ብዙሃነት፣ ህብረ- ብሄራዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት

ሸማ እንደሚጥፍ መርፌ በጉራማይሌ ቀለሞች የተዋብን እኛ፣ ማንም በሌለው ብኩርናና ልእልና ሰውና ሀገር የሆንን እኛ፣ ከቀለማችን እያጠቀስን ሌሎችን የቀለምን እኛ፣ ከዚህ እስከዛ በሌለው ዳር አልባ ትቅፍቅፍ በአብሮነታችን ዓለምን ከባርነት ነጻ ያወጣን እኛ በብዙሃነት ውስጥ ህብረብሄራዊነትን፣ በህብረብሄራዊነት ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን አጽንተን ሰው፣ ሀገር እና ባለታሪክ ሆነናል።

ጭን እንዳሾረው እንዝርት በአናታችን ላይ ብዙሃነትን ጠምጥመን፣ ማንም እንዳያላላን በጥብቅ ቋጠሮ የተጣበቅን፣ መሠረቶቻችንን በፍቅርና በአብሮነት አጽንተን በውርርስ ሥነልቦና ልዩነታችን የተደባለቀ እኛ ብዙ ነን። እኔነት ባልገባበት ሕዝባዊነት፣ ተቃቅፈንና ተደጋግፈን ሀገር ያቆየን፣ ታሪክ የሠራን፣ በአንድነት ጎልምሰን፣ በልዩነት አብበን፣ በአበባችን ፍሬ አፍርተን የፍትህ ማማዎች የተባልን እኛ አጽናፎች ነን። በድብልቅ የጋራ እሴቶቻችን የጋራ ሀገር የማገርን፣ የአብሮነት መሠረት ያነጽን፣ በላቀ የመከባበር ባህል ጉምቱ ትውልድ የሠራን እኛ ፊተኞች ነን።

ማንም ያልደፈረን፣ ሊደፍረን የመጣን አሳፍረን የመለስን፣ ታላቅነታችን ሰው ሀገርና ሉአላዊነት የሆነ፣ ስለሌላው ግድ የሚለን፣ በፍቅር ካልሆነ በጥላቻ የሚበልጠን የሌለ፣ ከማንነታችን በፊት ኢትዮጵያን ያስቀደምን፣ ተጠላልፈንና ተወራርሰን በህብረብሄራዊነት ያበብን፣ በመቻቻልና በመከባበር የተደነቅን እኛ የክረምት አበባዎች ነን።

ብዙሃነት፣ ህብረብሄራዊነትና ኢትዮጵያዊነት ከትናንት ወደዛሬ የመጣንበት፣ ከዛሬም ወደነገ የምንሄድበት የክብር፣ የሉአላዊነትና የወንድማማችነት አርማችን ነው። ሰው ሀገርና ባለታሪክ ተብለን ስንጠራ፣ በፍቅርና በሰላማዊነት ስንታወቅ፣ በስልጣኔና በፊተኝነት ስንወደስ መነሻዎቻችን እነዚህ ነበሩ። ፍትህና እኩልነት፣ ነጻነትና ሰብአዊነት ቅጥያዎቻችን ሆነው ከስማችን እኩል ሲጠሩ፣ አብሮነትና ኅብረት፣ ታሪክና ሥርዓት ቀለሞቻችን ሆነው ሲያደምቁን፣ ደግነትና ሩህሩህነት፣ ጥበብና ማስተዋል ዳኛችን ሆነው ሲያራምዱን በእነዚህ ሦስት የክብር ጫፍ በኩል ነበር።

እስኪ ወደአንድ ስፍራ..በክረምት ዝናብ ወዳበቡና ፍሬ ወዳፈሩ፣ ቀለማቸውም ወደጎመራ አበቦች ልውሰዳችሁ። አረንጓዴ ወደተቀለሙ፣ ቅርንጫፋቸውን ወደሰተሩ፣ ሲታዩ የሚቦርቁና የሚፈነጩ ወደሚመስሉ ዛፎች መኖሪያ ልምራችሁ። መስኩ አረንጓዴ ነው፣ የተለያየ ቀለም ያላቸው አበባዎች መስኩን ጉራማይሌ ቀለም አጎናጽፈውታል። የተለያዩ እጽዋቶች፣ ዜማ በሚፈጥር ንቅናቄ እያሸበሸቡ፣ አጠገባቸው ካለ ሌላ ዛፍ ጋር እየተሳሳሙ ቀዬውን አሳምረውታል።

አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ፣ ሰማያዊ፣ ነጭ፣ ጥቁር፣ ቡኒ፣ ሮዝ፣ ወይንጠጅ ቀለም ያላቸው አበባዎች በደስታ ስቀው፣ በክረምት ዝናብ የፋፉ፣ የደለቡ ለምለም እንግጫዎች ስፍራውን የገነት ጓሮ አስመስለውታል። በዛ ስፍራ ንቦች ያጠዘጥዛሉ፣ እርግቦች ይፈነጫሉ። አየሩ በውብ ሽታ ከሳንባ ሲወጣና ወደሳንባ ሲገባ በልዩ ስሜት ነበር። ቦታው መንፈስ ያድሳል፣ መኖር ያስናፍቃል፣ ጭንቀት ያስረሳል፣ ትካዜ ይገነድሳል፣ ሳቅ ይፈጥራል፣ ሰላም ይሰጣል።

ይሄ ስፍራ በአንድ ቃል ቢገለጽ ህብረብሄራዊነትን ይወክላል። ህብረብሄራዊነት በአንድ ሀገር ላይ መስኩን እንዳሳመሩት አበባና ዛፍ፣ እንግጫና እጽዋት ነው። አየርና ድባብ ፣ ንቦችና ርዕግቦች ነው። የእነዚህ ሁሉ ውህድ ነው ባዶውን መስክ በአረንጓዴ ሸፍኖ፣ በአበባዎች አድምቆ፣ በዛፍና በአእዋፍት ከልሎ ልዩ ውበት የሰጠው።

ህብረብሄራዊነት በአንድ ሀገር ላይም እንዲሁ ነው። ኢትዮጵያ የደመቀችው፣ ያማረችው ከብዙሃነት ውስጥ በተወጣጡ ባህሎች፣ ወጎች፣ ሥርዓቶች፣ ልማዶች፣ ቋንቋዎች፣ ቀለሞች፣ ማንነቶች ነው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ቢጎል ወይም ደግሞ ፉክክር ቢጀምሩ ኢትዮጵያዊነት ይደበዝዛል። መስኩ ላይ አበባዎቹ ባይኖሩ አስቡት? እጽዋቶቹ ባይኖሩ አስቡት? እጽዋቶቹ ቢጎሉ አስቡት? የሁሉም ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር ነው ኢትዮጵያን ያደመቃት።

ህብረብሄራዊነት ከብዙሃነት ውስጥ የሚወለድ የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የመተሳሰብ፣ የወንድማማችነት እንዲሁም የታሪክ፣ የባህል ቀለም ነው። መስኩ ላይ ያሉት የተለያዩ ተፈጥሮዎች ብዙሃነትን ይወክላሉ። እነዚያ የተለያዩ ተፈጥሮዎች ባላቸው ችሎታ፣ በተሰጣቸው ውበት፣ በወረሱት ድምቀት እና ተፈጥሮ መስኩን ልዩ ውበት ሰጥተውታል። መስኩ ኢትዮጵያን ይወክላል። እኔና እናተን አቅፋና ደግፋ የያዘችውን ኢትዮጵያ። አበባዎቹ ያበቡባት፣ ዛፎቹ ያደጉባት፣ እጽዋቶቹ የለመለሙባት፣ አእዋፍቱ የረኩባት፣ ንቦች ያጠዘጠዙባትን ኢትዮጵያ።

መስኩ ባይኖር የእነዚህ ሁሉ ተፈጥሮ ውበት ትርጉም ባልኖረው ነበር። የመስኩ መኖር በክረምት ዝናብ ለራሱ ብዙ ተፈጥሮዎች ትርጉም ሰጥቷል። የእኛም ትርጉማችን ሀገራችን ናት። ወልደን እንድንስም፣ ዘርተን እንድንቅም የእሷ መኖር ግድ ይለናል። ወጥተን እንድንገባ፣ ተምረን ለቁም ነገር እንድንበቃ፣ ሰርተን እንድንከብር ሰላሟ ዋስትናችን ነው። አስበን እንድናሳካ፣ አልመን እንድንፈጽም ሰላሟ፣ ክብሯ፣ ሉአላዊነቷ፣ አንድነቷ፣ ወንድማማችነቷ አስፈላጊያችን ነው።

