
ኢናይ አቢዳ የዕደ ጥበብ ኮሌጅ የተመሰረተው በ2007 ዓ.ም ነው፡፡ የሀረሪ ባህላዊ የእድ ጥበብ ሙያዎች በሆኑት ባህላዊ ቆብ፣ አለላ ስፌት፣ሐረሪ ባህላዊ ቤት ግንባታ፣ በቆዳ ስራ፣ በእንጨት ስራ፣ በሽመና ስራ፣ በጌጣጌጥ፣ በጥልፍ፣ በልብስ ቅድ እና በሴንጀር በድምሩ በ10 የሙያ አይነቶች ስልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት አንድ ሺህ 729 ተማሪዎችን አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የኢናያቢዳ የዕደ ጥበብ ኮሌጅ ዋነኛ ተግባር ባህልን ማሳደግና የስራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡ አንደኛ ማህበረሰቡ ባህላዊ ልብሶቹን እና ጌጣጌጦቹን ለትውልድ በማስተላለፍ ማንነቱን እንዲጠብቅ ያደርጋል፤ በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ሰልጥኖ ስራ በመጀመር የገቢ ምንጭ የሚያገኝበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ በአጭሩ ባህልን ወደ ዳቦነት የሚቀይር ማዕከል ነው ያሉት፡፡
በማዕከሉ የሚመረቱት የዕደ ጥበብ ውጤቶች ለቱሪስቶች ከፍ ባለ ዋጋ ለሽያጭ እንደሚቀርቡ የሚናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተጨማሪም በውጭ ሀገሮች ለሚኖሩ የሀረሪ ተወላጆች ኤክስፖርት እንደሚደረጉ ይገልጻሉ፡፡ በተለይም የሐረሪ የሙሽሮች የባህል ልብስ በብዛት በውጭ ሀገራት በሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች እንደሚፈለጉ የሚጠቁሙት አቶ ኦርዲን፤ የተለያዩ ባህላዊ ዝግጅቶች በሚኖሩበት ወቅት ጥያቄዎች እየቀረቡልን የባህል አልባሳቱን እንልካለን ይላሉ፡፡
ከሀረሪ ባህላዊ የዕደ ጥበብ ሙያዎች ሁለቱ በዓለም አቀፍ ምድብ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የንግድ ምልክት ሆነው ተመዝግበው ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የንግድ ምልክት ምዝገባ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውንም ይገልጻሉ፡፡
የሀረሪ ክልል ባህልና ቱሪዝም ዳይሬክተር ተውለድ አብዱሽ ኮሌጁ የሚገኝበት ህንጻ በራሱ ታሪክ ያለው ቅርስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ህንጻው በቅድሚያ የዕቴጌ ጣይቱ ጫጉላ ቤት እንደነበርና በተለያዩ ዘመናት የተለያየ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱንም ይገልጻሉ፡፡ ቀጥሎ የፈረንሳይና የእንግሊዝ ካውንስል ሆኖ ያገለገለ ሲሆን፤ በኋላም ሆቴል፣ ቀጥሎ ደግሞ የእቴጌ መነን ማረፊያ የነበረ ነው፡፡ በደርግ ዘመን ተወርሶ የከተማው ነዋሪዎች የሚኖሩበት የቀበሌ ቤት ሆኖ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል፡፡ በመጨረሻም በ2007 ዓ.ም. የክልሉ መንግሥት የህንጻውን ታሪካዊነት ከግምት በማስገባት የኢናይ አቢዳ ኮሌጅ ተብሎ እንዲጠራና ስልጠና እንዲሰጥበት ተወስኖ በስፔን ኤምባሲ በተገኘ ድጋፍ ጥገናው መከናወኑን ያወሳሉ፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚገልጹት፤ ኮሌጁ ስልጠናዎችን የሚሰጠው በሁለት መንገድ ነው፡፡ የመጀመሪያው ለመደበኛ ተማሪዎች የሚሰጥ መደበኛ ስልጠና ሲሆን፤ ሁለተኛው በክረምት ትምህርት በሚዘጋበት ወቅት ለተማሪዎች የሚሰጥ ስልጠና ነው፡፡ የእደ ጥበብ ማዕከሉ ከመከፈቱ በፊት የዕደ ጥበብ ሙያዎችን ማስተማር የእናቶች ተግባር ነበር፡፡ አሁን ማዕከሉ ኃላፊነቱን ተጋርቷል፡፡ ታዳጊዎች የእረፍተ ጊዜያቸውን ሌላ ቦታ ከማሳለፍ ተቆጥበው በቤት ውስጥ የቀሰሙትን ትምህርት የሚያዳብሩበት ማዕከል አግኝተዋል፡፡
