በመመሪያ ክፍተት የሚሰቃዩት የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች

በዓለም ታሪክ የባቢሎኑ ሀሞራቢ የመጀመሪያውን “ኮድ ኦፍ ሎው” እንዳዘጋጀ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ። ይህ ሕግ ለዘመናዊ ሕጎች መነሻ ከሆኑት መካከል አንደኛ ሆኖ ይጠቀሳል። ለሀገረ መንግሥት ካስማ እና ምሰሶ ከሚባሉት መካከል የተደራጀ ሕግ መኖር ግንባር ቀደሙ ነው። ምክንያቱም ሕግ የሁሉም ነገር ማሰሪያ ቁልፍ ነውና።

ሕግ አምባገነን መንግሥታት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት የሚያበጁት እና የሚያጸድቁት መመሪያ ማለት አይደለም። ሕግ የሚሻሻል እና የሚዳብር እንጂ መንግሥታት ሲቀያየሩ ቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ የሚጨመር አይደለም። ይህ ማለት ግን መንግሥታት ሲተኩ የፖለቲካ ርዕዮተ አለማቸውን የሚያስፈጽሙበት የራሳቸውን አዲስ ፖሊሲ እና እስትራቴጂ መቅረጽ የለባቸውም ማለትም አይደለም።

ዋናው ጉዳይ የዳበረ ሕግ ያላት ሀገር፤ ዜጎች መብታቸውን ሳይ ሸማቀቁ ይጠይቃሉ፤ ግዴታቸውንም በወሰዱት መብት ልክ የሚወጡ ናቸው። ሕግ ዜጎች የሚያደርጓቸውን ድርጊቶች የሚገድብ ፣ መንግሥታት እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ስልጣናቸውን ተጠቅምው ሕዝብን እንዳይጎዱም የመቆጣጠሪያ አጥር ወይም ወሰን ነው።

ባለንበት ዘመን ሁሉም ነገር እየተራቀቀ በመምጣቱ መንግሥታትም በጊዜው ወቅቱን የሚመጥን፣ የተራቀቁ ኩነቶችን ለመቆጣጠር እና ለማስተዳደር የሚያስችሉ የተለያዩ መዋቅሮችን ሲዘረጉ ይስተዋላል። የተዘረጉ መዋቅሮች በሥርዓት እንዲመሩ ሕግጋት እና መመሪያዎች ይወጣሉ።

ነገር ግን የተዘረጉ የመንግሥት መዋቅሮች ሕግጋት እና መመሪያዎች የማይቀመጥላቸው ከሆነ ግለሰቦች እና የመንግሥት ባለስልጣናትም እንደፈለጉ እንዲሆኑ በር ይከፍታል። በሰዎች ህይወት እና ንብረት ላይ አደጋ ይደርሳል። ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከተመሰረተች በርካታ ዘመናትን ብታስቆጥርም ጥንቅቅ ብለው የተደራጁ የተቋማት መዋቅር እና ሕግጋት አሏት ለማለት ግን አያስደፍርም።

ለዚህ በርካታ ምክንያቶች እንደሚኖሩ እርግጥ ነው። ለዛሬው ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ግን በኢትዮጵያ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም ቤቶች) ዙሪያ ከሕግ እና መመሪያዎች ክፍቶች ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ ችግርች አሳሳቢ በመሆናቸው ነው። የጋራ መኖሪያ ቤት በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያለው አይደለም። ይሁን እንጂ ቤቶቹን የሚቆጣጠረው ተቋም በወጥነት ቤቶችን ለማስተዳደር የሚችልበትን የሕግጋት እና መመሪያዎች ማዘጋጀት ይገባዋል።

ይህ ሲባል አሁን የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የሚያስተዳድር ተቋም ምንም አይነት መመሪያ እና ሕጎች የሉትም ማለት አይደለም። ነገር ግን ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከዚህ ቀደም ከነበሩ መመሪያዎች በተጨማሪ ሌሎች ሕግጋት እና መመሪያዎች ማዘጋጀት እንደሚገባ ለማመላከት ነው።

የሕግ አንደኛው አስፈላጊነት በአንድ ሀገር ተመሳሳይ ወይም ወጥነት ያለው ሥራዎችን ለማከናወን ነው። ይሁን እንጂ በሀገራችን በተለይም በአዲስ አበባ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚተዳደሩበት ወጥ የሆነ መመሪያ ያላቸው አይመስልም። ለሥራ በተንቀሳቀስኩባቸው በአዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የመመሪያ ክፍተቶች በመኖራቸው በርካቶች እንደፈለጉ ሲሆኑ አስተውያለሁ።

እነኝህ የመመሪያ ክፍተቶች መካከል አንደኛው የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ይዞታ ለጸጥታ በሚል ሸፋን ማጠር፤ በዚህም አጥር ውስጥ የሚገቡ እና የሚወጡ ተሽከርካሪዎችን ያልተገባ ክፍያ መጠየቅ እና ማንገላታት አንደኛው ነው። ሁለተኛ በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገኙ የንግድ ቤቶች ምን መምሰል እንዳለባቸው የሕግ ክፍትት ያለ ይመስለኛል።

በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገነቡ የንግድ ቤቶች የተገነቡበት ዋና ምክንያት በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገኙ ዜጎችን ለማገልገል ታስቦ ነው። ይሁን እንጂ የንግድ ቤቶች የሚያደርጉት ድርጊት በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚኖሩ ዜጎች ከሚፈልጉት በተቃራኒው ነው።

ለምሳሌ በጋራ መኖሪያ ቤቶች የጭፈራ ቤቶች ይገኛሉ። እነኝህ የጭፈራ ቤቶች “አስረሽ ምችው” ሲሉ ነጭ ወረቀት የሆኑ ሕፃናት እና የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች የሚያዩ ከሆነ እነሱም አስረሽ ምችውን “እንሞክረው” ማለታቸው የማይቀር ነው። ይህ መሆኑ የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዳነሳ አስገድዶኛል።

መጫወቻ እያዩ ማደግ የሚገባቸው ሕፃናት ስለምን በአልኮል አንኮላው የዞረን ሰው እያዩ እንዲያድጉ ይፈረድባቸዋል? ተማሪዎችስ ስለምን ሃሳባቸውን ሰብስበው እንዳያነቡ ይከለከላሉ? ቀኑን ሙሉ በሥራ ተወጥሮ ድካም ውስጥ ያለ አባወራ ወይም እማወራ ስለምን በቤቱ እንዳያርፍ ይደረጋል? ይህ አሁኑኑ በመመሪያ መልስ የሚያስፈልገው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ችግር ነው ።

ከንግድ ቤት ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው እና በተለያዩ ወረዳዎች እንዲሁም ክፍለ ከተማዎች የሚገኙ የንግድ ጽህፈት ቤት ባለሙያዎችን እና አመራሮችን አነጋግሬ ነበር። ጽህፈት ቤቶቹም “በጋራ መኖሪያ ቤቶች ምን አይነት ንግድ ፈቃድ ይሰጥ ወይም አይሰጥ የሚል መመሪያ ስለሌለ ባር እና ሬስቶራንት ብሎ የሚጠይቅ መስፈርቱን የሚያሟላ ነጋዴ ከመጣ ፈቃድ ይሰጣል። አሁን ላይ ፈቃድ የሚሰጠው “በኦንላይን” በመሆኑ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል።” የሚል ምላሽ ሰጥውኛል።

ሌላው በጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚስተዋለው ችግር ደግሞ ከተሽከርካሪዎች ፓርኪንግ ጋር የተያያዘ ነው። ከፓርኪንግ ጋር ተያይዞ በወር እስከ 800 ብር የሚያስከፍሉ የጋራ መኖሪያ ቤት ማህበራት መኖራቸው ይነገራል። ይህ ትክክል አይመስለኝም። ከቤት እድሳት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር ደግሞ ሌላኛው የጋራ መኖሪያ ቤት መገለጫ ነው ።

የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሳቸው ሰዎች ከዋናው የቤቱ ገጽታ ውጭ ያለውን በተለይም የውስጠኛውን ክፍል እንደፈለጉ አድርገው አፍርሰው ሲገነቡ ይስተዋላል። ይህን ሲያደርጉ ከላይ እና ከታች እንዲሁም ከጎን ያሉ ጎረቤቶቻቸውን ይረብሻሉ። የተገነባውን አፍርሶ ለመገንባት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሕንጻ መደርመስም ሊያጋጥም ይችላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሥራ አጋጣሚ ያነጋገርኩት አንድ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ሠራተኛ ከቤቶች እድሳት ጋር በተያያዘ ምንም አይነት መመሪያ አለመኖሩን ገለጸልኝ። ስለእውነት ይህን ማመን የሚቻል አይደለም ።

የጋራ መኖሪያ ቤት የማህበር ኮሚቴዎች ነዋሪዎችን አሰላችተዋል። በርካታ ድርጊቶቻቸውም አሳፋሪ ናቸው። “ሞኝ ባያፍር፤ የሞኝ ዘመድ ያፍር” እንዲሉ የጋራ መኖሪያ ቤት የማህበራት ኮሚቴዎች እነሱ ማፈርን ቢያቆሙም የሚሠሩት ሥራ ግን ወገን እና ሀገርንም የሚያሳፍር ነው። በተጨማሪም የጋራ መኖሪያ ቤት የማህበራት ኮሚቴዎች ራሰ ገዝ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ኮሚቴዎቹ “ማህበሩ በጠቅላላ ጉባኤ የወሰነው ውሳኔ ነው” በሚል የሞኝ ፈሊጥ የሀገሪቱን ሕግ መንግሥት እና ሌሎች ሕጎች ዓይናቸውን ጨፍነው ሲጥሱ ይስተዋል።

ለምን የሚል የመንግሥት አካልም አይታይም። ከላይ የጠቀስናቸውን ችግሮች እና ሌሎችም በዚህ ጽሁፍ ያልገለጽኳቸው አደባባዮችን ያጣበቡ ችግሮችን መቅረፍ የሚቻለው ወጥ የሆነ መመሪያ በማጽደቅ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥበት ይገባል።

ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You