“ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን” (የአበው ምርቃት

ከማህበረ-ባህላዊ እሴቶች አንዱ ምርቃት ነው። ከስነልቦና ሕክምናዎች አንዱ ምርቃት ነው። “ወልዳችሁ ሳሙ፤ ዘርታችሁ ቃሙ” እንዲል ስነቃሉ፣ ከበጎ በጎውን መመኛ መንገዶች አንዱ ምርቃት ነው። ማህበረሰብን እንደ ማህበረሰብ ከሚያስቀጥሉት ማህበራዊ ተግባራት አንዱ ምርቃት (መመረቅ፤ መመራረቅ) ነው። አዎ፣ የእርግማን ቀጥተኛ ተፃራሪም ምርቃትና ምርቃት፤ እንዲሁም “በረከት” ነው።

በአንድ ሀገር የወል/የጋራ መንፈሳዊ ሀብቶች ያሉ ሲሆን አንዱም ምርቃት ነው። ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አጠቃላይ ማህበረሰብ እና ሕዝብ ድረስ ምኞት፣ ተስፋና እና ህልም እውን ይሆኑ ዘንድ የሚታወጅበት በአደባባይ የሚገለፅበት፤ ሀገር ሰላም ውላ ሰላም ታድር ዘንድ ለፈጣሪ “አቤት” የሚባልበት ወዘተ ኢትዮጵያዊ ትውፊትና እሴት ቢኖር ምርቃት ነው።

ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አጠቃላይ ሕዝቡ ድረስ መንፈሳዊ ብርታትን የሚሰጥ መንፈሳዊ ሀብት ቢኖር እሱ ምርቃት ነው። ባህልን፣ እምነትን፣ ስነልቦናን፣ ስነማህበረሰብን፣ ስነአእምሮን ወዘተ አጣምሮ የያዘ ማህበራዊ ትውፊት ቢኖር ምርቃት ነው። “ሀገራችንን ሰላም አድርግልን”ም የዚሁ አካልና አምሳል ነው።

በዘርፉ ጥናት ያደረጉት በጅጋ “የምርቃት ስነ[1]ቃላዊ ፍቺ“ (Etymological definition) በሚል ርእስ ስር እንዳሰፈሩት ከሆነ፣ በኦሮሚኛ Eebaa፤ በአማርኛ (ቡራኬ(תֹוכָרְּב .pl; ‎הָכָרְּב በእብራይስጥ ምርቃት፤ berakhot, brokhoys፤ በእንግሊዘኛው ደግሞ bene[1]diction ወይም blessing የሚሉት አቻ ቃላት ናቸው። “ምርቃት” ስንል “መራቂ”ም አለና፤ መራቂ ከፍተኛ መንፈሳዊ የስልጣን (በጅጋ “በአምላክ አበርክቶ ወይም በዘመንና በእውቀት መገለጥ የሚገኝ የመንፈሳዊ ህይወት መገለጫ” ሲል ይፈታዋል) ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው መሆኑን፤ ምርቃት የመመረቅ ኃላፊነትን በተመለከተም፣ “በአያና/ውቃቢው የተመረጡ መንፈሳዊ አገልግሎት ያላቸው ሰዎች፣ ሽማግሌዎች/ አሮጊቶች፣ አባገዳዎች ደግሞ እንደየ ማዕረጋቸው ምርቃት የመስጠት ስልጣን” ያላቸው (በጅጋ እንደሚለው) መሆናቸውን ብቻ ጠቅሰን እንለፍ። ሁሉም እንደሚስማማው፣ ምርቃት የሰለጠነ ማህበረሰብ የሚከውነው ስልጡን ተግባር ነው። በ“አሜን” የታሰረ የአንድነት፣ አንድ የመሆን ቋጠሮ ነው። “Eebaa/ምርቃት/ቡራኬ/Blessing፦ የትኛውም እምነት የወል/የጋራ የሆነ ማህበር ለመለኮታዊ ኃይል የሚቀርብ የፀሎት፣ ትምህርት፣ የመርሀ ግብር ክፍል ወይም በራሱ የመንፈሳዊ አቢይ ክንውን ነው።” በመሆኑም ይመስላል በየትኛውም የሀገራችን ክፍልና አቅጣጫ ቢኬድ (ሁሉም እንደየ እምነትና ባህሉ) “ሀገራችንን ሰላም አድርግልን” የጋራ ሃሳብ፣ የጋራ አጀንዳ፣ የጋራ ትርክት፣ የጋራ የፀሎትና ምርቃት ሆኖ የሚገኘው።