የሀረሪ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ኃላፊው ዘከሪያ አብዱላዚዝ ማዕከሉ የሚሰጣቸው የሙያ ዘርፎች ከፌዴራል በመጡ ባለሙያዎች ደረጃ (ስታንዳርድ) ተዘጋጅቶላቸው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲሰጡ የሚያስችል ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም አስሩ የስልጠና ዘርፎች ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አራት ድረስ ደረጃ ወጥቶላቸዋል ይላሉ፡፡
የሀገር በቀል እውቀትን የቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎች በሚሰጡበት ደረጃ የሚሰጥ ኮሌጅ ባለቤት በመሆን ሐረሪ ክልል በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው የሚሉት ኃላፊው፤ በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ መንግሥት ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል በጀት ለዕደ ጥበብ ኮሌጁ መድቦ፣ የትምህርት አሰጣጡ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲሰጥና ወጥ በሆነ መንገድ በስፋት ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ የሙያ ደረጃ ዝግጅት እንዲደረግ፤ ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾለት በማስተማሪያ መጽሐፍ እንዲታገዝ እና ለመማር ማስተማር ሂደት የራሱ ቁሳቁሶች እንዲዘጋጁለት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ኮሌጁ በአስሩም የሀረሪ የዕደ ጥበብ ሙያዎች የትምህርት ቁሳቁሶችን አሟልቶ ስልጠናወን የሚሰጠው በነጻ መሆኑን የሚያነሱት የኢናይ አቢዳ የዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲን ወይዘሮ ፍርዶሳ ቶፊቅ፤ ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት በአስር መምህራን እና ሦስት ረዳት በመምህራን 97 ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡
ዲኗ እንደሚገልጹት፤ ኮሌጁ የሐረሪ ባህላዊ ዕደ ጥበብ ውጤቶች ሳይበረዙ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፉ እና የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ የሚያደርገው ጥረት በሐረሪ ብቻ ሳይገደብ ከክልል ባህልና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ከሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና ትግራይ የመጡ ሰልጣኖችንም አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡
ኮሌጁ በሀገር በቀል እውቀት በዲፕሎማና ዲግሪ ደረጃ ስልጠና መስጠት ወደሚችልበት ደረጃ በማደጉ ትልቅ ደስታ ተሰምቶናል የሚሉት ወይዘሮ ፍርዶስ፤ ለሽግግሩ የሚያግዝ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ በቅርቡም ጀጎል ውስጥ ባህላዊ ቤት አድሰን በማስመረቅ ሌላ ቅርንጫፍ ከፍተናል፡፡ አሁን በኮሌጁ ስልጠና እየሰጡ የሚገኙት እናቶች እውቀቱን በባህላዊ መንገድ የወረሱ ስለሆኑ ጎን ለጎን በኮሌጅ ደረጃ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ሰዎች ለማሰልጠን እየሰራን ነው ይላሉ፡፡
ኮሌጁ ባህላዊ የዕደ ጥበብ ውጤቶች የሚሰሩበትና ለጎብኚዎች የሚሸጡበት ማዕከል መሆኑን የጠቆሙት ዲኗ፤ ጎብኚዎች ባህላዊ የዕደጥበብ ውጤቶችን በመስራት ሂደት ውስጥ በተግባር እንደሚሳተፉና በተማሪዎች የተሰሩ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን በርካሽ ዋጋ የመሸመት ዕድል እንደሚያገኙ ያመላክታሉ፡፡
የስርዓተ ትምህርት ቀረጻው ሲጠናቀቅ፣ ከሀረር ውጭ የትም ቦታ ስልጠናዎችን ለመስጠት ስለሚያስችል የሀረሪን ባህል ከማሳደግ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠቁማሉ፡፡
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም