ወደ እርቅ ትውልድ ሽግግር

ሀገራችን ኢትዮጵያ ‹እርቅ ደም ያድርቅ› በሚል መነሾ ሃሳብና ‹ከነጣጣይ ትርክት ወደአቃፊ ትርክት› በሚል ሚዛን ገፊ ምክረ ሃሳብ ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁማ፣ በመንግሥትና በሌሎች አካላትም መሃል መነጋገርን ለመፍጠር ረጅም ርቀት መራመድ ጀምራለች:: በተለይ መንግሥት ተቃዋሚ ሃይሎችን ወደሰላም ከመጥራት አኳያና የሰላምን አስፈላጊነት በየመድረኩ በመናገር ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት እያሳየ ይገኛል::

ሰላም ያጣንበት ያለፈው ጊዜ ይብቃን መጪውን ጊዜ በጋራ እንቀበል በሚመስል መነቃቃት አብሮነትን ለመፍጠር በተለያዩ መድረኮች ላይ ሰላም ሰባኪ ድምጾችን ሰምተናል፣ እየሰማንም እንገኛለን:: እኚህ ድምጾች መንግሥት ምን ያክል ሰላም ወዳድና የኢትዮጵያም ሕዝብ ሰላም ፈላጊ እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው:: የሰላም አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ባይሆንም አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ተነስተን ግን ያለሰላም አንዳች አማራጭ እንደሌለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን::

በብሄራዊ ምክክርም ሆነ በመንግሥት በኩል ቅድሚያ የተሰጣቸው የሰላም አማራጮች ዋና ዓላማቸው አብሮነትን ማጽናት፣ የጋራ ሀገር መፍጠር፣ በእርቅና በምክክር ወደነገ መሻገር የሚል ተልእኮ ያላቸው ናቸው:: ከዚህ በተጨማሪ እልህና ጥላቻን በማስቀረት መነጋገር የገዘፈበትን የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር፣ ጠያቂና የመፍትሄ አካል የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር የሚሉም አሉበት:: ችግሮችን በመነጋገር በመፍታት ሰላማዊ ኢትዮጵያን መፍጠር ሌላኛው ተልዕኮው ሲሆን ይሄን መሰሉ አካሄድ በመንግሥት በኩል አጽንኦት ተሰጥቶት እየተሠራበት ነው::

ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ አጋጣሚዎች ላይ ስለ ሰላም በመናገር፣ ጦርነትና መገፋፋት ከቂም በቀል ውጪ ሀገር እንደማይቀይር በማውሳት ሁሉንም ጥያቄ ያላቸውን ሃይሎች ለሰላም ጥሪ በማድረግ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት እያሳየ ይገኛል:: ከሰሞኑ በጉራጌ ዞን በወልቅጤ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሰል መልዕክትን አስተላልፈዋል:: ‹ስለሰላም ሳናስብ፣ ሳንኖር፣ ሳንናገር ሰላምን ልንጎናጸፍ አንችልም:: ኢትዮጵያውያን ሁላችንም ሰላምን አብዝቶ በመሻት፣ በአብሮነት በመኖር የበለጸገችና ለሁሉ የምትመችን ኢትዮጵያ መፍጠር አለብን› ሲሉ ተናግረዋል::

በመንግሥት በኩል የሚነገሩ ሰላም ተኮር የጥሪ መልዕክቶች መንግሥት ለሰላም ያለውን ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት በግልጽ ከማሳየቱ ጎን ለጎን ተነጋግሮ ከመግባባት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለንም ጥቁምታ የሚሰጥ ጭምር ነው:: መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀሱ በጠመንጃ የሚሆን ነገር ስለሌለና ሁሉም ሃይሎች በሃሳብ የበላይነት እንዲያምኑ ከመፈለግ የመነጨ እንጂ ከድካምና ከዝለት የመነጨ እንዳይደለ ሊታሰብ ይገባል::

ሰላማዊ ምክክር፣ የሃሳብ የበላይነት፣ እርቅና ትቅቅፍ ያለበት ፖለቲካ ሀገር የምትድንበት የመፍትሄ ሃሳብ ነው:: ቁርጠኝነቱ ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች መሃል የመጀመሪያ ሆኖ የሚነሳው ደግሞ በኮሚሽን ደረጃ የተዋቀረው ነጻና ገለልተኛ፣ አሳታፊና ሕዝባዊ በሚል ስም የሚጠራው ብሄራዊ ምክክር አንዱ ነው:: በሃሳብ የዳበረ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ፖለቲካ፣ አዲስ ትውልድ ለመፍጠር የበረታ ሂደት ላይ የሚገኘው ኮሚሽኑ ከተስፋችን መንደር ያደርሰናል ተብሎ ይጠበቃል::

