የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰሞኑ አፈፃፀማቸውን ከገመገመላቸው መንግሥታዊ ተቋማት መካከል ግብርና ሚኒስቴር አንዱ ነው። በዚህም ላይ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ ዶክተር የሚኒስቴሩንና የተጠሪ ተቋማትን የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርበዋል። ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ካቀረቧቸው ጉዳዮች መካከል የማዳበሪያ አቅርቦት፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋትና አረንጓዴ ዐሻራን የተመለከቱት ይገኙበታል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 16 ነጥብ አምስት ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 11 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታሉ ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዟል። በመስኖ ስንዴ በምርት ዘመኑ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ሁለት ነጥብ 97 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈን ተችሏል።
በተጨማሪም በመላ ሀገሪቱ 50 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ለማሠራጨት ታቅዶ 57 ሚሊየን ማሠራጨት መቻሉንና የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ለዚህ አስተዋጽኦ ማድረጉን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
በሌላ በኩልም በ2016/17 በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑና እስካሁን ባለው ስድስት ነጥብ 34 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውም ዶክተር ግርማ በሪፖርታቸው አስረድተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በዘርፉ እየተገኘ ያለው እምርታ እንደተጠበቀ ሆኖ በ2015/16 የምርት ዘመን በአፈር ማዳበሪያ የነበረውን ችግር በመፍታት በዘንድሮው ምርት ዘመን የግዥ ሥርዓቱን በማስተካከል ቀድሞ የማዳበሪያ ግዥ መፈፀም መቻሉ የሚበረታታ መሆኑን አስታውቋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት በርካታ ውጤታማና ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን አከናውነዋል።
ሚኒስቴሩ በተለይም የመስኖ ስንዴ ልማት ሥራውን በየዓመቱ በእጥፍ እያሳደገ መምጣቱ በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን አመላካች መሆኑን ነው ሲሉ የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ አሁንም በከተሞች አካባቢ የስንዴና የስንዴ ውጤቶች አቅርቦት እጥረትና የዋጋ መናር እንደሚታይ ጠቁመዋል። ሚኒስቴሩ ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት የታየውን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ችግር መፍታት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ ቋሚ ኮሚቴው ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የመስክ ምልከታ ከግዥው ባለፈ ምንም ዓይነት የአፈር ማዳበሪያ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን መታዘብ መቻሉን ጠቁመው፤ ለአብነትም በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋና በጎንደር ዞኖች እንዲሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያና አንዳንድ አካባቢዎች ሥርጭቱ በአግባቡ እየተከናወነ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም የግብርና ሚኒስቴር ሥርጭቱ ላይ በአጽንኦት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተገዛውን የአፈር ማዳበሪያ በጊዜ እና በበቂ መጠን ለአርሶ አደሩ የማቅረብም ሆነ በፍትሃዊነት የማሰራጨቱ ሂደት ምን ያህል እየተፈጸመ መሆኑ መታየት እንዳለበትና ሌብነትና ሕገወጥነትን ለማስወገድ የተዘረጋው የግብይት ሥርዓትም አዋጪነቱና ተደራሽነቱ መፈተሽ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም እስከአሁን ተጓጉዞ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ማዳበሪያ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በአንዳንድ ዩኒየኖች እና ህብረት ሥራ ማህበራት በመጋዘን ተቀምጦ የሚገኝ የአፈር ማዳበሪያ እንዳለ በመስክ ምልከታ ወቅት መረጋገጡን ተናግረው፤ ይህንን ችግር በመፍታትና በአፋጣኝ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት ረገድ ሚኒስቴሩ ተጨባጭ ሥራ መሥራት ይገባዋል ሲሉም አመልክተዋል።
በመኸር ወቅትም ሆነ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከአምናው የተሻለ የማሳ ዝግጅት መኖሩን በመስክ ምልከታ ወቅት ቋሚ ኮሚቴው ማረጋገጡን የጠቆሙት ሰብሳቢው፤ አርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታ ምርጥ ዘር እንዲያመርት፣ ለዚህም ክልሎች በቂ መሬት እንዲያዘጋጁ ግንዛቤ መፍጠር ሥራ ሊተኮርበት ይገባል ነው ያሉት።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እንዳስገነዘቡት፤ ሚኒስቴሩ በሌማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በሌሎችም መስኮች የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቅበታል። በእነዚህም የልማት መስኮች በአፈር ማዳበሪያና በምርጥ ዘር ሥርጭት ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን በመመልከት አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ቋሚ ኮሚቴው በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ክልል ከተሞች ላይ ባደረገው የመስክ ምልከታ ልማቱ ይበልጥ በስፋት እንዳይሰራ የተጀመረው የከተማ ግብርና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ከተማን መሠረት አድርጎ ወደ ሥራ አለመግባት፣ የመዋቅር ችግር፣ የፕሮጀክት አለመኖር፣ የሎጅስቲክ እና የባለሙያ እጥረት ዋነኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ መቻሉን አብራርተዋል። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች በመፍታትም ረገድ ሚኒስቴሩ ቀጣይ የቤት ሥራው አድርጎ መንቀሳቀስ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በመስኖ ስንዴ ልማት ላይ አበረታች ውጤት እንደተገኘ ሁሉ የቡና ምርትን ለማሳደግም በዚሁ ልክ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንደሚገባው የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አስገንዝበዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በቡና ልማትና ከክልሎች የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር እና የተለየ ትኩረት በመስጠት ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በሀገራችን የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ ምርቶች አንዱ የሆነውን የቡና የግብይት ሥርዓት በተሻለ ለማሳለጥ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት በመሥራት የተሻለ ለውጥ ለማምጣት መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።
