የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር የአሜሪካን የጦር መርከብ አጠቃን አሉ

የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር የአሜሪካን የጦር መርከብ ማጥቃታቸውን ገለጹ። የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር የአሜሪካን የጦር መርከብ እና “ደስቲኒ” የተሰኘች እቃ ጫኝ መርከብን ኢላማ ማድረጋቸውን በትናንትናው እለት ገልጸዋል።

ታጣቂዎቹ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ጥቃት የሚያደርሱት ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። የሀውቲ ጦር ቃል አቀባይ ያህያ ሰርኤ በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫው ሀውቲዎች “ማይሱን” የተባለችውን የአሜሪካ ዲስትሮየር በቀይ ባህር ላይ ስትጓዝ “በትክክለኛው የናቫል ሚሳይል” አጥቅተዋል።

ሀውቲዎች እቃ ጫን መርከቧን ያጠቁት በፈረንጆቹ ባለፈው ሚያዝያ 20 ወደ እስራኤሉ ኢላት ወደብ በማምራቷ ምክንያት መሆኑን ሰርኤ አክሎ ገልጿል። ሰርኤ በሁለቱ መርከቦች ላይ ጥቃት የደረሰው መቼ እንደሆነ በትክክል አልገለጸም። ሮይተርስ ሁለት መርከቦች መትተናል የሚለውን የሀውቲዎች መግለጫ ማረጋገጥ እንደማይችል ጠቅሷል።

ለወራት የቀጠለው ሀውቲዎች በቀይ ባህር የሚያደርሱት ጥቃት ዓለምአቀፉ የንግድ መርከብ እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎል፣ የመርከብ ኩባንያዎች በጣም ውድ የሆነውን በደቡብ አፍሪካ ዙሪያ ያለውን መስመር ለመጠቀም እንዲገደዱ እና የሀማስ እና እስራኤል ጦርነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ይስፋፋል የሚል ፍርሃት እንዲነግስ አድርጓል።

አሜሪካ እና እንግሊዝ የመን ግዛት ውስጥ በሚገኙ የሀውቲ ይዞታዎች ላይ ጥቃት በማድረስ ለመርከቦች ጥቃት ምላሽ እየሰጡ ናቸው። የሀውቲ ታጣቂዎች የጋዛ ተኩስ አቁም እስከሚደረግ እና በቂ የሰብዓዊ ርዳታ መግባቱ እስከሚረጋገጥ ድረስ፣ በተለይ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ባላቸው መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት እንደሚቀጥሉበት ግልጽ አድርገዋል ሲል አል ዐይን ዘግቧል። ሀውቲውች ባደረሱት ጥቃት አንድ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ከዚህ በፊት መስጠሟም ይታወሳል።

አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You