የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ተግዳሮቶች በጋራ ለመፍታት!

ከሀገሪቱ ዓመታዊ የካፒታል በጀት 60 በመቶው የሚንቀሳቀሰው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ነው።ኢንዱስትሪው የሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 25 በመቶው መሆኑንም መረጃዎች ያመለከታሉ።ከግብርናው ቀጥሎ በቀጥታና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለአያሌ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርም ኢንዱስትሪው በእጅጉ ይታወቃል።

የሀገር ዕድገት፤ የሀገር መሠረተ ልማት ግንባታ እና የሕዝብ ብልጽግና ሲታሰብ ቀድሞ ከሚመጡት የምጣኔ ሀብቱ ዘርፎች መካከል አንዱም ነው።ያለኢንዱስትሪ የተጠቀሱትን የሀገር አጀንዳዎች ማሳካት አይቻልም።

ይህ ግዙፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በሀገሪቱ በተገነቡ መሠረተ ልማቶች፣ በምጣኔ ሀብቱ ላይ በመጡ ዕድገቶች፣ በማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፉ በተገኙ ስኬቶች የራሱን ዐሻራ አሳርፏል።በተለያዩ ሥርዓቶች ውስጥ እየተነሳም እየወደቀ ሀገር አቅንቷል።

የሀገሪቱ የዘርፉ እቅዶች ብቻ ሳይሆን ሌሎች እቅዶችም ስኬታማ እንዲሆኑ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በማመን መንግሥት ይህ ዘርፍ ይበልጥ እንዲዘምን ለማድረግ ፣የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረቱ እንዲፈታ፣ የተቋራጮች አቅም እንዲጎለብት፣ አዳዲስ ተቋራጮች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ወዘተ በማድረግ በኩል ብዙ ሲሠራ ቆይቷል።ዘርፉ ስሙ በመጥፎ የሚነሳበት የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር እንዲፈታም የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አቋቁሞ ወደ ሥራ አስገብቷል፤ ሌሎች በርካታ ድጋፎችንም ማድረጉ ይታወቃል። ይህን ሁሉ ተከትሎም በዘርፉ መነቃቃቶች ታይተውም ነበር።

ይሁንና ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በተከሰቱ ዓለም አቀፋዊ፣ ሀገራዊና የየራሱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ችግሮች ሳቢያ ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ተግዳሮቶች ውስጥ ተተብትቦ ይገኛል።በኮንስትራክሽን ዘርፉ ተሰማርተው ሲሰሩ የቆዩ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ ወዘተ ህልውናቸው አደጋ ውስጥ መውደቁን እስከ መግለጽም ደርሰዋል።

ዘርፉ በአንድ በኩል ከፍተኛ የፕሮጀክት አስተዳደር ችግር፣ የግብአት አቅርቦት እጥረት፣ የሙያ ስነምግባር ግድፈት ወይም ብልሹ አሰራር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢንዱስትሪውን ባህሪ ባላገናዘበ የግዥ አሠራር፣ ከዋጋና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ እየተፈጠረ በሚገኝ ችግር እየተፈተነ ይገኛል።የክፍያ መዘግየት፣ የቴክኖሎጂ አቅም ውስንነት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ሌሎችም ተጨማሪ የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

የዘርፉን ችግሮች ለመለየትና ለመፍታት በተለይ በግሉ ዘርፍ ፣ ዘርፉን በሚመራው መንግሥታዊ አካል በኩል ጥናቶች እየተደረጉ ውይይት ሲደረግባቸው ቆይተዋል።የአሠራር ማሻሻያዎች በማድረግም ችግሮቹን ለመፍታት ተሞክሯል፡፡

ሰሞኑንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማና መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮንስትራክሽን ‹‹የኢንዱስትሪ ተግዳሮቶች – መውጫ መንገዶችና የሕግ አውጪው ሚና›› በሚል ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ እነዚሁ ችግሮች ተነስተዋል፤ መውጪያ መንገዶችም ተመላክተዋል።

