የጦርነት ስብከቶች እና ፉከራዎች ጆሮ ይነፈጉ!

ሰላም ከፍ ያለ ሠብዓዊ እሴት ነው። ከዚህ የተነሳም በየዘመኑ ስለሰላም ብዙ ተብሏል ፤ ተዘምሯል ። በተለይም ዓለም በተለያዩ ምክንያቶች የከፉ ጦርነቶችን ለማስተናገድ መገደዷን ተከትሎ ጦርነቶች በሰው ልጅ ሁለንተናዊ ፍላጎቶች ላይ ከፈጠሩት አሉታዊ ተጽእኖ አኳያ ስለሰላም የሚደረጉ ዝማሬዎች ጎልተው መደመጥ ከጀመሩ ውለው አድረዋል።

በአሁናዊው ዓለም የሰው ልጅ ከደረሰበት የአስተሳሰብ ልእልና አንጻር ፤ ለግጭት እና ለጦርነት ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን በውይይት እና በድርድር በሰላማዊ መንገድ መፍታት የተለመደ እና የመሰልጠንም አንዱ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ህሊና እንዳለው ፍጡርም ከራስ አልፎ ለሌሎች ማሰብን የሚያመላክት ሰው የመሆን ምልክት ነው።

በተለይም ግጭቶች እና ጦርነቶች ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የጥፋት አድማሳቸው ባየለበት በዚህ ዘመን ፤ ጦርነትን በማውገዝ ፤ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ፤ በእጅጉ የሚበረታታ ነው። ለውጤታማነቱም የሚደረግ የትኛውም አይነት ድጋፍ ለሰው እና ለሠብዓዊነት ያለን ክብር አግዝፎ የሚያሳይም ነው ።

በተለይም እንደኛ ባሉ የታሪካቸው አብዛኛው ክፍል በግጭትና በጦርነት የተሞሉ ሀገራት ሕዝቦች ፤ ጦርነትን እና የጦርነት ድምጾችን አብዝተው ማውገዝ፤ ስለጦርነት ለሚደረጉ ስብከቶች እና ፉከራዎች ጆሮውን መንፈግ አለባቸው። ቀጣይ ሀገራዊ እጣፈንታቸውን ማስቀጠል የሚችሉት ይህን ማድረግ ሲችሉ ብቻ ነው።

እነዚህ ሀገራት በአንድም ይሁን በሌላ በቀደሙት ጌዜያት ከገቡባቸው ጦርነቶች ከደረሰባቸው ሁለንተናዊ ጥፋት /ጉዳት አኳያ ስለጦርነት አስከፊነት የማንንም ምስክርነት የሚሹ አይደሉም ፤ የጦርነት አስከፊ ገጽታ በሁለንተናዊ መልኩ በራሳቸው ደርሶ አይተውታል። ብዙ ወንድሞቻቸውን በሞት አጥተዋል፤ አካለ ጎዶሎ ሆነው አይተዋል ፤ ለዘመናት የደከሙበትን ሀብት እና ንብረት አጥተው ተረጅም ሆነዋል።

እንደ ሀገር ይሁን እንደ ግለሰብ በብዙ ተስፋ የጀመሩት የሕይወት ጉዞ ተሰናክሎ ለከፋ ረሃብ እና እርዛት ፤ ለስደትና ለተስፋ መቁረጥ ተዳርገዋል። ዛሬዎቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ነገዎቻቸውም ጦርነት የፈጠረው ጽልመት ተጭኗቸው ፤ አስፈሪና አስጨናቂ ሆነውባቸዋል። ብዙ ተስፋ አልባ ቀናቶችን በግራ መጋባት እንዲያሳልፉ ተገድደዋል።

ይህ እውነታ ለኛ ኢትዮጵያውያን እንግዳ አይደለም። በየዘመኑ ካሳለፍናቸው የጦርነት እና የግጭት ታሪኮች አኳያ የለመድነው ፤ እንግዳ ያልሆነ እና ከማኅበረሰባዊ ታሪካችን ሰፊውን ትርክት የያዘ ነው። እንደ ሀገር ስለ ሰላም ብዙ እያዜምን ፤ ከትናንት ስህተቶቻችን ለመማር ባለመፍቀዳችን አልለቅ ያለን፣ ተጣብቆ ፤ ብዙ ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለን የኖረ እና ያለ ሀገራዊ ችግር ነው ።

