በፈተና ውስጥ ብልጽግናዋን እያረጋገጠች ያለችው ኢትዮጵያ!

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችና በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ስንሄድ ያልተነኩ እምቅ ሀብቶች በስፋት የሚገኙባት ሀገር ናት። እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ ከታወቁ እና ጥቅም ላይ መዋል ከቻሉም የኢትዮጵያ የብልጽግና መሠረትና የሕዝቦቿም የኑሮ መሠረቶች ይሆናሉ።ሆኖም ዕድገቷን የማይመኙ አካላት ይህንን የተፈጥሮ ጸጋ እንዳትጠቀም እና ብልጽግናዋን እንዳታረጋግጥ በርካታ ሴራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

ሕዝቡ የመከባበርና የመቻቻል ዕሴቱን እንዲያጣ፣ በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈልና በማናቆር ግጭት እንዲነግስና በሂደትም የተዳከመች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር በርካታ አካላት ያለመታከት ሠርተዋል።በዚህም የኢትዮጵያን የሰላም ዕሴት ደብዝዞ ነፍጥ ማንሳት እንደፋሽን ሊቆጠር በቅቷል፡፡

ይህንን አስተሳሰብ ከመሰረቱ ለመንቀልና ኢትዮጵያውያን ወደ ቀድሞው ዕሴቶቻቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር የሚል መርህን በማንገብ በመላ ሀገሪቱ ሰላምን የማስፈን እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል።በእስር ላይ የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ታግደው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን በይቅርታ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ፤ የታጠቁ አካላት ነፍጣቸውን እንዲያስቀምጡና በሀገራቸው ልማት ላይ በነጻነት እንዲሳተፉ ጥሪ በማድረግ ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

ሆኖም የውጭ ኃይላት ተላላኪ የሆኑ ቡድኖች አሁንም የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት የሚያናጉ ተግባራት ሲፈጽሙ ተስተውለዋል።በነጻ አውጪ ስም ብሔር ከብሔር ፣ ሃይማኖት ከሃይማኖት መቃቃር ውስጥ የሚከቱ ተግባራትን በመፈጸም አብሮ የኖረውን እሴት ለመናድ ሌት ተቀን ሲጥሩ እየታዩ ነው፡፡

በዚህ ሁሉ ጥፋት ውስጥ እያሉም ቢሆን መንግሥት የሰላም ጥሪ ከማቅረብ የቦዘነበት ወቅት የለም።በተለያዩ አጋጣሚዎች እነዚህ ኃይላት ወደ ሰላም እንዲመለሱና ሀገራቸውን በጋራ እንዲያለሙ ጥሪ በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡

ከሰሞኑም ታላቁ የዓባይ ድልድይ በተመረቀበት ወቅት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ነፍጥ ያነገቡ ቡድኖች ከአጥፊ ድርጊታቸው ተቆጥበው የተጀመረውን ልማት በጋራ እንዲያስቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

መንግሥት በሀገሪቱ ሰላም ለማስፈን ከሚያደርጋቸው ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ጎን ለጎን የሀገሪቱን መጻኢ ዕድል የሚወስኑ በርካታ ልማቶችንም በማከናወን ላይ ይገኛል።ለውጡ ዕውን ከሆነበት 2010 ጀምሮ ሀገራዊ ሀብቶችን በማወቅ፣ በመለየት፣ በማልማትና መጠቀም ረገድ እመርታዊ ለውጦች ታይተዋል፡፡

በገበታ ለሸገር የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ የአንድነት፣ የወንድማማችት እና የእንጦጦ ፓርኮች ለአዲስ አበባ ድምቀት ሆነዋታል።ለወትሮው በቱሪስት መተላለፊያነት የምትታወቀው አዲስ አበባ የቱሪስቶች መቆያ የመሆን ዕድልም አግኝታለች።በገበታ ለሀገር ፕሮጀክትም የጎርጎራ፤የኮይሻ እና የወንጪ የቱሪስት መዳረሻዎች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገት ተጨማሪ ዕድሎችን ፈጥረዋል።በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችም ይሄው ሰናይ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ሰሞኑን ደግሞ አዲስ አበባ በአዳዲስ ፕሮጀክቶች ብቅ ብላለች።አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ መዲና፣ የአፍሪካ ዋና ከተማ፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያ እንደ መሆኗ ይህን የሚመጥን ልማት እየተከወነላት ይገኛል።በአዲስ አበባ የሚከናወነው የኮሪደር ልማት አዲስ አበባ ውብና ጽዱ ከተማ እንድትሆን ከማድረጉ ባሻገር አህጉርና ዓለም አቀፍ ከተማነቷንም የሚያረጋግጥላት ነው፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም በዋናነት አዲስ አበባ ላይ ተጀምሮ በቀጣይም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እየሰፋ የሚሄድ የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ይፋ ሆኖ ሕዝቡ በነቂስ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።ግንቦት 4 ቀን 2016 በተካሄደው ንቅናቄም በአንድ ጀንበር ብቻ ከ154 ሚሊዮን በላይ ተሰብስቦ አዲስ አበባን ውብና ጽዱ የማድረጉ እንቅስቃሴ ወደ ተግባር ተሸጋግሯል፡፡

ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ ሆና እያስመዘገበቻቸው ያሉ ተግባራት ከዛሬ አልፈው ለነገው ትውልድ መድህን የሚሆኑ በመሆናቸው ሕዝቡ ጥቂቶች በሚፈጥሩት ውዥንብር ሳይደናገር የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች ማስቀጠሉ ለነገ ይደር የማይባል ሥራ መሆኑን መገንዘብ ይገባል!

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You