ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ለማህበራዊ መሠረቱ ወይም ለደጋፊው አልያም ለተከታዩ የሚቀርጸው መልዕክትና ለሀገርና ለሁሉም ዜጋ የሚያስተላልፈው መልዕክት መለያየት ያለና የነበረ ወደፊትም የሚኖር ነው። ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መልዕክት የሚቀርጽበት አግባብ እና በምርጫ አሸንፎ ወደ ስልጣን ሲመጣ የመልዕክት አቀራረጹ ከፍ ሲልም የተግባቦት ስትራቴጂው የተለያየ ነው።
የመጀመሪያው ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው መልዕክቱን የሚቀርጸው ለማህበራዊ መሠረቱ ነው። የሀገር መሪ ሲሆን ግን መሪነቱ ለመረጡትም ሆነ ላልመረጡት እንዲሁም በምርጫ ላልተሳተፉት ስለሆነ መልዕክቱ ይሄን ታሳቢ ያደረገ መሆን ይጠበቅበታል። እንዲሁም ለደጋፊ የሚተላለፍ መልዕክት የሚቀረጸው ከፓርቲው ፕሮግራም አኳያ ነው። ፓርቲው ስልጣን ከያዘ በኋላ ግን ብሔራዊ ጥቅምንና ፖሊሲን ታሳቢ አድርጎ ነው የሚቀረጸው።
በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚከተሉ ሀገራት ፖለቲካው የሚመራዊ እንዲህ ባለ ኃላፊነት በሚሰማው መርህ ነው። የዴሞክራትም ሆነ የሪፐብሊካን፣የሌበርም ሆነ የኮንሰርቫቲቭ ወይም የቶሪስ፣ወዘተረፈ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሰራር እንዲህ ነው።የማህበራዊ መሠረትን ወይም የደጋፊን ልብ ለማሞቅ ልወደድ ባይ ወይም ፓፑሊስት ለመሆን መልዕክት የሚቀረጽ ከሆነ፤ጊዜያዊና ታክቲካዊ ጥቅም ያስገኝ ይሆናል እንጂ ውሎ አድሮ ለፓርቲውም ሆነ ለደጋፊው የሚያስከትለው ዳፋ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ነው።
“ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ታሪክንና ዓሉታዊ ትርክትን ለይቶ መሥራት ያስፈልጋል”ሲሉ ባህሩ ዘውዴ (ኢሜሬትስ ፕ/ር) የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ ከአዲስ ዘመኑ ልጃዓለም ፍቅሬ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ አሳሰቡ። ያለፉ ታሪኮችን በተገቢው መንገድ በማጤን ከዓሉታዊ ትርክቶች ለይቶ ማየት ያስፈልጋል። በታሪክ ከትናንት በመማር ዛሬን ማሻገር ተገቢ ነው። የታሪክ ባለሙያዎችም ትክክለኛውን ታሪክ ለሕዝቡ ከማድረስ አኳያ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተለያዩ ልዩነት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ከስሩ በማጥራት ለምክክር እንዲቀርቡ ማስቻል ይኖርበታል።
