በግጭት አካባቢዎች የተመደቡ ሚድዋይፎች አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን እናቶችና ሕፃናትን አገልግለዋል

አዲስ አበባ፦ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የተመደቡ 200 ሚድዋይፎች ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ለሆኑ እናቶችና ሕፃናት የሕክምና አገልግሎት መስጠታቸውን የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ገለጸ።

ዓለም አቀፉ የሚድዋይፎች ቀን “የሚድዋይፎች እንክብካቤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የጤና ሥርዓት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ለ32ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ተከብሯል።

በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሚድዋይፎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሰለሞን ኃይለመስቀል (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ማለትም አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተመደቡ ባለሙያዎች ለአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን እናቶችና ሕፃናት የሕክምና አገልግሎት ሰጥተዋል።

ባለሙያዎቹ በግጭት ቀጣናዎች በመጀመሪያ ደረጃ ተጎጂ ሊሆኑ የሚችሉትን እናቶች እና ሕፃናትን በመታደግ እንዲሁም በማገዝ የራሳቸውን አወንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት ተነሳሽነት የወሰዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በዚህም በግጭቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የወሊድ አገልግሎት፣ የእርግዝና ክትትል፣ ድህረ ወሊድ፣ የቤተሰብ ምጣኔን ጨምሮ የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል። በወሊድ ወቅት ሊፈጠር የሚችለውን የከፋ ነገርም እንደ ባለሙያም ሆነ እንደ ሚድዋይፍ መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል።

በሀገሪቱ ሃያ ሁለት ሺህ ያህል የሚድዋይፎች ቢኖሩም ከሀገሪቷ የሕዝብ ቁጥር አንፃር ግን አነስተኛ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ በትምህርት ደረጃም ለማደግ ያለው እድል አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉ ከእናቶችና ሕፃናት ጤና ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲሠራ ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ሚድዋይፎችን ከማብቃትና ሥራውን የተሻለ ለማድረግ ከማሰብ አንጻር በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ያመላከቱት ፕሬዚዳንቱ፤ ከዚህ ቀደም ከ100 ሺህ እናቶች አንድ ሺ 800 ያህሉ ይሞቱ እንደነበር በማውሳት፤ አሁን ላይ ቁጥሩ ወደ 267 ዝቅ ማለቱን እንዲሁም የጨቅላ ሕፃናት ሞት ደግሞ ከ100 ሺህ አንድ ሺህ ይሞቱ የነበረውን ወደ 27 ሕፃናት ዝቅ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You