ሌላው ከመልካም ጉርብትና ጎን ለጎን የልማትና የኢኮኖሚ ትሩፋቶች ሆነው ከፊት ከሚመጡ ሁነቶች ውስጥ ቀዳሚው ሰላማዊ ትውልድ ነው:: ሰላማዊ ትውልድ የብልጽግናና የሀገር ፍቅር ፊት ተሰላፊ ነው:: በፍቅር ስም የሀገርን አንድነት ከማረጋገጥ አኳያም ሚናው የትየለሌ ነው:: ትውልድ በትናንትና በዛሬ በነገም የታሪክና የእሴት ቅብብሎሽ የሚበለጽግ የሀገር አንጓ ነው:: ይሄ አንጓ በጥላቻ ቅንጥስ እንዳይል፣ በዘርና ብሄር እንዳይቧደን ሰላማዊ ተግባቦት የጸናበት ትክክት ያስፈልጋል::

ወደ እርቅ ሽግግር እንደሀገር የነበሩብንን የጥላቻ ትርክት ጥለን፣ ባሉንና የጋራችን በሆኑ እሴቶቻችን ወደፊት የምንሄድበት ነው:: ወጣቱ ስለኢትዮጵያዊነት በአሉባልታ ከሰማው ይልቅ እውነቱን የሚያውቅበትን፣ በእንዴት ያለአብሮነት አብረን እየበላንና እየጠጣን እንደመጣን የሚረዳበት ሁነኛ መምህር ያስፈልገዋል:: መምህሩ ደግሞ ፖለቲካውና ፖለቲከኞች ናቸው:: እኔና ሌላው ሰው ነን:: ፍቅርን ለመስበክ፣ እውነትን ለመመስከር ራሱን ያገለለ ዜጋ ከወንበዴዎች እንደአንዱ ነው::

ለራስ ጥቅም የሰፋን ግዛት አጥቦ፣ የገዘፈን ማንነት አሳንሶ መናገር የዚህ ትውልድ የፖለቲከኞች ሴራ ቢሆንም ከዚህ እብለት ርቀው የተቀመጡትን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ልንገልጥና እውነቱን ልንመሰክር ይገባል:: በጦርነት ጀብደኝነት ኒሻንና ክብር ያገኘንባቸው ታሪኮቻችን በፍቅርና በይቅርታ ተቀይረው ጀግና ማለት ፍቅርን የሚያውቅ ነው በሚል ብሄል ቀይረን ትውልዱን የፍቅር ጀግና ልናደርገው ይገባል::

ወደ እድገት ሽግግር ላይ ነን:: ራስን በምግብ የመቻል፣ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለመላቀቅ ጥረት ላይ ነን:: የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር፣ በአብሮነቱ የሚደነቅ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሽግግር ላይ ነን:: በጤናው፣ በግብርናው፣ በኢንዱስትሪው፣ በትምህርቱ ዘርፍ ትውልድ ቀረጻ ላይ ነን:: በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምርምር እየላቅን ነው::

በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በማህበራዊ መስተጋብርና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ልቀን ለመውጣት ሽግግር ላይ ነን:: በህዳሴ ግድብና በቀይ ባህር ባለቤትነት ፊተኝነትን እያገኘን ነው:: እንደብሪክስ ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ፣ እንደኢጋድ፣ እንደአፍሪካ ህብረት፣ እንደ ጸጥታው ምክር ቤት ባሉ ድንበር ዘለል ተቋማት ውስጥ ሚና አለን እኚህ ሁሉ ቀጣናዊና አህጉራዊ ዓለምአቀፋዊ ሚናዎች ዋጋ የሚኖራቸው ሰላም ተኮር ፖለቲካና ማህበራዊ ምህዳር ስንገነባ ነው::

ተነጋግረን ሳንግባባ፣ ቁርሾዎቻችን ወደጦርነት እየወሰዱን ባለበት ሁኔታ የምናመጣው ለውጥ የለም ቢመጣ እንኳን እየገነባን የምናፈርሰው፣ እየተከልን የምንነቅለው ታሪክ ነው የሚሆነው:: ባለፉት የጦርነት ጊዜዎች ሁሉንም አይነት ሀገራዊ ተግዳሮት አስተናግደናል:: ከሰው ሕይወት መጥፋት፣ እስከ አካል መጉደል፣ ከመፈናቀል እስከ ንብረት መውደም ድረስ ሁሉም ደርሶብናል:: ኢኮኖሚያዊና ሥነልቦናዊ ጫናዎቻችን ዛሬም ድረስ አለቀቁንም::