ሀገራችንን ሰላም አድርግልን!!! ዝቅ ብለን የምንጠቅሰው ጥናት እንደሚነግረን ከሆነ፣ “በዋቄፈና ከማንም በላይ አያና/ውቃቢ ከሚሰጠው ምርቃት በላይ ከፍ የሚል የለም። በአያና/ ውቃቢ የሚሰጥ ምርቃት ያለው ደረጃ ከፍ የሚለው ምርቃቱን የሚሰጠው በሰዎች ላይ መንፈስ ሆኖ አድሮ ስለሆነ፤ ወይም ስለማይታይ፤ ወይም ደግሞ ለአምላክ ያለው ቅርበት ብቻ ሳይሆን አያናው/ውቃቢው የመረቀውን ምርቃት ለአማኙ ሁሉ ስለሚያደርግ ጭምር ነው። አያና/ውቃቢ የመረቀውን ምርቃት አማኞች እንደቃልኪዳንም እንዲፈፀም በእምነት” ይጠበቃል። እዚህ ላይ “• • • ለአማኙ ሁሉ • • •“ የሚለውን አስምረንበት፤ “ሀገራችንን ሰላም አድርግልን” የሚለውን አክለንበት፤ ምርቃት የጋራ፣ ለጋራ፣ በጋራ • • • ያልነውን በልቦናችን ይዘን እንደገና “ሀገራችንን ሰላም አድርግልን” ማለት የጋራ ቋንቋችን ሊሆን ይገባል። “ምርቃት/ቡራኬ የትኛውም እምነት የወል/የጋራ የሆነ ለመለኮታዊ ኃይል የሚቀርብ የጸሎት፣ ትምህርት፣ መርሀ ግብር ክፍል ወይም በራሱ የመንፈሳዊነት አቢይ ክንውን ነው።“የሚለው እንዳለ ሆኖ፤ ምርቃት ከቸር ሰብእናዎች፣ ቅን ልቦች የሚመነጭ የመልካም ምኞት መግለጫ ነው። ሁሉም እንደየሃይማኖትና እምነቱ ፈጣሪውን ከሚማፀንበት መካከል አንዱ ምርቃት ነው። በመሆኑም፣ “ሀገራችንን ሰላም አድርግልን” ባዩ ከአምላኩ ጋር ንግግር ሲያደርግ ይሰማል፤ ቆሞ ሲማፀን ይታያል። “አድርግልን” የተባለው እሱ፣ የላይኛው ነውና ከእሱው ጋር ንግግር ይደረጋል። ተስፋም ይጣልበታል።

በኢአማኒያን ዘንድ ትርጉም የሌለው፤ በአማኒያን ዘንድ ደግሞ ከፍተኛ ትርጉም ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ክብርና ስፍራ ያለው የስነቃል ሀብት ቢኖር ምርቃት ነው። የሰው ልጅ የሚያምነው አምላክ ካለ ምርቃት አለ። የአማኞችን ስነልቦና ከመንፈሳዊነት ጋር የሚያቀራርብ፣ የሚያስተሳስር፣ የሚያጋምድ ማህበራዊ እሴት ቢኖር እሱ ምርቃት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። በጅጋ “በጥናቴ ደረስኩበት” እንዳለው፣ ምርቃት በማህበር (ቢያንስ ሁለት መራቂ እና ተመራቂ/ ባራኪ እና ተባራኪ) ተሳታፊ ያሉት መንፈሳዊ ክንውን ነው። በባህሪው ምርቃት የጋራ በሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ እና ምኞቱ፣ ተስፋው እና ህልሙ እውን ይሆን ዘንድ የሚታወጅበት እና በይሁንታ እና በአሜንታ የሚቋጭ መልካም ምኞቶችን (aspiration/ manifestation/ wish of wonders and miracles) እንደሚያሳካ የምናምንበት መንፈሳዊ ሀብት ነው።