ጠልቆ የበቀለ ዛፍ መተማመኛው ስሩ ነው። ካለመሬቱ ስሩ ብቻውን ትርጉም የለውም። ዛፉ እንዲያፈራ ስሩ ጠልቆ መብቀሉ አስፈላጊ ቢሆንም ከዚህ በላይ አስፈላጊ የሚሆነው የመሬቱ አስተማማኝነት ነው። የሀገራችን ሰላም፣ ፍቅር አንድነቷ አሁን ላይ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነገራችን ነው። የሕዝቦቿ ትስስር፣ የትውልዱ ትስስብ በምንም የማናነጻጽረው አስፈላጊያችን ነው። እንደዛፉ ጠልቀን እንድንበቅል፣ ከበቀልንም በኋላ ጥሩ እንድናፈራ መብቀያ መሬት ያስፈልገናል። ያለ መሬት ሥራችን ብቻውን ትርጉም የለውም። መብቀያ መሬት ያስፈልገናል። ጠልቀን እንድንበቅል አስተማማኝ መሬት አስፈላጊያችን ነው። ውሃ የሚያጠጣን፣ የሚንከባከበን ያስፈልገናል።

ሀገራችን መብቀያ መሬታችን ናት። ሰላም ከሌላት፣ አንድነቷ ካልተረጋገጠ መብቀል አንችልም። ወንድማማችነት ካልጠነከረ፣ ቡዳኔ ከበዛ የሚነቅል እንጂ የሚተክል አይኖርም። ኦና እየሆንን ነው። በርሀነት እየወረሰን ነው። የሃሳብ ዘር፣ የፍቅር ፍሬ ያስፈልገናል። ሰላም ነጋሪ የአንድነት አፍ ግዳችን ነው። የሚነቅሉ እጆች እንዲተክሉ፣ የሚዘልፉ አፎች እንዲመርቁ ፍቅር ወለድ ትርክቶችን እንተርክ።

ትርክቶቻችን በጥላቻ የተለወሱ መርዛም ናቸው። መርዝ እየረጨን፣ መርዝ እየሰበክን ትውልዱን ስለፍቅር ልንነግረው አንችልም። ብሄርተኝነትን ዘርተን ዘረኝነትን አብቅለናል። እንዲደርቁ ከማድረግ ይልቅ እንዲለመልሙ ብዙ አስተዋጽኦ አድርገናል። ፍሬዎቻቸው መራራና ሞት ያለበት እንደሆነ እያየን ነው። ጥላቻና መገፋፋት የበዛባቸው እንደሆኑ ተመልክተናል። ድሃ፣ ኋላቀር፣ ተረጂ የሆነ ሀገርና ሕዝብ፣ በቀን ሦስት ጊዜ መመገብ ያልቻለ ማህበረሰብ ምን እንደሚያስፈልገው አለማወቃችን የሁልጊዜም አግራሞቴ ነው።

የሚያስፈልገን ፍቅር ነው። የሚያስፈልገን ልዩነቶቻችንን በውይይት አክመን የአብሮነት ጎዳና መጥረግ ነው። የሚያስፈልገን በቀል ሻሪ፣ አንድነት አብሳሪ ትርክት ነው። ደብቀን አደበዘዝናቸው እንጂ በርካታ ታሪክ ሰሪ የጋራ ትርክቶች ነበሩን። እንዳይታዩ ሸሸግናቸው እንጂ ተያይዘንና ተደጋግፈን የመጣንባቸው ከህብረብሄራዊነት ውስጥ የበቀሉ እልፍ የጋራ ጌጦች ነበሩን። ትውልዱ ተንጠራርቶ እንዳይደርስባቸው አራቅናቸው እንጂ በፍቅርና በወንድማማችነት፣ በብዙሃነትና በእርስ በርስ መተሳሰብ የበለጸጉ ከእኛ አልፈው ለጎረቤት ሀገራት፣ ከዛም ለአፍሪካና ለዓለም የተረፉ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የእርቅ፣ የይቅርታ፣ የትቅቅፍ፣ የካሳ፣ የቅጣት ባህሎች ነበሩን።

ወርቆቻችንን መግለጥ አለብን። ስንጣላ የታረቅንባቸው፣ ስንፋቀር የተወዳደስንባቸው ገዝፈንና ልቀን ሰው የሆንባቸው የብዙሃነት መልኮቻችን መታየት አለባቸው። ብዙሃነትን ሰውረን፣ ህብረብሄራዊነትን ሸሽገን በጥላቻና በዘር አስተሳሰብ የምናራምደው ትውልድ፣ የምንቀይረው ማህበረሰብ የለም። መነሻዎቻችንን እንያቸው፣ ወደ ኋላ ዞር ብለን የመጣንባቸውን የትቅቅፍና የትይይዝ መንገዶች የት ጋ እንደጎረበጡን፣ የት ጋ እንደሳትናቸው፣ በማንና በምን ምህኛት እንደራቅናቸው እንመልከት።

የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ። ሀገር ከትናንት ወደዛሬ ወደነገም ናት። በክብር ያራመዱን፣ በስልጣኔና በቀዳማይነት ያቆሙን የብዙሃነት ምንጣፎቻችን አቧራቸው ተራግፎ በትውልዱ እግር ስር ዳግም ይነጠፉ። በስልጣኔና በሰብአዊነት ያጸኑን የህብረብሄራዊነት መሠረቶቻችን ከተዛነፉበት ተቃንተው አንቱታን እንዲሰጡን ዳግም እንቃኛቸው። ሰው፣ ሀገርና ባለታሪክ አድርገው በክብር ያነጹን የግብረገብነትና የጨዋነት የሥነምግባርም አውዶቻችን ከተደበቁበት ወጥተው በትውልዱ ፊት ይገለጡ።

ከዚም ከዛም ተወጣጥተው በአንድ ስም ኢትዮጵያዊነት የክብር ካባን ያለበሱን፣ ከዛም ሲልቅ የፍቅር መለከትን የነፉልን የእዝነትና የርህራሄ ጸዳሎቻችን ከወደቁበት ይነሱ። እንዳይታዩ በጥላቻ የተሰወሩ፣ እንዳያበሩ በዘረኝነት የደበዘዙ የጋራ እሴቶቻችን ክብሮቻችን ናቸውና፣ እርቆቻችን ናቸውና፣ ሰላሞቻችን ናቸውና ማንም ዝር እንዳይል ወደወደቁበት እንሂድ። ምንም አዲስ ነገር ሳንፈጥር ባሉንና በነበሩን ማህበራዊ ሥርዓቶቻችን እርቅና ፍቅርን ማምጣት እንችላለን።

የትዕቢት ልቦች ተንፍሰው፣ የማንአለብኝነት ደጆች ተዘግተው ስለፍቅር ተንበርክከን በምንካድማት ሀገራችን በኩል መቃናት እንችላለን። የእኔ የአንተ ክፍፍል ሳይኖር እንደመጣንበት በብዙሃነት ከቀጠልን ሕመሞቻችንን መሻር ይችላሉ። ጥላቻና ዘረኝነትን ተጸይፈን፣ ኢትዮጵያዊነትን አግዝፈን እጆቻችንን ለመያያዝ ከዘረጋን፣ አፎቻችንን ከእርግማንና ከዘለፋ ወደምርቃትና ውዳሴ ከቀየርን ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል።

ብዙሃነት ውርርስ ነው። ህብረብሄራዊነት ድብልቅልቅ ነው። ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የነዚህ እልፍ ማንነቶች የወል ስም ነው። ሺ ፍልጥ በአንድ ልጥ እንደሚታሰር የእኛም እልፍ ሃሳብ፣ እልፍ አመለካከት፣ እልፍ ባህልና ሥርዓት በኢትዮጵያዊነት ታስሯል። ልዩነታችን ውበትን ፈጥሮ፣ ውበታችን አንድነታችንን አረጋግጦ በአንድ ስም እንድንጠራ ሆነናል። ይሄ የተቋጨንበት፣ ያበቃንበት፣ ተከባብረንና ተቻችለን የጸናንበት የመጨረሻ ምዕራፋችን ነው። ብሔርና ዘር ሊያላሉት አይችሉም። አሉባልታና እብለት ሊያዝሉት አቅም የላቸውም። ፖለቲካውና ፖለቲከኞች ሊሸረሽሩት አይችሉም።

