በክፍሎች ስያሜ ትውልድ የማስተማሪያ መንገድ

ስምና ስያሜን በተመለከተ ብዙ ተብሏል። በተለይ በሃይማኖቱ ዘርፍ ከነ ጥልቅና ረቂቅ ብያኔው ተተንትኗል። “ስምን መላእክ ያወጣዋል” እስከሚለው ድረስ በመዝለቅ በሥነ-ቃል ውስጥም ተካትቶ እናገኘዋለን። ምናልባት ካላከራከረ በስተቀር፣ “ስም ምግባርን ይገልፃል” የሚልም አለ። ሊቁ ሼክስፒርም በዘመን ተሻጋሪ፤ እንዲሁም፣ ቦታና ጊዜ ባልገደበው “ሮሚዮ እና ጁሊየት” ድራማው “ሥም እና ሥያሜን ምን አገናኛቸው?” ዓይነት ጥያቄን “What is in A Name?” ሲል የጠየቀው ጥያቄ እስከ ዛሬም እያወዛገበ የመገኘቱ ጉዳይ ሌላ ሳይሆን የሥም እና ሥያሜ ጉዳይ “የትም ፍጪው፤ ዱቄቱን አምጪው” አለመሆኑን ነው። የኛም ድምፃዊ “ስያሜ አጣሁላት” ያለው ሊዘነጋ የሚገባው ማህበራዊ ርእሰ ጉዳይ አይደለም።

ወደተዘነጉት ስሞች ስንሄድ ደግሞ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው “መቼ ተነሱና የወዳደቁት” እንዳለችው ለሀገርና ወገን ሲሉ የወዳደቁት እንኳን ስማቸው ገና ምናቸውም አልተነሳም። በመሆኑም፣ ሁላችንም አደራም፣ ከፍተኛ የቤት ሥራም አለብን ማለት ሲሆን፤ የቤት ሥራቸውን እየሠሩ፤ ሀገራዊና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውንም እየተወጡ ካሉት አንዱ የሀረሩ ትምህርት ተቋም በመሆኑ አርአያነቱ ለሁላችንም ይሆናል።

ባለውለታዎችን ማንሳት፣ ማንገስ፣ መዘከር እና ማስታወስ ፋይዳው ለእነሱ አይደለም። እነሱ እኮ የሉም። ፋይዳው ለሀገር፣ ለታሪክ፣ በተለይም ለትውልድ ነው። የአሁኑም ሆነ መጪው ትውልድ ማያ፣ መመልከቻ፣ አቅጣጫ ጠቋሚ (በአራቱም ማዕዘን) ወዘተ ይፈልጋል፤ ያስፈልገዋል። ይህ መስታወት ትውልድ ወደፊትም ሆነ ወደ ኋላ ሲሄድ ገደል እንዳይገባና በእሱም ሆነ በሌላው ላይ አደጋ እንዳያደርስ ይጠቅመዋል። ግራ ቀኙን ተመልክቶ እውነቱ ላይ ይደርስ ዘንድ ያግዘዋል።

ከዚህ የመስታወት አካል ደግሞ ሰፊውን ድርሻ የሚይዙት የሀገር ባለውለታዎች ሲሆኑ፤ ገድላቸው የትውልድ አስተማሪ፣ መቅረጫ፣ መሪ ወዘተ ነውና በተቻለ መጠን፤ በተገኘው አጋጣሚ (ወይም አንድ ታዛቢ “እንደ ምንም ብሎ፣ የሆነች ቀዳዳም ትሁን ፈልጎ ያገር ባለውለታዎችን ማንሳት ያስፈልጋል” እንዳሉት) ባለውለታዎችን፣ ምሁራንን፣ አርበኞችን ወዘተ ማንሳት እጅጉን ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ የሀረሩ ሀይ-ቴክ ሥራውን እየሰራ ነውና ምስጋናችን ከአዲስ አበባ ይድረሰው ስንል ከልብ ነው።

በየትም ሀገር ላይ “ስም ከመቃብር በላይ ነው”ና የሀገር ባለውለታዎች ስማቸው ይነሳል። ታሪክ ነውና ስምና ተግባራቸው ሲወደስ፣ ሲጠቀስ፣ ሲተነተን … ይኖራል። መስራቾች ናቸውና በየትውልዱ አዳዲስ ምዕራፎችና ገፆች ተቸሯቸው በአዲስ ቀለም ሁሉ ነገራቸው ይፃፋሉ። በየትምህርት ሥርዓታቱ ውስጥ ሁነኛ ቦታዎችን ይይዛሉ። ታሪካቸው ትውልድ ይቀረጽበታል። ሀውልት እዚህም እዛም ይቆምላቸዋል። በስማቸው ተቋማት ይገነባሉ። መንገዶች፣ አዳራሾችና የመሳሰሉት ይሰየማሉ። መጻሕፍት ይደረሳሉ። የሕይወት ታሪካቸው በየጊዜውና ዘመን ባፈራው ንድፈ ሃሳብና ቀመር ይብላላል። እየዳበረም ይሄድ ዘንድ የምሁራን ርእሰ ጉዳይ በመሆን ይመረመራል ወዘተርፈ … ።

መቼም ባለታሪኮች፣ ዝም ብለው “ባለ ታሪክ” አልተባሉምና ከጥፍር እስከ ፀጉራቸው ታሪኮች ናቸው። የተኙበት አልጋ ታሪክ ነው፤ የተመረኮዙት ከዘራ በየ ሙዚየሙ ተገቢውን ስፍራ ይይዛል። የጠጡበት አንኮላም ይሁን ሽክና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ (በቱሪዝሙ ዘርፍ) ነው። ኮፍያቸው፣ መነፅራቸው፣ መቀመጫ ወንበራቸው፤ በተለይም፣ እዚህ እንደኛ ሀገር ሳይሆን፣ መኖሪያ ቤቶቻቸው በከፍተኛ የሀገርና የሕዝብ ቅርስነት ተመዝግበው ተገቢውን ስፍራ ይይዛሉ። (“እዚህስ?” የሚል ገራገር ጠያቂ ካለ የሀዲስ ዓለማየሁ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ አፈወርቅ ተክሌ… ሀውልቶችን በከተሞቻችን እየዞረ “መጎብኘት” ይችላል። በቅርስነት “በተመዘገበው” መኖሪያ ቤታቸው “መንፈላሰስ” ይቻለዋል። “ተባለ እንዴ” አለ ፀሐዬ።)

ርግጥ ነው፣ ከላይ ያልነውን እንበል እንጂ፣ በቂም ባይሆን እኛም ሀገር ባለ ውለታዎችን የማስታወሱ (ብልጭ ድርግምም እያለ ቢሆን) አልፎ አልፎ ይታያል። በባንክ ቅርንጫፎች፣ በትምህርት ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ የንግድ ተቋማት፣ ሕንፃዎች፣ አዳራሾች (ለምሳሌ የአአዩ “እሸቱ ጮሌ አዳራሽ”)፣ መንገዶች እና ሌሎችም የማስታወሱ ጉዳይ አለ። ምናልባት ቋሚነታቸው (ብዙዎቹ በግለሰብ ኪራይ ቤቶች ላይ ስለሆኑ) ሊያጠራጥር ይችል ይሆናል እንጂ ሙከራና ተግባሩ የሚያስመሰግን ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ባለውለታዎቻቸውን ችላ የሚሉ ሀገራት እነሱ ችላ ያሏቸውን ባለውለታዎች ሌሎች ወድቀው ካገኟቸው አንስተው በመስውሰድና በማንገስ ሲኮሩባቸውና የኢኮኖሚ አቅማቸውን ሲደጉሙባቸው እያየን ነው። እዚሁ አፍሪካ ውስጥ እንኳን ያለውን እውነታ ብንወስድ እውቅ ኢትዮጵያዊያን የበርካታ ሀገራት ጌጥ ሆነው እንመለከታለን። ዝርዝሩ ብዙ ስለሆነ እንለፈው።