በሌላ በኩል እንደ ሀገር የተጀመረውን በምግብ ሰብል ራስን የመቻል ዘመቻና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ከእንሰት ጋር ተያይዞ የተሠሩ ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን እንሰት አብቃይ ለሆኑ ክልሎች ለዘርፉ የተዘጋጁትን ቴክኖሎጂዎች በማስተዋወቅ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
‹‹አሲዳማ አፈርን በሚመለከት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አበረታች ጅምር ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም ክልሎችም ባለቤት ሆነው እንዲሠሩ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል›› ብለዋል። አሲዳማ መሬቶችን ለማከም ሚኒስቴሩ እያከናወነ ያለውን ሥራ ክልሎች እንዲደግፉት በማድረግ መሥራት እንደሚገባም ነው የገለጹት።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ ዶክተር በበኩላቸው እንዳስታወቁት፤ በ2015/16 የምርት ዘመን በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት የነበረውን ችግር በመቅረፍ ለዘንድሮው የምርት ዘመን የግዥ ሥርዓቱን በማስተካከል ቀደም ብሎ የአፈር ማዳበሪያ በመገዛቱ 20 ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል። እስካሁን ባለው ሂደት 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ የጂቡቲ ወደብ ላይ እንደደረሰና ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ትልቅ መሻሻሎች ታይተዋል። ሀገር ውስጥ ከገባው 11 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል።
በዘጠኝ ወራቱ የዓመቱን ግብ ሊያሳካ በሚችል መልኩ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን መሥራታቸውን ጠቁመው፤ ‹‹ሞዴል አርሶ አደሮችን በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ የጀመርናቸውን ሥራዎች በማጠናከር እና ትኩረት አድርገን በመሥራት የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ሥራዎችን እንሠራለን›› ብለዋል። ተያይዞም ተጨማሪ ዘር የማምረትና የቀረበውን ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ በተገቢው ተደራሽ ለማድረግ በበጀት ዓመቱ ውጤታማ ሥራዎች መሥራታቸውን ጠቁመዋል። በተጨማሪም የግብርና ሜካናይዜሽን ማዕከላቱ ተጠናቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ የበኩላችንን ድጋፍ እናደርጋለንም ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በቋሚ ኮሚቴው የተነሳውን የሥርጭት ችግር አስመልክተው በአማራ ክልልና በአንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የጸጥታ ችግር ተቋቁሞ አሽከርካሪዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እያለፉ ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ ለማዳረስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ በሥርጭት ወቅት ሕገ ወጥነት ተግባር እያጋጠመ መሆኑን ጠቅሰው፣ ድርጊቱን በሚያከናውኑ አካላት ላይ ተገቢዎቹ ርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም በተያዘው ዓመት የመስኖ ስንዴ ልማት ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለት ነጥብ 97 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸው፤ እስካሁን 80 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል። ባለፈው ዓመት 47 ሚሊዮን ኩንታል ከበጋ ስንዴ መሰብሰቡን ሚኒስትሩ አስታውሰው፤ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የምርት አሰባሰብ ሂደቱ በእጥፍ እየጨመረ መሆኑን አንስተዋል።
በተመሳሳይ የቡና እና ሻይ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የተሠራው ሥራ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ በሆርቲካልቸር ዘርፍ እንዲሁ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በመጨመር ገበያን ለማረጋጋት የተሠራው ሥራ ውጤት ማስመዝገቡን አስታውቀዋል።
ባለፈው የመኸር ምርት 17 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሶ 506 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡ መቻሉን ተናግረዋል። በቀጣይም ሚኒስቴሩ ከቋሚ ኮሚቴው የተነሱ ጥያቄዎችና ምክረ ሃሳቦችን በመውሰድ ከተጠሪ ተቋማት ጋር የመፍትሔ ርምጃዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ዶክተር ግርማ አመላክተዋል።
አያይዘውም ሚኒስቴሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባከናወናቸው ተግባራት በተለይ አትክልትና ፍራፍሬዎች ላይ የዋጋ ለውጦች እንዲኖሩ ማስቻሉን ጠቁመዋል። በዶሮና እንቁላል ዋጋ ላይም ቅናሽ መታየቱን ጠቅሰው፤ በስንዴና የሌማት ትሩፋት ላይ ያሉ ተሞክሮዎችን በማስፋት የቡናና ሌሎች ሰብሎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፍያ ካሳ ዶክተር በበኩላቸው፤ በተያዘው የምርት ዘመን 16 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ መግባቱንና አምና በዚህ ወቅት የገባው 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል እንደነበር አስታወሰዋል። እስካሁን ባለው 11 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ መጓጓዙንና ከዚህም ውስጥ እስከ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ባለው 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል መሠራጨቱን እሳቸውም ገልጸዋል። በዚህ ረገድ በቋሚ ኮሚቴው ከሥርጭት ጋር ተያይዞ የተነሱ ውስንነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አምነው፤ ይሁንና አንድም ማዳበሪያ ያልተሰራጨበት አካባቢ አለ ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል። ያም ቢሆን ግን ሚኒስቴሩ ሥርጭቱንም ይበልጥ ለማቀላጠፍ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም