ትጋትን ከኮሪደር ልማቱ

የከተማችን የኮሪደር ልማት ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። ልማቱ ለከተማችን ውበትና ጽዳት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ የከተማውን ነዋሪ ያገለለ ነው በሚል ቅሬታ የሚያነሱ ሰዎችም አልጠፉም። እርግጥ ነው! አዲስ አበባ እንደ ስሟ አበባ መሆን እንዳለባት ይታመናል። ዓለምአቀፍ ከተማ ከመሆንዋ አንፃር የሀገር መሪዎች፣ ሚኒስትሮች እና ዲፕሎማቶች የተለያዩ ስብሰባዎችን ሲደረጉባት ቆይቷል። ዓለምአቀፍ እና አህጉር አቀፍ ጉባዔዎችን እንደምታስተናገድ ከተማ በኮሪደር ልማቱ እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየሩ ባለፈ ከተማዋን ለተለያዩ ሀገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ተመራጭ እንድትሆን ያስችላታል።

መንግሥት አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ ለማድረግ የከተማዋን ውበት እና ገጽታ የማይመጥኑ በጭቃ የተሠሩ እና የፈራረሱ ቤቶችን በማንሳት እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ህንፃዎች ለመሥራት እየተጋ ነው። ይህም የከተማዋን ዓለም አቀፋዊነት በእጅጉ ያጎላዋል።

ከዚህ ቀደም በነበረ የአሠራር ችግር ሳቢያ በአዲስ አበባ በየመንደሩ ያለፕላን የተገነቡ ቤቶችን ማግኘት ብርቅ አይደለም። እነዚህ ቤቶች ከፕላን ውጭ በመገንባታቸው ሳያንስ በላያቸው ላይ ተለጣፊ ዛኒጋባ ቤቶችም ይጨመርባቸዋል። ይህም በመዲናዋ የሚገኙ በርካታ መንገዶች እንኳን ለተሽከርካሪ ይቅርና ጋሪ የማያሳልፉ ሆነው እናገኛቸዋለን። የእሳት አደጋ ቢያጋጥም የእሳት አደጋ መከላከያ መኪና እንደልብ ገብቶ እሳቱን ለማጥፋት፣ የቀይ መስቀል አምቡላንስ መኪናዎችም የተጎዱ ሰዎችን ወደ ሕክምና ቦታ በፍጥነት ለማድረስ ይቸገራሉ። አብዛኛዎቹ ቤቶች በእንጨትና በቆርቆሮ የተሠሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በቀላሉ ለእሳት እና መሰል አደጋዎች ሲጋለጡ ቆተዋል። እነዚህ የተጠቀሱት ዓይነት ውጥንቅጥ ቤቶችና ጠባብ መንገዶች ለዘመናት በመሐል ከተማዋ ሲታዩ የቆዩ ናቸው።

መዲናዋ በተወሰኑ ዓመታት ልዩነት የከተማ ማስተር ፕላን አውጥታ በማስተር ፕላን ለመመራት ጥረት ስታደርግ እንደነበር አስታውሳለሁ። ማስተር ፕላኑን በትክክል ተከታትለው የሚያስፈጽሙ የማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች ግን ግዴታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው ፕላን እያላት ፕላን የሌላት ከተማ ሆና ለመቆየት ተገዳለች ። ፕላን አልባ የሆች ከተማ ደግሞ ጽዳት አልባ፣ ውበት አልባ መሆኗ የማይቀር ነው ።

ማስተር ፕላን ከተሞች ሥርዓታቸውን ጠብቀው እንዲለሙ የሚረዳ ነው። በተጨማሪም ማስተር ፕላን መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች ፣ ንግድ ቦታዎች፣ ፋብሪካዎች ፣ መንገዶች እንዴት እና የት መገንባት እንዳለባቸው የሚያመላክት ቀስት ነው። ምክንያቱም የማስተር ፕላን የመሬት አጠቃቀምን እና ልማትን፣ የህንፃ አሠራርንና መዋቅርን እና የገበያ ቦታዎችንና ከፍተኛ መንገዶችንና ንዑስ መንገዶች አረንጓዴ ሥፍራዎችን ክፍት ቦታዎችንና የህንፃ ዓይነቶች በዝርዝር የሚይዝ ሰነድ ነውና። በተጨማሪም ማስተር ፕላን ዓላማዎች እና ግቦች ያሉት የአንድ ከተማ ቁልፍ የዲዛይን ሰነድ ሲሆን በውስጡም ከተሞች ከፕላኑ ውጭ አፈንግጠው ምንም ዓይነት ነገሮች እንዳይሠሩ የሚገድብ ነው።

ከዚህ ቀደም ለአዲስ አበባ በተለያየ ጊዜ ማስተር ፕላን እንደተዘጋጁላት መረጃዎች ያሳያሉ። ይሁን እንጂ የተዘጋጁት ማስተር ፕላኖች ከወረቀት (ከእቅድነት በዘለለ) መሬት ላይ በትክክል መውረድ ባለመቻላቸው ከተማዋ በጨረቃ ቤቶች አቧራ ተውጣ እንድትኖር ተፈርዶባት ቆይቷል።

በመዲናዋ ሕገወጥ የመሬት ወረራና የጨረቃ ቤቶች እየተበራከቱ ስለመሆናቸው በተደጋጋሚ በተለያዩ ዘገባዎች ሽፋን ሲሰጣቸው ተመልክተናል። በሚዲናዋ እንዴት የመሬት ወረራና የጨረቃ ቤቶች ሊበራከቱ ቻሉ? ከተባለ መልሱ “የመንግሥት ሹመኞች ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው” የሚል መልስ እናገኛለን።

እነዚህን እና መሰል ሲንከባበሉ የቆዩ ችግሮች የከተማዋን እድገት በማይመጥኑ ቤቶች እንድትሞላ አድርጓታል። ስለሆነም አሁን ላይ የተጀመረው እና እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ሲንከባበሉ በመጡ ችግሮች ሳቢያ በአቧራ እና በዳዋ የተዋጠችውን አዲስ አበባ ውበት የሚያጎናጽፍ ነው።

ከኮሪደር ልማቱ ጋር በከተማዋ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ሠራተኞችም በታታሪነትና በትጋት ሲሠሩ እያስተዋልን ነው። መንግሥትም የሠጠውንም ትኩረት ያሳያል። ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ እንደ ኤሊ እያዘገሙ ለሚገኙ ሌሎች መንግሥታዊ ግንባታዎችም ትኩረት ቢሠጠው መልካም ነው።

በመጨረሻም ልማትን የሚጠላ የለም። ልማቱ ሕዝብ ገፊ ሳይሆን አቃፊና ደጋፊ እንዲሆን የሚደረገው ጥረት ግን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ከዚሁ ጎን ለጎን በከተማው ዳርቻ የሚታዩ የጨረቃ ቤቶች፣ ሕገ ወጥ መሬት ወረራ (በመሠረቱ ሕገ ወጥ መሬት ወረራ የሚባል የለም ፤ መሬት ወረራ በራሱ ሕገወጥ ነው። ) መቆጣጠር ስንችል ነው። ከልማቱ አካባቢ የተነሱ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችም በጥቃቅንና አነስተኛ ሥራ ታቅፈው ሊሠሩ የሚችሉበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል።

ሜሮን ፈይሳ

 

አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You