ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በመከተል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል ይገባል

አዲስ አበባ፦ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በመከተል እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት መከላከል እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የዓለም የደም ግፊት ቀን “ደም ግፊትዎን ይለኩ፣ ይቆጣጠሩ እና ረጅም እድሜ ይኑሩ” በሚል መሪ ቃል ከትናንት በስቲያ ተከብሯል። በእለቱ ነፃ የኩላሊት፣ የደም ግፊት፣ የስኳር ምርመራ እና የማማከር አገልግሎት በብሔራዊ ቴያትር ተሰጥቷል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሂወት ሰለሞን በወቅቱ እንደገለጹት፤ በዓለም ላይ በየዓመቱ ከሚሞቱት ሰዎች ውስጥ 31 በመቶ የሚሆኑት በልብ ነክ በሽታዎች ሳቢያ ነው። የልብና ደም ስር በሽታዎች ከአጠቃላይ ሞት ውስጥ 16 በመቶ ድርሻ ይወስዳሉ። ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች አማካኝነት ከሚከሰተው ሞት ውስጥ ስትሮክና ድንገተኛ የልብ ህመም ከፍተኛ ድርሻ ይይዛሉ።

ስትሮክ በ100 ሺህ ሰዎች ውስጥ 83 ነጥብ ሰባት በመቶ ሞት ሲያስከትል፤ ድንገተኛ የልብ ሕመም በ100 ሺህ ሰዎች ውስጥ 77 ነጥብ አምስት በመቶ ሞት ያስከትላል ያሉት ዶክተር ሂወት፤ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት በመከላከሉ ረገድ ኅብረተሰቡ የበኩሉን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የደም ግፊት መጨመር ለስትሮክ እና ለድንገተኛ የልብ ህመም ዋነኛው አጋላጭ መንስኤ ነው ያሉት ዶክተር ሂወት፤ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በመከተል፣ የደም ግፊት ቅድመ ምርመራና ሕክምና በማድረግ በልብ ነክ በሽታዎች አማካኝነት የሚከሰተውን ሞትና የአካል ጉዳት መቀነስ ይቻላል ብለዋል።

እንደ ዶክተር ሂወት ገለፃ፤ ከፍተኛ የደም ግፊት ድምጽ አልባ ገዳይ በመባል ይታወቃል። ምክንያቱም ከፍተኛ የደም ግፊት አብዛኛውን ጊዜ ምልክት የለውም። ለከፍተኛ ደም ግፊት የሚያጋልጠው ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ጨው የበዛበት ምግብ መመገብ፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን ያለፈ የአልኮል መጠጥ፣ ከልክ ያለፈ የሰውነት ውፍረት እና የእድሜ መጨመር ናቸው።

ጤናማ የኑሮ ዘይቤን በመከተል የደም ግፊት በሽታን መከላከል ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ አዋቂዎች ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የደም ግፊት ቅድመ ምርመራ ሊያደርጉ ይገባል ያሉት ዶክተር ሂወት፤ ይህም በሽታውን አስቀድም ለማወቅና አስፈላጊውን ሕክምና ለመውሰድ ይጠቅማል ብለዋል።

የደም ግፊትን መለካት የልብ ነክ በሽታዎች፣ የኩላሊት ሕመም፣ አካል ጉዳተኝነትና ድንገተኛ ሞት ሳይከሰት በፊት በሽታው እንዲታወቅ ያደርጋል ያሉት ዶክተር ሂወት፤ ኅብረተሰቡ የደም ግፊት ምርመራ ማድረግን ባህል ሊያደርገው እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሽታውን አስቀድመን ማወቁ ደግሞ ብቻውን በቂ አይሆንም በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጠንን ምክርና ሕክምና መከታተል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የዓለም የደም ግፊት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን፤ የደም ግፊት መጨመር ምጣኔን ከነበረው ከ74 በመቶ ወደ 40 በመቶ ለማውረድ መታቀዱ ተገልጿል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You