

ነገሮችን ሁሉ ለምን ከመብትና ግዴታ አንጻር ብቻ እንለካቸዋለን? የተበላሸ አለባበስ ለብሰህ አትሂድ የተባለ ሰው መተው ያለበት ግብረገባዊነትን ወይም ሳይንሳዊ ጉዳቱን አመዛዝኖ ነው ወይስ ስላልተከለከለ ብቻ ነው? አንዳንዶቹ እኮ ገና ማንም ሳይናገራቸው ‹‹እስኪ ዛሬ ማን ምናባቱ እንደሚለኝ አያለሁ!›› ብለው ይፎክራሉ።

ዓመታት በፊት የተከታተልኩት የማስታውሰው አንድ ጉዳይ ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የምትሰራ አንዲት ሠራተኛ ከቤተ መጻሕፍት ጥበቃ ጋር ተጣላች። የተጣላችው ‹‹አግባብ ያልሆነ ልብስ ለብሰሻል›› ተብላ ነው። ከዚያ ወጥታ ያዙኝ ልቀቁኝ አለች። ጉዳዩም በአንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ መከራከሪያ ነበር። ሁሉም ሃሳብ ሰጪዎች ሲሉ የነበረው ‹‹መብቷ ነው›› ነው።

ልክ ናት አይደለችም አልልም። ግን ልክ ከሆነችም ከልካዩ የሚጠየቅበት አግባብ ይኖረዋል። እሷ ልክ ካልሆነች ያልሆነችበትን ማብራራት ሲገባ ‹‹መብቴ ነው›› በሚል ብቻ ተጣሉ። ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲው ቤተ መጻሕፍት በጣም አጭር የሆነ ቀሚስ መልበስ ክልክል ከሆነ ሴትዮዋ መከራከር የነበረባት ሕጉ ትክክል አይደለም፤ መስተካከል አለበት፣ ራቁትም መግባት ይቻላል ካለች ያንን የሚያስችል ሕግ መኖር አለበት ብላ መከራከር ነው። ሕጉ እያለ ግን ‹‹መብቴ ነው›› እንዴት ይሆናል?

እንዲህ መብት ብርቅ የሆነብንን ያህል ግዴታ ብርቅ ቢሆንብን የት በደረስን ነበር።

ለማንኛውም ‹‹መብቴ ነው›› ስንል ቢያንስ ቢያንስ ግብረ ገብነትንና ሳይንሳዊ ጉዳትን እንኳን ከግምት ውስጥ እናስገባ! ጉዳት የሚያደርስብንን ነገር ስላልተከለከልን ብቻ እናድርገው ካልን ይሄ ሰውነት ሳይሆን እንስሳነት ነው፤ ስላልተከለከልን ብቻ ነውር የሆነን ነገር ማድረግ መብት ሳይሆን ብልግና ነው!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You