ፍቅር ራሳችንን ከመከራ ነጻ የምናወጣበት ብቸኛ እጣ ፈንታችን ነው። በፍቅር እስከተራመድን ድረስ የማንደርስበት አንዳች የበረከት ወደብ የለም። ያለ ፍቅር፣ ያለአብሮነት፣ ያለወንድማማችነት እንዳንቆም ሆነን የተሠራን ሕዝቦች ነን። ወደምንጫችን እንመለስ። ተዋህደንና ተደባልቀን ወዳጸናነው ማንነታችን እንመልከት። በምክክርና በውይይት ከተራመድንባቸው ብዙ እድሎች ከፊታችን አሉ። በእርቅና በይቅርታ ከሄድንባቸው እልፍ በረከቶች ወደእኛ ሊመጡ የእኛን መተቃቀፍ እየጠበቁ ነው።

በብዙሃነት አብረን፣ በህብረብሄራዊነት ደምቀን ኢትዮጵያዊ ስንባል መነሻችንን ፍቅር መድረሻችንን ደግሞ ኢትዮጵያ አድርገን ነው። ይሄ መነሻና መድረሻ ወደነገ ለምናደርገው የበረከት ጉዞ ጥላቻን በመሰወር ረገድ ዋጋው የላቀ ነው። በለም መሬት ላይ ወድቀን፣ በደግ ሕዝብ ታርሰን በቅለንና አፍርተን ባለታሪክ ስንባል በጋራ ሃሳቦቻችን ስር ነው። በተለያዩ ክፉ ጊዜዎች ሃሳቦቻችን ነጻ አውጥተውን ባለክብር አድርገውናል። አሁንም ላሉብን ልዩነቶች ሃሳቦቻችንን እንደዋና የመፍትሔ አማራጭ በመጠቀም እርቅና ስምምነትን ባስቀደመ መልኩ መነጋገር መቻል አዋጪ ነው።

ዘመን የሃሳብ ልኬት ነው። ያለፉት ዘመናት በሃሳብ ሚዛን ላይ ተቀምጠው ጎሸዋል። አሁን ያለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ግን በሃሳብ የዳበረ፣ ለሃሳብያውያን ቅድሚያ የሰጠ በመሆን ይታማል። እናም ምን ለማለት ፈልጌ ነው…ነጻ የምንወጣው፣ ነጻነት የምንቀዳቸው፣ እንደሀገር የምንቀጥለው በሃሳብ ልውውጥ በኩል ነው እያልኩ ነው።

ተነጋግሮ ከመግባባት ውጪ የልዕልና መንገድ እንዳይኖረን ሆነን የቆምን ነን። ከመነጋገር ውጪ እንደመፍትሔ የምናስባቸው ማናቸውም ነገሮች ተቀምጦ የመወያየትን ያክል ትርጉም የማይሰጡን ናቸው። በእርቅና በፍቅር ያልታከመ ቁስል ሰንብቶ መመርቀዙ አይቀርም። ተወያይተን ወደበረታ፣ ሁሉን አቃፊና አስማሚ ወደሆነ የብዙኃን እውነት ሚዛን እንድፋ። ከዚህ የተሻለ ነጻ አውጪ እውቀትም፣ ሙቀትም የለንም።

ህብረብሄራዊነትና ብዙሃነት ለኢትዮጵያዊነት መሠረቶች ናቸው። ከብዙሃነት በተውጣጣ ህብረብሄራዊነት ኢትዮጵያዊነትን ቋጭተን ባለታሪክ ሕዝቦች ተብለናል። እንዴት ካልን..ተማክረን፣ ተፋቅረን፣ ተከባብረን የሚል እውነት ላይ እንደርሳለን። የተነሳንባቸው የታሪክ አውዶች በዳበረና በበረታ ልዕለ ሃሳብና ብዙሃነ ህብራዊ ላይ የቆሙ የህያው መሠረት ምስክሮች ናቸው።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You