እንደ ፕሮፌሰር ባህሩ ገለጻ፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ዓላማ ልዩነቶችን በመፍታት ወደ አንድ ሀገራዊ እሳቤ ማምጣት ነው። ከዚህ አኳያ ታሪክን በአግባቡ መገንዘብ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ‹‹ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ›› በሚል ርዕስ ላይ የተካሄደ የጥናት ሰነድ ለምክክር ኮሚሽኑ ማቅረቡን ጠቁመዋል። ሰነዱ የታሪክ ተመራማሪዎች የደረሱበት ድምዳሜ የሚዳስስ ነው። ይህም ትክክለኛውን ታሪክ ለመለየት የሚያግዝ ይሆናል። ተጋንነው ከሚወሩት ውስጥ አብዛኞቹ ከእውነት የራቁ ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚከፋፍለው ይልቅ በአብዛኛው አንድ የሚያደርግ ታሪክ እንዳለው አስረድተዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በቅርበት እየሠራ ሲሆን፤የምክክር ኮሚሽኑ በየጊዜው የሚያማክር አማካሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ማህበሩም የተዛቡ የታሪክ አረዳዶች ለመቀልበስ እየሠራ ነው። ኢሚሬትስ ፕሮፌሰር ባህሩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመፈራረጅ ይልቅ ትክክለኛውን ታሪክ መገንዘብ ይኖርበታል። እንዲሁም ከተዛባ ትርክት ሊወጣ ይገባዋል። ሀገሪቱ አሁን ላይ ላለችበት ውስብስብ ችግር መንስኤው ታሪክን በአግባቡ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው።
የታሪክና የትርክት ነገር ከተነሳ አይቀር ትንሽ ልበል። በአአዩ የተዘጋጀ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፦ “ ተረከ ስለአለፈ ነገር ዘርዝሮ ተናገረ ፣ አወራ ፣ አወጋ ፣ አተተ ማለት ነው ይለናል ። “ትርክት ደግሞ ስለአለፈ ነገር ዘርዝሮ የመናገርና የማውራት ሒደት ነው ። መንግሥታት ፣ ገዢዎችና የፖለቲካ ቡድኖች ቅቡልነትን ለማግኘትና ከተነሱበት አላማ አንጻር የዜጎችን ወይም የተከታዮቻቸውን እምነት፣ አመለካከትና እይታ ለመቃኘት ታሪኮችን ፣ ማስረጃዎችንና ገለጻዎችን አደራጅቶ ገዥ ሃሳብ አንጥሮ የመለየትና የማኸዘብ ስልት ነው።
በእርግጥ ትርክት የጋራ ማንነትን ለማነጽ ያግዛል። በተለያዩ ማህበረሰቦች ዘንድ አንድነትን ለመፍጠርና የጋራ ተግባር ለመተለም ፤ የጋራ ታሪካዊ ፣ ባህላዊና ማህበራዊ አላባውያንን በመጠቀም ብሔራዊ ማንነት ለመፍጠር ያስችላል። ከዚህ ባሻገር ትርክት ብሔራዊ እሴቶችንና ሕልሞችን ለመቅረጽ ፤ ማህበራዊ ስምምነት ለመፍጠር ፣ ታሪካዊ ትውስታ ለመጫር ፣ ሕዝብን ለአንድ አላማ ለማነሳሳት ንቅናቄ ለመፍጠርና ዓለም አቀፍ ገጽታ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የማይተካ ሚና አለው።
በነገራችን ላይ ትርክት አዎንታዊና አሉታዊ ሊሆን ይችላል። ሀገርን ለመገንባት የሚውል አዎንታዊ ትርክት እንዳለ ሁሉ ሀገርን ለማፍረስ የሚውል አሉታዊ ትርክት እንዳለ በዘርፉ የተጻፉ ድርሳናት ያትታል። አዎንታዊ ወይም አካታች ትርክት አካታችነትን ፣ ብዝሀኅነትንና ማህበራዊ ውህደት ይሰብካል ። አሉታዊ ትርክት በዜጎች መካከል ልዩነትን ፣ ጥላቻን ፣ አለመተማመንና መጠራጠርን የሚጎነቁል ከመሆኑ ባሻገር ሀገርን እስከማፍረስ ሊደርስ ይችላል። የሀገራችንን መልክዓና ሰማይ የሞላው ይህ አሉታዊ ትርክት ነው። ይህ አደገኛ ትርክት ሥራ ላይ እያለ አዲስ “ታላቅ ትርክት” ማንበር ያዳግታል። ለመሆኑ የዚህ ትርክት መነሻ ከወዴት ነው።