ካለፈው መማር ለምን እንዳቃተን ያልገባኝ የማይገባኝ ጉዳይ ነው:: ብልህነት መነሻው ከትናንት መማር ዛሬን አጥብቆ መያዝና ነገን ተስፋ ማድረግ ነው:: የእኛ ዘወትራዊ ሁኔታ ከትናንት መማር ሳይሆን ትናንትን መድገም ነው:: ታሪኮቻችን እኛን ለማስተማር በቂዎች ናቸው:: ከግለሰብ እስከማህበረሰብ ድረስ ጦርነት አቁስሎናል:: አዝሎናል:: አስጎንብሶናል:: ይሄን ለማንም የማይበጅ፣ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለውን የወንድማማቾች ትግል በፍቅርና በይቅርታ፣ በመነጋገርና በመወያየት ማሳፈር ስንችል ለዳግም ስቃይ እዛና እዚህ ሆነን ይዋጣልን ማለት እጅግ የሚያሳዝን ነገር ነው::

ጦርነት ምንም ውበት የለውም:: የሰላም ምንጭም ሆኖ አያውቅም:: ሲጀምር ብዙ አጃቢዎች አሉት:: መሀል ላይ ግን አንዳቸውም አጃቢዎች አብረው አይቀጥሉም:: በለው በማለት የመጀመሪያውን ጥይት ከተኮሱ በኋላ ምንም ለማያውቀው ምስኪን አስረክበው ደብዛቸውን ያጠፋሉ:: ከተሳካላቸው ቦታ ይቀይራሉ ካልሆነላቸው ደግሞ ወጣቱን አስጨርሰው ባሉበት ይቆያሉ::

ጦርነትን ለሰላም የሚጠቀሙ እነርሱ ያልነቁ፣ ያልበቁ ፖለቲከኞችና ቡድኖች ናቸው:: ሀገር መውደድ በጦርነት አይገለጽም ፍቅር ጠብ በተደረገበት ሰውነት እንጂ:: ተፋልመን ገለንና ሞተን እናውቃለን:: በእርስ በርስ ግጭት ልጆችን ያለአሳዳጊ፣ ቤተሰብን ያለጠባቂ በትነን እናውቃለን:: ሌላው የጦርነት አስከፊ ገጽታ ከዛሬ ወደነገ መሄዱ ነው:: እዚህ ጋ ልብ እንድትሉኝ እፈልጋለው..ዛሬ እየሞትንና እየተገፋፋን ያለነው ምናቸውንም በማናውቃቸው የትናንት ቁርሾዎች ነው::

የዛሬ መገፋፋቶች ደግሞ ለነገ የሚቀመጡ፣ መጪው ትውልድ ሀገር አለኝ፣ ወገን አለኝ ብሎ በሰላም እንዳይኖር የሚያደርግ እዳ ነው:: ይሄ የትውልድ እዳ በፍቅር ካልተከፈለ፣ በይቅርታ ካልታለፈ መቆሚያ የለውም:: ለዛም ነው መንግሥት አብዝቶ ስለሰላም የሚጮኸው:: ለዛም ነው በብሄራዊ ምክክር ብሄራዊ እርቅ እናምጣ ስንል የምንናገረው::

ብሄራዊ እርቅ ብሄራዊ ሰላም የሚወርድበት፣ የትናንት ትርክቶች የሚሽሩበት አዲስ የሰላም ፋይል የሚከፈትበት መድረክ ነው:: ትናንትን በይቅርታ፣ ዛሬን በእርቅ፣ ነገን በፍቅር የምንቀበልበት የሽግግር አውዳችን ነው:: በተውጣጣ ሃሳብ ሕዝባዊነትን ያቀፈ፣ በምክንያታዊነት እና በስሌት፣ በአሳታፊነትና ገለልተኛነት ልዩነትን በማጥበብ፣ አንድነትን በማግዘፍ በጋራ ለጋራ የምንሰራበት የተሀድሶ አቅጣጫችን ነው::

በዚህ አይነቱ አቃፊና አንቂ መድረክ ፊት ተወያይተን ካልተግባባን በአፈሙዝ ብቻ የምንፈታው ቋጠሮ የለም:: አፈሙዛችን ሰላምን አላመጣልንም:: እልሃችን አንድነትን አልሰጠንም:: ሰላም በአፈሙዝ ቢሆን ኖሮ ዓለም ላይ በሰላም ቀዳሚዎቹ እንሆን ነበር:: ግን እንደዛ አልሆነም በተቃራኒው ቃታዎቻችን አንድነታችንን እየሸረሸሩ ሰላም የለሾች አድርገውናል:: መፍትሄው ቃታ መሳብ አቁመን ሃሳብ ማዋጣት ነው:: ጠመንጃ መወልወል ሳይሆን ለተሻለ ሃሳብ ጉሮሮ መሞረድ ነው::

መጨረሻችን ይናፍቀኛል.. ለምን መጨረሻ አልባዎች እንደሆንን ታውቃላችሁ? ከጦርነት አስተሳሰብ ስላልወጣን ነው:: እኩይ ሃሳብ እኩይ ድርጊትን ነው የሚወልደው:: ሃሳብ መሰሉን ነው የሚስበው:: የጦርነት አስተሳሰቦቻችን ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውን፣ ማህበራዊ ሕይወታችንን አበላሽቶብናል:: እየተፈራራንና እየተሰጋጋን የቆምነው ለምን ሆነና? ወጥቶ መግባት፣ ሰርቶ ማትረፍ ጭንቅ የሆነብን ለምን ሆነና? አቅጣጫዎቻችንን እስካልቀየርን ድረስ ከነበርንበት የሚታደገን አይኖርም::

ጦርነት ዛሬ ላይ አያበቃም..አብቅቶም አያውቅም:: እንደወረርሽኝ ነው ምንም የማያውቀውን ትውልድ ሊሰይፍ ጊዜና ቀን ቆጥሮ እንደእሳተ ገሞራ ድንገት የሚፈነዳ:: በፍቅር ስም እዚህ ጋ ካልገዘትነው፣ በይቅርታና በእርቅ አሁን ላይ ካላስቆምንው ወደነገ የሚሄድ ነው:: ብሄራዊ ምክክር ብሄራዊ እርቅን ሊሰጠን እየጠበቀን ነው:: ሁላችንም የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆነን ሀገራችንን፣ ሕዝባችንን ከሞትና ከመከራ ካልታደግነው መሰል እድሎችን ለማግኘት ዓመታት መጠበቅ ግድ ይለናል::

ብሄራዊ ምክክር ስለሰላምና አብሮነት እጃችን ላይ ያለ ወርቃማ እድላችን ነው:: ሁሉን ነኪና አሳታፊ በሆነ ሂደት ለዓመታት መሰንበቱ ይታወቃል:: ምን እንደምንፈልግ፣ ምን እንደጎደለን፣ ምናችን እንደተነካ፣ እንደመንግሥት፣ እንደዜጋ፣ እንደጠያቂ በነጻነት ተናግረን በነጻነት መልስ የምናገኝበት ነው:: በእርቅና በይቅርታ፣ በካሳና በፍቅር የበለጸገው ብሄራዊ ምክክር ኢትዮጵያን ከነሕዝቦቿ ከዚህኛው ወደብ ወደዛኛው ወደን ሊያሻግር የእኛን ንቃት እየጠበቀ ይገኛል::

ጦርነት አክሳሪና ሕይወት ቀጣፊ እንደሆነ ገብቶን የምንዋጋ ነን:: ታዲያ ይሄ አይገርምም ትላላችሁ? እንደዚህ የሚገርም በዓለም ላይ ምን አለ? ለማይጠቅመን ነገር እየሞትንና እየገደልን ያለን ሕዝቦች ነን:: ሳንሞትና ሳንገል በሃሳብ ልውውጥ ብቻ ብዙ ነገሮችን ማስተካከል እንደሚቻል ማወቅ አዲስ አቅጣጫን የሚሰጠን ነው:: እርግጥ ነው ብዙ ጥያቄ ሊኖረን ይችላል፣ ቅሬታ የፈጠረብን፣ ያልተስተካከሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ እኚሁ ሁሉ ነገሮች ግን ሞት ሳይሆን የሃሳብ ሙግት ነው የሚያስፈልጋቸው::

ውስጣዊ ሰላማችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በር ከፋች ነው:: ሳንስማማና ሳንተቃቀፍ በሮች ይዘጉብናል እንጂ አይበረገዱልንም:: ለጀመርነው ሀገራዊ ለውጥና ተሀድሶ ውስጣዊ ሰላማችን የላቀ ድርሻ አለው:: ከሁሉ በላይ ከግጭት ይልቅ የሰላምን በር፣ ከንትርክ ይልቅ የውይይትን በር እንክፈት ::

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You