ሀገራችን በርካታ እውቆች እንዳሏት ዓለም ያውቃል። ዓለምን እጁን አፉ ላይ ያስጫኑ ጀግኖች አርበኞች (በምድር ጦር፣ በአየር ኃይል፣ በባህር ኃይል)፣ ለዓለም የተረፉ ስመ ጥር ምሁራን፣ መሪዎች (ወንድም፣ ሴትም)፣ አርቲስቶች፣ ስፖርተኞች ከየዓይነቱ (ይድነቃቸው ተሰማ፣ አበበ ቢቂላ…) አሉን። ሰዎች ብቻም አይደሉም፣ “ተፈጥሮ የለገሰችንን” እንዳለው ሎሬቱ ተፈጥሮ የለገሰችን ድንቅ መልካምድራዊ ገፀ በረከቶች (የዓድዋ ተራሮችን ብቻ መውሰድ ይቻላል) አሉን። አሉን እንጂ፣ ከአንዳንድ ሆቴሎች አዳራሾች ስያሜ ባለፈ ምንም ዓይነት ጥቅም ሳይሰጡን ባሉበት አስቀምጠናቸው እንገኛለን። ከዚህ አኳያ ግን የሚቀጥለው ተቋም ይለያል፤ ከብጤዎቹ ይለያል።

ከላይ እየተነጋገርንበት እዚህ ድረስ ስለዘለቅነው ጉዳይ በተጨባጭ ማሳያ ይሆነን ዘንድ ወደ ሀረር ከተማ የገሰገስን ሲሆን፤ ለሥራ ጉዳይ እዚህ አዲስ አበባ መጥተው ያገኘናቸው የሥራ ኃላፊ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ስለተቋማቸው እንደሚከተለው አጫውተውናል።

አቶ ኃይሉ አሰፋ ይባላሉ፤ በሀረሩ ከተማ የሀይ-ቴክ አካዳሚ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ናቸው። ርእሰ መምህር ኃይሉ አሰፋ እንደሚናገሩት በ1999 ዓ·ም የተመሰረተው ይህ ትምህርት ቤት ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምር ሲሆን፣ በአጠቃላይ 3ሺህ 500 ተማሪዎች አሉት። ቅርንጫፎችን የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶችን በየአካባቢው አቋቁሟል፡፡ አካዳሚው ሀረርን ጨምሮ በኬጂው ዘርፍ በአጠቃላይ ስምንት ቅርንጫፎች አሉት።

የትምህርት ቤቱን ይዞታ፣ የመምህራንን ትጋትና የተማሪዎችን ውጤት በተመለከተ የጠየቅናቸው ርእሰ መምህር ኃይሉ አሰፋ ሁሉም በጥሩ ይዞታ ላይ እንደሚገኙ የገለፁልን ሲሆን፣ ተማሪዎቻቸውን በተመለከተም በየዓመቱ ጥሩ ውጤት በማምጣት ከክፍል ወደ ክፍል እንደሚዘዋወሩና የ12ኛ ክፍሎችን በተመለከተም ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየገቡ መሆናቸውን ይናገራሉ።

ወደ ሀረር አቅንተው በነበሩትና ለትምህርት ቅርበት ካላቸው የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያው አቶ አንዷለም ዘመዴ ባገኘነው መረጃ መሠረት ያነጋገርናቸው አቶ ኃይሉ አሰፋ እንደነገሩን ከሆነ እሳቸው የሚመሩት ሀይ-ቴክ አካዳሚ ከሌሎች መሰል የትምህርት ተቋማት ለየት ያለ ገፅታ አለው። በተለይ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉት ክፍሎች እንደ ሌሎች “ክፍል” ብቻ ሳይሆኑ የየራሳቸው ታሪክ ያላቸው ክፍሎች ሆነው ነው በየዓመቱ ለተማሪዎች ዝግጁ የሚሆኑት።

በአብዛኛው በየትምህርት ተቋማቱ የሚገኙ ክፍሎች (የክፍል ደረጃዎች) በሴክሽን ተመድበው፣ ለምሳሌ 7ኛኤ፣ 7ኛቢ፣ 7ኛሲ፣ 7ኛዲ (መቼም የማትረሳ) ወዘተ ተማሪዎችን ተቀብለው ሲያስተናግዱ ነው። በመሆኑም፣ እነዛ “ፊደሎች” ዘላለማዊ በሚመስል መልኩ ከተማሪዎች የአእምሮ ጓዳ ሳይፋቁ (ልክ እንደ “7ኛ ዲ” እና ሌሎችም) ረጅም ዓመታትን ሲያስቆጥሩ ይኖራሉ። ፊደሎቹ ብቻም አይደሉም፤ በፊደሎቹ በተሰየሙት ክፍሎች ውስጥ አብረዋቸው “ሀ” ያሉ፣ “ሁ” ያሉ… ሁሉ አብረው፤ ተግተልትለው ይመጣሉ።