ሠብዓዊ እሴቶች ለዘመናት በባህል እና በሃይማኖቶች በስፋት እየተሰበኩ ባለበት ፤ የማኅበረሰቡ የለት ተዕለት መስተጋብር ውስጥ የሰላም ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ በሆነበት ሁኔታ ፤ ዛሬም ለሕዝባችን የሰላም እጦት ጉዳይ ትልቁ አጀንዳ እንደሆነ ነው። ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘም እየተፈጠሩ ያሉ ፈተናዎች ሕይወቱን በብዙ ዋጋ እያስከፈሉት ነው።

በተለይም በፖለቲካው ዓለም በአጋጣሚ ይሁን በጥሪ የተደባለቁ ልሂቃን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ዋነኛ የፖለቲካ ስትራቴጂ ከማድረግ ይልቅ ፤ የአቅመ ቢስነት መገለጫ አድርገው የማየታቸው ፤ በዚህም የመታመናቸው እውነታ ፤ አጠቃላይ የሆነው ሀገራዊ የፖለቲካ ባህል ሰላማዊ እንዳይሆን አድርጎታል ። ኃይልን እና ሴራን መሠረት ያደረገ እንዲሆን አስገድዶታል ።

በዚህም ከሁሉም በላይ ሰላማዊ ሕዝባችን በዘመኑ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል ሆኗል። ሀገርም እንደሀገር ከፍ ካለ የሥልጣኔ ማማ ወርዳ የድህነት እና የኋላቀርነት ተምሳሌት የሆነችበት የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንድትዳክር አድርጓታል። በብዙ መስዋዕትነት ያገኘናቸውን ነጻነት ምሉእ በሚያደርግ የብልጽግና ጎዳና እንዳትገኝ ተግዳሮት ሆኖባት ኖሯል።

በ21ኛው ክፍለዘመን ለሰላም የተዘረጉ እጆችን መቀበል አቅቷቸው የዘመናችን ፖለቲከኞች በጫሩት ጦርነት፤ ሕዝባችን ትናንት ላይ የቱን ያህል ዋጋ እንደከፈለ ለማስታወስ የሚከብድ አይደለም። ጦርነቱ ከፈጠረው ሠብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት አኳያ እንደ ሀገር ያስከተለው የልብ ስብራት ትልቅ የታሪክ ስብራት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ከዚህ የትናንት ስብራታችን መማር ያልቻሉ ፤ዛሬም ሰላምና ሰላማዊነትን አቅመቢስነት አድርገው የሚወስዱ ግለሰቦች እና ቡድኖች ፤ በማን አለብኝነት ፤ ኃላፊነት በማይሰማው የጥፋት መንገድ ተመልሰው ለመገኘት በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለጦርነት የሚያደርጉት ዲስኩር፤ እንደ ትናንቱ ለማንም እንደማይጠቅም በአግባቡ ሊያጤኑት ይገባል።

ከጦርነት አውርድ ፉከራ እና ቀረርቶ በስተጀርባ ያለው ፤ ሥልጣን በአቋራጭ የመያዝ ሆነ ፍላጎትን በኃል የመጫን መሻት ፤ የሕዝቦችን በሰላም የመኖር መብት ከመገዳደር ባለፈ ፤ በነገዎቻቸው ላይ ያላቸውን ብሩህ ተስፋ የሚያጨልም ነው። ምንም አይነት ትርክት እና ትርጓሜ ቢሰጠው ፤ የቱንም ያህል ሕዝባዊ ካባ ቢደረብበት፤ በየትኛውም መመዘኛ ሕዝባዊ መሠረት የለውም፤ ሊኖረውም አይችልም!

አዲስ ዘመን ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You