ባለሥልጣኑ ለአቅመ ደካሞች ያስገነባውን ቤት አስረከበ

አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ስር የሚገኘው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት፣ በወረዳ 12 ላይ የሦስት አቅመ ደካማ አባወራ ቤቶችን አፍርሶ በመሥራት ለባለቤቶቹ ቁልፍ አስረክቧል፡፡

እነዚህ ቤቶችን ሠርቶ ለማስረከብ አንድ ወር ተኩል ጊዜ እንዲሁም አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን፤ በጉልበት የሚገመት ደግሞ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደፈጀ የክፍለ ከተማው ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ ኢትቻ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዳሉት፤ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣኑ ከአባላቶቹ ጋር በመተባበር የአቅመ ደካማ ቤቶችን እያፈረሰ መሥራቱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከዚህ ቀደም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እና በየካ ክፍለ ከተማ የአቅመ ደካማ ቤቶችን አስገንብቶ አስረክቧል፡፡ በቀጣይም ይህን መሰል ሰው ተኮር ተግባራትን አቅዶ ያከናውናል፡፡

የቁልፍ ርክክብ ከተደረገላቸው አቅመ ደካሞች መካከል ሰባት ልጆች ወልደው ሰባቱንም በሞት ያጡትና ከልጅ ልጃቸው ጋር አብረው እየኖሩ የሚገኙት ወይዘሮ እሸቴ ውሪሳ እንዳሉት፤ ከሀዘኑ በላይ ጧሪ የሚሆን ልጅ ስለሌለኝ ቤቱ በላዬ ላይ ፈርሶ በዝናብና በብርድ ብዙ ችግር አሳልፌአለሁ፡፡ አሁን ቤቱ በጥሩ ሁኔታ ተገንብቶ ስለተሰጠኝ መንግሥትን እና ለዚህ ግንባታ ወጪ ያወጡትን ሁሉ አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡

በቁልፍ ርክክብ ሥነሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር የበላይ ኃላፊዎች፣ የክፍለ ከተማው የበላይ ኃላፊዎች፣ የወረዳ 12 አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የወረዳው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You