ይህንን ትዝታ ወደ ምስል በመቀየር ክፍሎቹን በታዋቂ ሰዎች ስም የሰየሙ ሲሆኑ፤ እነዛ ሰዎች በዛ ክፍል በተማሩ ሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚኖራቸውን “ዘላለማዊነት” ብቻ ሳይሆን እንደ እነሱን ለመሆን የሚደረገውን ጥረት፤ ምናልባትም እነዛን ሰዎች በአርአያነት ተጠቅሞ እነሱ የደረሱበት የደረሰን የቀድሞ ተማሪ ማሰብ ይቻላል።

ርእሰ መምህር ኃይሉ አሰፋ እንደገለፁት ትምህርት ቤታቸው ከኬጂ እስከ 12ኛ ክፍል የሚዘልቅ እንደመሆኑ መጠን፣ ሁሉም ሴክሽኖች ያሏቸው ሲሆን፣ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ያሉት ግን ይለያሉ። እንደ ርእሰ መምህሩ ማብራሪያ ሴክሽኖቹ በሙሉ በታዋቂ ሰዎች፣ እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን ለሀገርና ለወገን ያፈሰሱ ሰዎች፣ በየተሰማሩባቸው የሥራና የሙያ ዘርፎች ሀገርና ሕዝባቸውን ያስቀደሙ ሰዎች፣ ከሀገርና አህጉርም ባለፈ ለመላው የሰው ልጆች ሁሉ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ለሁሉም የተረፉ ሰዎች፤ ታዋቂ፣ ዝነኛ፣ ጀግና፣ በተሰማሩበት ሁሉ ሀገርና ሕዝብን ያኮሩ፤ ለትውልድ አርአያነታቸው ከዚህ በመለስ የማይባሉ ሰዎች የየሴክሽኖቹ (ክፍለ – ክፍሎቹ) መጠሪያ ናቸው።

እንደ ርእሰ መምህር ኃይሉ ማብራሪያ በእሳቸው ተቋም “12ኛኤ” ወይም “12ኛቢ” የሚባል ነገር የለም። እሳቸው ተቋም ያለው በፕሮፈሰር አክሊሉ ለማ (የእነ ዶ/ር ገቢሳ ኤጀታና ሌሎችም በተመሳሳይ) ፎቶግራፍ የተደገፈ 12ኛ ሴክሽን ነው ያለው። በቃ እንደዚህ ነው – ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉት ሴክሽኖች የሴክሽን አሰያየማቸው ይህንን መሠረት ያደረገ ነው።

“አላማው ምንድን ነው?” በማለት ላቀረብንላቸው ጥያቄ “አላማው፣ የሀገር ባለውለታዎችን ማስታወስ፣ ለትውልድ ማስተዋወቅ፣ አርአያ እንዲሆኑ ማድረግና ተማሪዎች ከእነዛ ሁሉ ሴክሽኖች የሚፈልጉትን ሰው ሞዴል በማድረግ ትልቅ ቦታ እንዲደርሱ ከወዲሁ ማበረታታት ነው” በማለት መልሰውልናል።

ይህ ብቻም አይደለም፣ ተማሪዎች በየተመደቡበት ክፍል ክፍላቸው ስለተሰየመበት ታላቅ ሰው ጥናትና ምርምር አድርገው ለክፍል ያቀርባሉ። “ዲፌንስ” (ተቋቁሞ) ያደርጋሉ። በሚያቀርቡት ጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸው ላይ ውይይት፣ ክርክር ይካሄዳል። በዚህ መሠረትም ስለዛ ሰው (ለምሳሌ ይህ ታዋቂ ሰው ቦታኒ ያጠና ቦታኒስት ከሆነ ስለ ቦታኒ ከማወቃቸውም በላይ ስለ ሰውየውና ሥራዎቻቸው ይረዳሉ ማለት ነው። ይህ እነሱም እንደዛ ሰው ጎበዝ ለመሆንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ ሰው ሆኖ ለሀገርና ወገን መሥራት ውስጣቸው እየሰረፀ ይሄዳል፡፡ ተማሪዎች ወደዚያው እየሄዱ፣ በውጤቶቻቸውም እየተሻለ በመሄድ ላይ መሆናቸውን፤ ሴክሽኖቻቸው የተሰየሙባቸው እውቀትን ጥረትና ግረትም እየተጋባባቸው በመሄድ ላይ መሆኑን ይናገራሉ ርእሰ መምህሩ።

ይህ አሁን ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ካሉት ብቻም አይደለም እየተስተዋለ ያለው የሚሉት አቶ ኃይሉ፣ የቀድሞ ተማሪዎች ማህበር (አሉሚኒ) ስላለ በማህበራቸው አማካኝነት በሚሰባሰቡ ተማሪዎችም የተንፀባረቀና እየሆነ ያለ ጉዳይ መሆኑንም ይገልፃሉ።

ርግጥ ነው መዝገበ-ቃላቱ “ስምን መሰየም ካለመኖር ተፈጥሮ ወደ መኖር መገለጥና መታወቅ ገንዘብን፣ አካልን ኾኖ መገኘት።” ይበል እንጂ፣ የስያሜም ሆነ ስም ጉዳይ አያወዛግብም፤ አያጨቃጭቅም ማለት አይደለም። እስከ ታሪክ ሽሚያ ድረስ ጦር ሊያማዝዝ ይችላል (ቦታው አይደለም እንጂ ብዙ መጥቀስም ይቻላል)። ይህንን ደግሞ በየጊዜው የምናየው ነው። ርእሰ መምህር ኃይሉ አሰፋ የሚመሩት ትምህርት ቤት ግን ይህ ዓይነቱ ዝባዝንኬ እንዳይፈጠር አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ ያደርጋል።

የሀይ-ቴክ አካዳሚ የክፍለ ክፍሎች አሰያየምና የእውቅ ኢትዮጵያዊያን ምደባ ሥርዓታቸው “ሥርአተ ምደባ” (ታክሶኖሚ) ከሚለው ጥናት ጋር አብሮ ይሂድ/አይሂድ ለጊዜው ይህ ፀሐፊ ያደረገው ጥናት ባይኖርም፣ (“ሥርዓተ ምደባ” ማለት “በሥነ ሕይወት (የሮማይስጥ ስያሜ የሆነውን «ጥበበኛ ሰው» (ሆሞ ሳፒየንዝ) ጨምሮ) ሕያዋን ነገሮች በሚጋሯቸው የጋራ ባህሪያት ላይ በመመስረት ስያሜ የመስጠት፣ ባህሪያቸውን የመተንተን እና በተለያዩ ቡድኖች ምደባ የመስጠት ሳይንሳዊ ጥናት”) የተለፋበት ሥራ ስለመሆኑ ግን ምንም መጠራጠር አይቻልም።

ርእሰ መምህር ኃይሉ አሰፋ እንደነገሩን ከሆነ፣ ታወቂ፣ የሀገር ባለውለታና በሕዝብ ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት ያላቸውን ምርጥ ሰዎች ወደ አደባባይ የማምጣቱና በተቋሙ የየክፍሎች ስያሜ የማድረጉ ሥራ ዝም ተብሎ፣ በአቦ ሰጡኝ የሚከናወን ሳይሆን፤ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ ተደርጎበት፤ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ተካሂደው፤ ኢንሳይክሎፔዲያዎች፣ የራሳቸው የየክፍሎቹ የመማሪያ መጻሕፍት ሁሉ ተመርምረው በእነዛ ውስጥ ይሁንታንና እውቅናን ያገኙ ናቸው በስማቸው ክፍል ይሰየምላቸው ዘንድ ብቃት የሚኖራቸው። የፈረሱን ውለታ ወሰደው … የሚለው እንዳይከሰት፤ አላስፈላጊ ውዝግብ እንዳይነሳ ሁሉ አስፈላጊው ጥንቃቄ አስቀድሞ ይደረጋል።

ባጠቃላይ፣ የሀገር ባለውለታ በምንም መልኩ ለአፍታ እንኳን ለዘነጋ አይገባም። ይህ ሊሆን የሚገባው ደግሞ ለሟቹ ሳይሆን ለራስ፤ በተለይም ለመጪው ትውልድ ሲባል ነው። በመሆኑም፣ የሀይ-ቴክ አካዳሚ አርአያነት በሌሎች ተቋማትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል መልእክታችን ነው፡፡

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You