ምርቃት/ቡራኬ የበለጠ በመንፈሳዊ አገልግሎት የመለኮታዊ ስልጣን ያለው አካል (spiritual hi[1]erarchy) ሊያስተላልፈው፤ እንዲሁም ሊመራው የሚገባውና አማኙ ማህበር ደግሞ በመቀበል እና በመሳተፍ ምሉዕ የሚያደርገው ቃላዊ (በጽሑፍ ሳይሆን በጥልቅ መንፈሳዊነት ከልቦና የሚመነጭ ወይም በልምምድ የሚነገር) መለኮታዊ ኃይልን የምንለምንበት መሳሪያ ነው። (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ 2008 ዓ•ም) ምርቀት በማህበራዊ አውድ ብቻም አይደለም፣ በኪነጥበቡም በሽበሽ ነው።

ፀሀዬ ዮሀንስ (ስለ ኢትዮጵያ)

ዘርተን እንቃምባት፣

ወልደን እንሳምባት፤ አምላኬ ሆይ፣ ልጆችህ ነንና፣ አውጣን ከፈተና።

በማለት ለአምላኩ የሚያደርገው ተማፅኖ ከአባቶች እና እናቶች “ሀገራችንን ሰላም አድርግልን/ያድርግልን” ጋር መሳ እንጂ የተለየ አይደለም። ድምፃዊው በዚሁ ዜማው ″ሰላም አይለየን / ፍቅር አይለየን″ ሲል ለ“ሀገራችንን ሰላም አድርግልን” የተለየ ነገር እየተናገረ ሳይሆን ያንኑ የአበውን “ሀገራችንን ሰላም አድርግልን” ምርቃት እያጠናከረ ስለ መሆኑ አስረጂ መጥቀስ ሳያስፈልግ ሁሉችንም እኩል እምንረዳው ጉዳይ ነው። ወደ ጦርጦራዎቹ ጉሬጌዎች ዘንድ ጎራ ብሎ “ኬር ይሁን”ን ሳይሰማና ሳያደንቅ የሚመጣ አለ ሲባል አልተሰማምና የለም። ወደ ቦረና ሄዶ በሁሉ ነገራቸው አንጀቱ ያልተላወሰ፤ እዛው “ቅር ቅር” ያላለው ካለ እሱ ላገሩ እንግዳ፤ ለሰው …ካልሆነ በስተቀር ሌላ ሊሆን አይችልም።

ወደ ሀላባ ቆሊቱ ሄድ ብሎ ሴራን የተመለከተ “ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን” የምርቃቱ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነገር መክፈቻና መዝጊያ ሆኖ ያገኘዋል። በሌሎች አካባቢዎችም እንደዛው። እነዚህም ሆኑ ከላይ እያልን የመጣናቸው “ምርቃት” ተኮር ጉዳዮች ሰው ከአምላኩ ጋር፣ ሰው ከማህበረሰቡ ጋር፣ ሰው እትብቱ ከተቀበረችበት ሀገር ጋር፣ ሰው ከሰው ጋር፤ ሰው ከአካባቢው ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝትና ትስስር ያመለክታልና ምርቃት የዋዛ አይደለም ሲባል መሰረቱ ጥንታዊነቱ እንጂ ሌላ አይደለም። ምርቃት ወደ አምላክ በልመና የቀረቡ ሰዎች የሚለግሱት ፈዋሽ ሃሳብ ነው። ልክ እንደ “ሀገራችንን ሠላም አድርግልን/ያድርግልን” ሁሉ “ወልዶ መሳም፤ ዘርቶ መቃም፤ በሀገር እንደ ሆነ ሁሉ፤ ሰላም አለመሆንም ሆነ ዘርቶ አለመቃም ወይም ወልዶ አለመሳም ምድባቸው ከእርግማን ነውና፤ ምንግዜም፣ እንደ አባት እናቶቻችን ሁሉ፣ “ሀገራችንን ሰላም አድርግልን” ማለቱ የጋራ ቋንቋችን ሊሆን ይገባል። ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን!!! አሜን!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You