በእዚህ የዘርፉ ተዋንያን በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የግሉም ዘርፍ፣ ሕግ አውጪውና ሕግ አስፈጻሚው አካላት በተገኙበት መድረክ የዘርፉን ችግሮች፣ መውጫ መንገዶች ያመላከቱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።በውይይቱም፤ የችግሮቹ ባለቤቶች እከሌ ነው፤ እከሌ ነው ከመባባል በመውጣት በጋራ ችግሮቹን ለመፍታት መረባረብ እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል።ሁሌም እየተገናኙ በመምከር ለችግሮች መፍትሔ ማመላከት እንደሚገባ፣ ያጋጠሙ ችግሮችንም እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የልማት መሣሪያ ማድረግ እንደሚያስፈል የሀገሮች ተሞክሮ ጭምር ተጠቅሶ መፍትሄ ተመላክቷል። ሁሉም የየድርሻውን ወስዶ እንዲሠራም ተጠቁሟል፡፡

መድረኩ መንግሥት የዘርፉን ችግሮች ለማዳመጥና መፍትሔ ለማስቀመጥ ያለውን ቁርጠኛ አቋም በእርግጥም ያሳየበት ነው ሊባል ይችላል። ችግሮችን መለየት መቻል የመፍትሔው አንድ እርምጃ ተደርጎ እንደሚወሰድ ሁሉ የዘርፉን ተግዳሮቶች መለየት መቻል በራሱ እንደ አንድ የመፍትሔ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል።

በዚህ ላይ ደግሞ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በራሱ ይዞ መድረኩን ማዘጋጀቱ፣ በዚህም የዘርፉን ቤተሰቦች በሙሉ አቀራርቦ ማወያየቱ ችግሮቹን ለመፍታት አሁንም አንድ ሌላ እርምጃ ተሄዷል ሊባል ይቻላል።

የዘርፉን ችግሮች በሚገባ ለይቶ መፍታት አማራጭ የሌለውና በፍጥነትም ሊሠራበት የሚገባ ተግባር ነው።ዘርፉ ለመሠረተ ልማት ግንባታ መሳለጥ፣ ሕዝቡን ከዚህ መሠረተ ልማት በወቅቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ፣ ለሀገር ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ወዘተ ካለው ፋይዳ አኳያ ችግሮቹን ለይቶ እየተመካከሩ ፈጥኖ መፍታት ልማቱን ማፋጠን እንደመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካል ከዚህ አኳያ የራሱን ድርሻ ወስዶ በትኩረት መሥራት ይጠበቅበታል።

ችግሮችን ወደ ሌላው መግፋት መፍትሔ አለመሆኑ ተለይቷል፤ መፍትሔው በጋራ መክሮ መፍታት እንደሆነና ለዚህ ደግሞ አንዱ ሥራ የየራስ ኃላፊነትን መወጣት መሆኑ ላይ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።ችግሮቹን አሠራር በማስቀመጥ መፍታት፣ የኢንዱስትሪውን ባህሪ ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ልዩ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በልዩ መንገድ ለመፍታት በጋራ በመምከር እርምጃ መውሰድም ያስፈልጋል።

እንደ ግዥ ሕጉ ያሉ አላሠራ ያሉ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ሕጎች እንዲሻሻሉ፣ ክፍያ ላይ የሚስተዋሉ መጓተቶች እንዲቀነሱ እንዲሁም እንዲወገዱ ፣ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግሮች በወሳኝ መልኩ እንዲፈቱ ፣ የግብአት ችግሮችን ለመፍታት ግብአቶችን በሀገር ውስጥ በማምረትና ከውጪ ለሚመጡ አስፈላጊ ግብአቶችም ድጋፍ ማድረግ ዘርፉን ከገባበት መቀዛቀዝ በማውጣት ወደፊት መራመድ እንዲችል ያግዛል።

ለእዚህ ደግሞ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ የራሱን ኃላፊነት መወጣት ያለበት መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ ችግሮችን ወደየትኛውም አካል ሳይገፉ በጋራ ተደማምጦና ተማምኖ መሥራት ያስፈልጋል።ይህ ሲሆን የኮንስትራክሽን ዘርፉን ብቻ ሳይሆን፣ የዘርፉ ተጠቃሚ የሆኑትን ሀገርንም ሕዝብንም መታደግ ይቻላል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You