በተማሪዎች የ1960ዎች እንቅስቃሴ ከእነ ግርማቸው ለማ ፣ መለስ ተክሌ (የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ስሙን የወረሱት ) ፣ ሰለሞን ዋዳ ፣ ጥላሁን ግዛው ይልቅ ዛሬ ድረስ በበጎም ፣ በክፉም ስሙ ከፍ ብሎ የሚወሳው የደሴው ዋለልኝ መኮንን ነው ። ከእነ ሌኒን ማንፌስቶ እንዳለ ገልብጦ/ ኮርጆ / ማታገያውን ከመደብ ጭቆና ወደ ጠባቡ የብሔር ጭቆና በማውረዱ ተደጋግሞ ቢወቀስም፤ አንዳንዶቹ ዋለልኝ የተማሪዎች ማህበር መሪዎች ያሳለፉትን ውሳኔ አነባብ ጻፈ እንጂ የብሔር ጥያቄን ቀድሞም ሆነ ለብቻው አላነሳውም በማለት ጥያቄው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የወለደው ስለሆነ ከዋለልኝ ጫንቃ ውረዱ የሚሉ ወገኖች አሉ።
ያም ሆነ ይህ በፈጠራ ትርክትና በግልብ ትንተና መታገያና ማታገያ ሆኖ የመጣው የብሔር ጥያቄ ሀገራችን ዛሬ ድረስ ለምትገኝበት ምስቅልቅል እና አጣብቂኝ መግፍኤ ከመሆኑ ባሻጋር ፤ ሀገር ፣ ሕዝብና የባህር በር አሳጥቶናል ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ልሒቃኑን በሁለት ጎራ ከፍሎ እያባላና እያጨቃጨቀ ይገኛል። በሀገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው ጭቆና የመደብ ነው አይደለም የብሔር ጭቆና ነው በሚሉ ሁለት የማይታረቁ ቅራኔዎች ተጠምዷል። የብሔር ጭቆና በተጠየቃዊነት በምክንያታዊነት የሚተነተን ሳይሆን በማንነት በስሜት የሚቀነቀን የሚራገብ መሆኑ ልዩነቱን የማጥበብ ሂደቱን አዳጋች አድርጎታል።
እዚህ ላይ በብሔርተኞችና እና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በሚያራምዱ ወገኖች መካከል ያለውን ልዩነት በአብነት ማንሳት ይቻላል። ሆኖም የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለትህነግ ፣ ለኦነግና ለሌሎች የብሔር ድርጅቶች መፈጠር እርሾ ሆኖ ማገልገሉ አይካድም። የትርክታቸው መነሻም ሆኖ አገልግሏል። የጋራ ሀገር ፣ ታሪክ፣ ትርክትና ጀግና እንዳይኖረን አድርጓል። ጥላቻ፣ ልዩነትና ጎሰኝነት እንዲጎነቁል ለም አፈር ሁኗል።
እነ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴና ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ነፍሳቸውን ይማርና ደጋግመው ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ መሰረት ታሪካችንን መፈተሽ እንደ ገና መበየን ይጠይቃል። ይህን ስል እንደ በጀት ታሪካችን በቀመር ይደልደል ማለቴ እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ከዚህ ጎን ለጎን ፍርጥርጥ ፣ ግልጥልጥና እስከ ሀቁ መዳረሻ መነጋገር አለብን ። ሲለፈፍ በኖረው ትርክት ላይ ተነጋግረን እልባት መስጠት ያሻናል። ይሄን ሀሰተኛ ትርክት ህልው ያደረጉ መዋቅሮች ፣ ሥርዓቶችንና ተቋሞችን በማፍረስ መሠረቱን ማሳጣት ይገባል። ደጋግሜ እንደገለጽኩት ይሄን ሳናደርግ አዲስ ታላቅ ትርክት እውን ለማድረግ መሞከር ሌላ ተቃርኖ መቀስቀስ ነው ።
አሜን።ሻሎም።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም